ለኔ ቴዲ አፍሮ “በኢቶሪካ” አልበሙ ከሎሬት ፀጋዬ እና ሙሉጌታ ተስፋዬ የብእር ዙፋን ተርታ በብቃትና በኩራት ተንሰራፍቶ ተቀምጧል። ለቴዲ ያልሆነ ሎሬትነት ይበጣጠስ ብያለሁ። ይህ የድፍረት ቀረርቶ አይደለም። በብቃት አድርጎታል። የታገሰ ሐሳቤን ተመልክቶ ይፍረድ።
ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ) “እውነት ከመንበርህ የለህማ” በሚለው ዘላለማዊ ግጥሙ ፣ “ሐቅ” ፥ ፍትህ ፥ ርትእ፥ ከመለኮት የሆነው “እውነት” ከመንበርህ የለህ ሆኖ እንጂ ፣ ይህ ሁሉ ግፍና መከራ በህዝባችን ላይ ሲወርድ ዝም አትለንም ነበር፤
“ምነዋ መንግስተ ሰማይ የምህረትሽ ቀን ራቀ፤
ምነው ትንግርትሽ ረቀቀ?
ምነው ኪዳንሽ ታጠፈ፥ ወዝሽ ወዘናሽ ነጠፈ?”
. . . እያለ አጥንት ድረስ ዘልቀው በሚሰሙ ቃላት ፤ የዚህን አለም የሞራል ካስማ ከምሰሶው በሚያንቀጠቅጡ ቃላት ይሞግታል። ቅኔው ከሮ ሲጦዝ ደግሞ በግልፅ ቃላት አምላክን ደፍሮ ይከሳል። ይህ የአያሙሌ ድንቅ የጥበብ እንባ በ1977 ዓ.ም. የተከሰተውን ፥ ዛሬም ድረስ አለም ፊት እንደ ኢትዮጵያዊያን መልክ ተቀርፆ የቀረውን አሰቃቂ ረሃብ ፣ሰው እንደቅጠል ሲያረግፍ በአቅመቢስነት ካየ በኋላ ነበር “እውነት ከመንበርህ የለህማ” የሚለውን የግጥም ፍላፃ እየተቃጠለ የፃፈው።
የማይነጥፈው የኢትዮጵያ ማሕፀን ያፈራው ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አያ ሙሌ የ”እውነትን” ከመንበሯ መሰወር እንደሞገተው ሁሉ ፣ ቴዲ አፍሮ “ዳስ ጣል” በሚለው ዜማው የዚያን “የተከዳ” ፥ የተዋረደውን ዛሬ ላይ ያለን ኢትዮጵያዊያን “የእውነታችን የሐቃችን መልክዓምድሩን” እንከን በማይወጣላቸው ቃላቶቹና ዜማው ቅርፅ አድርጎ ይስለዋል። እውነትን ሐቅን ሲያነቡ የሁለቱም ባለቅኔዎች ብዕሮቻቸውን አንድ ድምፅ ያወጣሉ። የቴዲ ግን የሚለየው ፣ አሳዛኙን የኢትዮጵያን ሐቅ በግጥም ብቻ ሳይሆን በዜማ ህያው አድርጎ ቁልጭ አድርጎ ያንቆረቁረዋል።
በዜማው የኢትዮጵያን እውነታ የሚያሳይ “ዳስ ጣል” የሚባል መስታወት ይዞ ህሊና ባለው ሰው ሁሉ ፊት ቆመ። በነገራችን ላይ “ዳስ ጣል” ቅንብሩን ላስተዋለው ከልክ አልፎ የሚደለቅ ከበሮ የለውም። ውስጡ ያለው ሐቅ በሽብሸባ የሚነገር በመሆኑ ይመስለኛል። ሐዘን ላይ መተናነስ እንጂ የደስታ ድቤ አይደለቅም። በዜማው መጨረሻ ላይ ያለው ፉከራም የዚህ ዜማ ፈውሱ ፥ መድኃኒቱ ነው። ከተጣለው የሐዘኑ ዳስ ውስጥ ጨክኖ መነሳትን በወኔ በፉከራ ያበስራል። ቴዲ ከአያ ሙሌ የሚለየው በዚህ ነው። ከመንበሩ የጠፋውን እውነትና ልብ ሰባሪው የሐቅ ሸለቆን ብቻ ሳይሆን ፣ ኢትዮጵያ ካለችበት የድባቴ ሸለቆ ተወጥቶ የተራራው ጫፍ ጋር እንዴት እንደሚደረስ በቀረርቶ ይጠቁማል። ፈውስ እንካችሁ። ከዚህ በፊት አደጋ አጋጥሟቸው የተሻገሩ አባቶች አሉህና “ካነሳኸው” ተስፋ አለ ይላል።
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅንም እንደዚሁ ጴጥሮስ ሐውልት ስር ሰክሮ የሚሸና ጀብራሬ ሲያይ ፣ በወጣትነት ግለቱ ላይ ንዴት ተርከፍክፎበት፤ ከአቡነ ጴጥሮስ በላይ ሰማእት እና ጀግና ከየት ሊገኝ ይህ ሁሉ ንቀት ብሎ ፣ ከድንጋይ በላይ ህያው የሆነው የአቡነ ጴጥሮስን ድንቅ ስብእና በግጥሙ አስፍሯል። “እንኳን ህዝቡን ምድሩን ገንዤዋለሁ” ብለው እምቢኝ በማለታቸው በመትረየስ ተደብድበው ከመገደላቸው በፊት በስነጥበብ ቅባቱ ፥ አቡነ ጴጥሮስ ከእመብርሃን ጋር ፈተናቸውን የሚጋሩባቸውን ምልልሶች መቃተታቸውን በብእሩ ድንቅ ሰረገላ እየቀዘፈ፤ ሊረሽኗቸው ከቆረጡት ጣሊያኖች ፊት ሆነው አቡነ ጴጥሮስ የፀኑበትን አፍታ,
“አየ፥ ምነው እመብርሃን? ኢትዮጵያን ጨከንሽባት?
ምነው ቀኝሽን ረሳሻት?
. . . ያቺን የልጅነት ምስራች? የህፃንነት ብስራት፣
የሣቅ የፍንደቃ ዘመን ፥ የምኞት ተስፋ ብፅአት፤
ያቺን የልጅነት እናት?
አዛኚቱ እንዴት ብለሽ ፥ ጥሮሶችሽን ነከስሽባት?
. . . እያሉ እንደ በገና ልብ የሚሸረሽሩ ቃላት በምልሰት “ሰቆቃወ ጴጥሮስ” ጴጥሮስ ያቺን ሰአት በሚለው ቲያትራቸው ላይ የከተቡት። የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ድንጋዩ መናቁ አልነበረም ሎሬትን ያሳዘነው ስህተት። ቁምነገሩ ሐውልቱ የወከላቸው ሰው የሚወክሏት ሐገር ኢትዮጵያ እና የአርበኝነትን ዋጋ መናቅ ነበር። ይህ ኢትዮጵያ እንደ ሐገር በየ ትግል ሜዳው ተሰዉተው አገር ያፀኑ ጀግኖችን ማዋረድ አገር ያሳጣል የሚለው ቁጭት ነበር። ቴዲ አፍሮ ደግሞ ያንን አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ላይ ለመሽናት ያልከበደውን ጀብራሬ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያዊያን በዘር እንድንከፋፈል ሌት ተቀን የተሰራበትን ቀመር ጣጣ ፥ “ስምምነ” በሚለው ዜማው ቅልብጭ አድርጎ ያቀርበዋል። ለቴዲ “ጴጥሮስ ያቺን ሰአት” ቲያትር ላይ አቡነ ጴጥሮስን ለመረሸን የሚሰለፉት የፋሽስት ተኳሾች – ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ክፍፍል ቀመር ህግ የሆነበት አሁንም እየሆነ ያለበት ተቃርኖ ነው። ከመጠፋፋት ውጪ ያመጣው መፍትሔ አለመኖሩንና አለመስራቱን በዜማው ውስጥ የሚናገረውም ለዚያው ነው። ልክ እንደ “ዳስ ጣል” አጥብቆ ለሰማው ይኼኛውም ዜማ (“ስምምነ”) የሚሰራ የሚመስለውን የመፍትሔ ሐሳብም ያቀርባል።
