>

ሰዓት እላፊው – (በዕውቀቱ ሥዩም)

” አንገብጋቢ ችግር -አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት- አስቸኳይ ጊዜ አዋጂ- ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ደባሪ ነገሮች በሙሉ “ፈጣን”ናቸው፡፡ በፍጥነት መጥተው ደሞ በፍጥነት አይመርሹም ፡፡ ድንኳን ተሸክመው መጥተው ከተማቸውን በላያችን ላይ ሠርተውብን ይቀራሉ፡፡

በነገራችን ላይ“ የቁርጥ ቀን ልጅ” ማለት ቁርጥ በሚበላበት ቀን የተወለደ ልጅ ማለት ነው፡፡ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡

ሰሞኑን በምትገምቱት ነገር ምክንያት ስለፖለቲካ ላልጽፍ ወስኛለሁ፡፡ ቀን እስኪያልፍ ስለ ወሲብ እየተማማርን እንቆይ፡፡

ለወንዶች፤ ከሴት ጋር ወሲብ ሲያደርጉ በፍጥነት ይጨርሳሉ ?ገንዘብዎትን ማለቴ ነው፡፡ መፍትሄው ቀላል ነው፡፡ በደመወዝ ማግስት በችቺኒያ በኩል አይንዱ፡፡

ግን የምር፤ ከፍቅረኛዎት ጋር ወሲብ ሲያደርጉ ለረጅም ጊዜ መቆየት ይፈልