የነገደ አማራን ሕዝብ የህልውናን ትግል ታግሎ በማታገል ደረጃ የመጀመሪያዋን አስጀማሪ የትግል ጥይት የተኮሰው ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ – እጅግ ከለፋበትና ብዙ ዋጋ ከከፈለበት አዲሱ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ አመራር አባልነት በአስገዳጅ ሁኔታ እራሱን ሊያገል እንደቻለ አስታወቀ!!!
ታላቁ አርበኛ እራሱን ከአዲሱ አደረጃጀት እንዲያገል ያስገደዱት አስገዳጅ ሁኔታዎች ምንድናቸው???
ጋዜጠኛ ወንድወሰን ተክሉ
*** የህልውናውን ትግል ያስጀመረን ታላቅ አርበኛን ማቀፍና ማካተት ያልቻለ የፋኖ አደረጃጀት ለነገደ አማራ ሕዝብ ህልውና ጥብቅና መቆም የሚችል ነው ብሎ መቀበል እጅግ ያዳግታል!!!
አርበኛው አዲስ ከተመሰረተ የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ አመራር አባልነት እራሱን አግላል። ይህ የሆነው የአዲሱ የአማራ ፋኖ አደረጃጀት ከታወጀ አምስተኛ/ ስድስተኛ ቀን በኃላ ቢሆንም አርበኛው እራሱን ያገለለበትን አቢይተ ምክንያት ባስራጨው አጭር ደብዳቤ ላይ ፈጽሞ አልጠቀሰም። በአጭሩ ”
በቅድሚያ፣ በአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ ምስረታ የተሰማኝን ደስታ መግለፅ እወዳለኹ። የዚህ ታሪካዊ ድርጅት ምስረታ አካል በመሆኔ ትልቅ ክብር ይሰማኛል።
በአዲሱ ውህድ ድርጅታችን ውስጥ የፖሊት ቢሮ አባል ሆኜ መሥራት እንደማልችል ታውቆ፣ በተመደብኹበት ቦታ ላይ ሌላ ሰው እንዲተካ አሳስባለኹ።
ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በተራ የድርጅት አባልነቴ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደምቀጥል እና የሚጠበቁብኝን ኃላፊነቶች እና ግዴታዎች በሙሉ እንደምፈፅም በዚህ አጋጣሚ አረጋግጣለኹ።
በመጨረሻም፣ ድርጅታችን አፋብን እና አዲሱ አመራር የተጣለባቸውን ታሪካዊ ኃላፊነት በሰኬት እንዲወጡ ልባዊ እና ጓዳዊ ምኞቴን እገልፃለሁ።
ከአክብሮት ሰላምታ ጋር ፣
እስክንድር ነጋ። ” በሚል ድፍን ያለ መልእክት ከተሰጠው ኃላፊነት እራሱን በማግለል በተራ አባልነት እንደሚታገል ነው አርበኛው የገለጸው።
የነገደ አማራን ሕዝብ ህልውናን ለመጠበቅ ታላቁ አርበኛ በአማራ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ በአይነቱ ልዩ የሆነን ትጥቅ ትግልን በግንቦት 20 ቀን 2023 የአማራ ሕዝባዊ ግንባርን በመመስረት የህልውናውን ትግል ያወጀ ልዩ አርበኛ ነው። የአማራ ፋኖ የብልጽግናው ፋሺስታዊው ስርአት ከህወሃት ጋር በሚዋጋበት ወቅትና የአማራ ክልል ጎንደር፣ ወሎና ሸዋ በህወሃት በተወረረበት ወቅት በተካሄደ ስድስት ግዜ ክተት ጥሪ እራሱን አደራጅቶና በጎበዝ አለቃ አሰባስቦ ወያኔ ላይ ሲዘምት ከፋሺስቱ የብልጽግና ሰራዊት (መከላከያ ሰራዊት ) ጎን ለጎን ሆኖ በአንድ ምሽግ ሲዋጋ ስለበረ ይህንን አማራዊን ሀይል የታጠቀውን አፈሙዝ በ”መከላከያ” ተብዬው የፋሺስቱ ሰራዊት ላይ እንዲያዞርና እንዲተኩስ ያደረገው ብቸኛው ሰው ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ብቻ እና ብቻ ሲሆን ከዚያን ግዜ ጀምሮ የትግሉ አድማስ እጅግ በመስፋት በአራቱም ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ያሉትን የፋኖ አደረጃጀቶችን በአንድ አማራዊ አደረጃጀት ስር ለማደራጀት ታላቁ አርበኛ ሁለት አደረጃጃቶችን – ማለትም የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ሰራዊት እና የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን በመመስረት የበኩሉን ታላቅ ሚና እና ድርሻን መወጣት ችላል።
የህልውና ትግሉ ከፈነዳበት ግንቦት ወር 2023 ጀምሮ ለአምስተኛ ግዜ አምስተኛ ድርጅት የሆነው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ ( አፋብን) ከስድስት ወር ያላነሰ ብርቱ ስራ በሃላ ሰሞኑን በይፋ የተመሰረተ ሲሆን ታላቁ አርበኛ እስክንድር ነጋ ለዚህ ድርጅት መመስረት ታላቅ አበርክቶንና ዋና አስተዋጾኦን በማበርከት ለድርጅቱ መመስረት የራሱን አሻራ ያኖረበት ድርጅት የተመሰረተው። እንዲያም ሆኖ ይህንን ታላቅ ዋጋ የከፈለበትን ድርጅት ማለትም የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ የፖሊሲና የእስትራቴጂ መምሪያ ኃላፊነትን ባለመቀበል ከ19 አባላት ካሉት የፖሊት ቢሮ አባልነት እራሱን በማግለል በተራ አባልነትና በተራ ታጋይነት እንዲሚቀጥል አስታውቃል።
የአርበኛው ውሳኔ ብዙዎችን እጅግ አስደንግጣል። ብዙዎችንም እጅግ አናዳል፣ እጅግም አስደስታል። የሁለቱም ወገኖች – ማለትም በአርበኛው እራሱን ከኃላፊነት ማግለል እጅግ የተናደዱትም ሆነ የተደሰቱት ለአመታት አርበኛውን በጽናት ሲከተሉ የቆዩ ተከታዮቹና ደጋፊዎቹ ሲሆን የንዴታቸውና የደስታቸው ምክንያትም
፩ኛ- አርበኛውን የማይመጥን ኃላፊነት ቦታ ላይ እንዴት ሊመድቡት ቻሉ በማለት የተናደዱና
፪ኛ- አርበኛው ይህንን የማይመጥነውን ኃላፊነት ጥሎ በመውጣቱ የተደሰቱት ደጋፊና ተከታዮቹ ናቸው ሁለት የተቃረነ ስሜት የንዴትና የደስታ ሲያንጸባርቁ የታዩት።