“መሬማ”
ከልጅነት እስከ እውቀት የኖርኩበትን ኢትዮጵያዊያንን በአንድ ቃል ሳል ተብዬ ብጠየቅ የሚመጣልኝ “አዛኝ” የሚለው ቃል ይመስለኛል። ይሄንን ማህበረሰባዊ እሴት በጥበብ ተንቆጥቁጦ የሚገለፀው ደግሞ ፥ “መሬማ” በሚለው የቴዲ ዜማ ነው። ካገር የወጡ ሰዎች “ዳያስፖራ” በሚል ግርድፍ ቃል በሚጠሩበት በዚህ ዘመን ፥ ቴዲ በአረብ አገራት ለተሰደዱ ወገኖቻችን በቃላትና ዜማው ያፈሰሰው እንባ የአልበሙ እንቁ ፥ እርሱንም የሰው እንቁ መሆኑን ያረጋገጠበት ነው። እንደ ሰው ሞልቶላት ፥ የቤተሰቦቿን ህይወት ልትቀይር ካገር የምትወጣ ሴት ፥ ያሰበችውን ከፍታ ሳይሆን በተቃራኒው የሰውነት ስብእናዋን ተገፍፋ ከሰው በታች ስለምትሆነው “መሬማ” መርየም ፥ ሄዋን፤ የሁላችን እህት “ጠጋ ብለሽ አውጊኝ እስኪ ያለሽበት ሁኔታውን ንገሪኝ እያለ አብሮ ያነባል። አይ ቴዲ! የማያባራው ድንቅ ብቃትህን ቃላቶች ሁሉ በልክህ መግለፅ ያቅታቸዋል። በሰብአዊ ሚዛኑ ፣ ለአዛኙ የኢትዮጵያዊያን ስብእና እጅግ በጣም የቀረበ፤ “መሬማ” የዚህ አልበም ፈርጥ ነው። የመከራችን ከአገራዊ ሐዘን እስከ ግለሰብ ድረስ የዘለቀ ጥልቀት እንዳለው እና እንዳሰቃየን ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ የጉድ ስንክሳር ማሳያው ነው መሬማ።
“ጀምበር”
በ”ጀምበር” ስራው ቴዲ አገራዊ ድባቴያችንን የኛ በሐምሌ ጨለማው መስሎ ከላያችን ላይ እንዲገፍ ሲል የህዝብ ምልጃ እኛን ወክሎ ያቀርባል። የቀደመውን ፀሐይንም በትውስታ ይከስታል። የሞቀውን የቤቱን ወጋገን ይንቃል። ሊመጣ ያለውን ጉም ቢፈራም ፤ የሚዘንበውም አመዳይ ቢጠላውም ማልደኝ ይላል። “ብርሃን አውሰኝ ፥ ብርሃን አውሰኝ” እያለ ይለምናል። ጀምበር የአልበሙ የመጨረሻ ስራው ነው። ጥቂት ዜማዎች ቀደም ብሎ 15ኛው ዜማው ላይ ፣ አማኙ ቴዲ ፀሎቱ ተመልሶ በሰርግ ዜማ ይጨፍራል። ተክዘን የቆምነውንም በ “ፅዮን ሙሽራዬ” ይወርፈናል።
“የቄዳር አበባ ነሽ ኢትዮጵያዬ” እያለ እያቆላመጠ ሲያምርባት ሲል ፣ ጥጋቸውን ይዘው ለሚያዩት ፥ ለምናየው፥
“የት ወለም ዘለም ትላለህ፤
አምሳለ ጦቢትን ስንድር እያየኽ፤
“የት ወለም ዘለም ትያለሽ፤
ዳግማዊት ሄዋንን ስንድር እያየሽ፤ . . እያለ ወዳመነው የትንቢቱ ብስራት ይጋብዘናል። እኔ ስእለቴ የሰመረ ቀን እገናኝኃለሁ ቴዲዬ!
