>

“ የህዝቡ የመብት ጥያቄ መብትን የሚጥስ አዋጅ አይመለስም  (ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም)  

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚደነገግ አይደለም፡፡ ሁለት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው አዋጁ ሊጣል የሚችለው፡፡ አንደኛው ግልፅ ጦርነት ሲኖር ነው፡፡ ያንን ጦርነት ለመወጣትና በሀገር ላይ የተቃጣን ጥቃት ለመከላከል ሲባል፣ በጊዜያዊነት የሰብአዊ መብቶች ሊገደቡ ይችላሉ፡፡

ሁለተኛው የተፈጥሮ አደጋ ሲከሰት ነው፡፡ ለምሳሌ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ የጎርፍ አደጋ የመሳሰሉትን በሙሉ አቅም ለመቋቋም ሲባል፣ አዋጁ ሊታወጅ ይችላል፡፡ አሁን ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ፣ ሰው አደባባይ ወጥቶ፣ በሰላማዊ ሰልፍ መብቱን ነው የጠየቀው፡፡ ይሄን ያህል ለሀገር ደህንነት የሚያሰጋ ነገር ስለመኖሩ አስረጂ ማግኘት አይቻልም፡፡ ከዚህ አንፃር አሁን በሀገሪቱ ያለው ሁኔታ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚጠይቅበት አይደለም፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የመብት ጥያቄ ነው፡፡ ይሄ ጥያቄ የበለጠ መብትን የሚጥስ አዋጅ በማወጅ አይመለስም፡፡ ምላሽ ሊያገኝ የሚችልበት ብቸኛ መንገድ፣ ውይይትና ፖለቲካዊ ማሻሻያ ነው።

አሁን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ ግን ይሄን ውይይትና የፖለቲካ ንግግር ለማድረግ አይመችም። አዋጁ የበለጠ ጉዳዩን አክርሮ፣ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ እንዳይፈጥር ስጋት አለኝ፡፡ ጉዳዩንም የበለጠ ያሰፋዋል እንጂ አያሻሽለውም። ህግና ቅጣት ማብዛት ወንጀልን አይቀንስም፡፡ የበለጠ ያባብሰዋል፡፡ በአጠቃላይ እንደኔ ምልከታ፣ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚጋብዝ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ስልጣን መልቀቃቸው ብዙም የሚያመጣው ለውጥ አለ ብዬ አልገምትም፡፡ ኃይለማርያም ቢሄዱ ሌላ ይመጣል፡፡ ሰውን መለወጡ ምንም ትርጉም የለውም፡፡ ዋናው ስርአቱን ነው ማስተካከል የሚያስፈልገው፡፡ የአቶ ኃይለ ማርያም መለወጥ የፖሊሲ ለውጥ አይሆንም፡፡ የህዝቡ ጥያቄ የግለሰብ ለውጥ ሳይሆን የፖሊሲ ለውጥ ነው፡፡ ወሳኙ ጉዳይ፣ መሰረታዊ የህዝብን ጥያቄዎች መመለስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ገዥው ፓርቲን፣ ተቃዋሚዎችን እንዲሁም የሲቪክ ማህበራትን ያካተተ የሽግግር መንግስት ቢቋቋም መልካም ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

Filed in: Amharic