*** ለመሆኑ አርበኛ እስክንድር ነጋ የተሰጠውን ኃላፊነት እንዳይቀበል ያስገደዱት አስገዳጅ ሁኔታዎች ምንድናቸው ???
እርበኛ እስክንድር ነጋ ከአፋብን ኃላፊነት እራሱን እንዲያገል ያደረገውን አስገዳጅ ሁኔታን ባሰራጨው አጭር ጽሁፍ ውስጥ ፈጽሞ ያላሰፈረ ቢሆንም እጅግ ከለፋበት እና ከደከመበት የአማራ ፋኖ ብሄራዊ ንቅናቄ ድርጅት ኃላፊነት እራሱን ሊያገል የቻለው ወዶና ደስ ብሎት ሳይሆን እጅግ አስገዳጅ በሆኑ ሁኔታዎች ተገዶ እጅግ ብዙ ከደከመበት ድርጅት እራሱን ሊያገል እንደተገደደ መናገር ይቻላል።
እነዚህ አስገዳጅ ሁኔታዎችን ለአብነት ለማስቀመጥ ያህል
፩ኛ- የአፋብን ድርጅት አመራር ምደባ በድርጅቱ ሕግና ደንብ መሰረት ሁሉን ባሳተፈ ምርጫ ከማካሄድ በጥቄት ግለሰቦች ማን አለብኝነት እና እብሪት የአመራር ኃላፊነቱ በምርጫ ሳይሆን በምደባ በመደላደሉ
፪ኛ- በኃላፊነት ቦታ የተመደቡ አመራሮች ፍቃደኝነት ባለመጠየቁና እንዲሳተፉበት ባለመደረጉ
፫ኛ- ሁለቱ ድርጅቶች ማለትም – አፋሕድ እና አፋብኃ በ Memorandum of Understanding (MoU) መሰረት ከተስማሙበት ስምምነት ውጪ እጅግ ጥቂት የሆኑ ግለሰቦች ይህንን የስልጣን ድልድል በዘፈቀደ የፈጸሙ በመሆኑ
፬ኛ- ሁሉም አመራሮች ከአርበኛ ዘመነ እስከ ታላቁ አርበኛ እስክንድር ሁሉም በእኩልነት እና በፍጹም ድርጅታዊ ዴሞክራሲያዊነት መሳተፍ ሲገባቸው ድርጅታዊ ዴሞክራሲን ደፍጥጦ በጨፈለቀ መልኩ የጥቂት ግለሰቦችና ቡድኖች ፍቃድና ይሁንታ ተፈጻሚ መደረጉ እና
፭ኛ- ሁሉም ነገር ለሕዝብ ይፋ ከመደረጉ በፊት ሁሉም የድርጅት አመራሮችና አባላት አውቀውት፣ ተስማምተውበትና ፈርመውበት መገለጽ ሲገባው ይህንን ሂደት ሳይከተል የድርጅት ምስረታውና የስልጣን ድልድሉ ይፋ በመደረጉ ታላቁን አርበኛ ሳይወድ በግድ ከተመረጠበት ሳይሆን በጥቂቶች ፍላጎትና ችሮታ ከተጣለበት ኃላፊነት እራሱን እንዲያገል ያስገደደው ሁኔታዎች ውስጥ በጥቂቱ የሚጠቀሱ ናቸው።
የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ (አፋብን) የአፋሕድ እና የአፋብኃ ጥምረታዊ አንድነት ውጤት የሆነ አደረጃጀት ቢሆንም ለዚህ አማራዊ አንድነት እውን መሆን የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን ያህል የቃተተ፣ እጅግም ለአንድነቱ ዋጋ የከፈለ አለ ብሎ ለመግለጽ እጅግ ይከብዳል። በተለይ የሊቀመንበሩ ታላቁ አርበኛ እስክንድር ሚና በቃላት ተነግሮ የማያልቅ እጅግ ወሳኝ የመሆኑን ያህል ድርጅቱ ተመስርቶ በኃላፊነት ድልድል ላይ ግን ለአንድነቱ እጅግ የታከቱት ገሸሽ ተደርገውና አቅማቸውን የማይመጥን ስፍራ እንዲሰጣቸው ተደርጎ ይፋ መደረጉ እጅግ ብዙዎችን አስቆጥታል።
