“ፅዮን ሙሽራዬ”
በህይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘፈን ሰምቼ ስእለት ተስያለሁ። የቴዲ ዘፈን ሐጥያት ሊሆን እንደማይችል ያወቅኩት በዚህ ነው። ዘፈን ሰምቼ ቀጥታ ተሳልኩ። የእናቴ ስእለት ጠብ ስለማይል ለርሷም ተሳይልኝ ብዬ ደውዬ ነግሬያታለሁ። የተሳልኩት “ለቀን” ነው። የሞላልኝ ቀን ስእለቴን አስገብቼ እጨፍራለሁ። ያቺ ቀን ትናፍቀኛለች። ፅዮን እማምላክ እናቴ ማርያም በደጇ መድኃኒዓለም ስእለቴን ሞልቶልኝ ፥ በ”ፅዮን ሙሽራዬ” ነብሱን ይማረውና አባቴ በጥምቀት ማግስት ይጨፍር የነበረውን ያንን የምንጃር ጭፈራ በሚካኤል ንግስ እደልቃለሁ።
በልጅነት ድሬዳዋ በከተራ ምሽት የሚጀመረው የጥምቀት የደስታ ማራቶን የሚቋጨው በጥምቀት ማግስት በሚካኤል ንግስ ነበር። ከዚራ በሚገኘው የሚካኤል ቤተክርስቲያን ያለው የአባቴ እና የጓደኞቹ ጭፈራ ይሰጠኝ የነበረውን የደስታ ስሜት ፥ በፅዮን ሙሽራዬ ዜማ ከእንባ ጋር በስንት አመቱ ዛሬ ላይ ፅዮን ሙሽራዬ”ን እየሰማሁ ተመለሰ። ስንቴ እንደሰማሁት አላውቅም። በ”ፅዮን ሙሽራዬ” ላይ ጮቤ የሚረገጥበት ደስታ ግን የትንቢት ነው። ቴዲ ያመነውን ትንቢት እኔም አምኜበት በደስታ አነባሁ። “ዳስ ጣል” ላይ ቴዲን ሰብራ ሸለቆ ውስጥ ሆና ከዚህ በላይ ሀዘን የለምና “ዳስ ጣል” ያስባለችው ኢትዮጵያ፤ የዳስ ጣልን ጥልቅ ሐዘን ቀጥሎ በአልበሙ የጨረሻ ዜማ “ጀምበር” ላይ ብርሃን ተጠምቶ “ጀምበር ልይሽ ባይኔ” እያለ ህዝብን ወክሎ የቃተተው ቴዲ ፥ በ”ፅዮን ሙሽራዬ” ትንቢቱ ደስታ ሆኖለት አምሳለ ጦቢትን ቆሞ ይሞሽራል። በትንቢቱ ተማምኜ ፥ እኔም ስእለት ተስዬ ያንን ቀን እስካየው ከልቤ እናፍቃለሁ።
በጦርነት የምትታምስ ፥ ሰው በዘሩ ምክንያት የሚታረድባት ፥ ከዶክተር እስከ ገበሬ የኑሮ ቀንበር የተንሰራፋባትን አገር በዚያ ሁሉ ዘፈን ቁልጭ አድርጎ ገልፆ ሲያበቃ ፤ ኢትዮጵያን ሙሽራ ሆና “የፍቅር እናት” አደርጎ በ”ፅዮን ሙሽራዬ” ያቀርባታል።
አይ ቴዲ አንተ ብቁ! አንተን የፈጠረው አምላክ ሲያምርበት ብዬዋለሁ። አባቴ በህይወት አጠገቤ ባይኖርም በ“ፅዮን ሙሽራዬ” ስራህ፥ በስደት ብቻዬን ሆኜ የልጅነቴን ደስታ ዳግም እንዳጣጥም እድል ስለሰጠኸኝ ዘርህ ይባረክ። አንተ የተወለድክባት ቀን ትባረክ።
Elixir reflections
Elixir @YimaYada On X



















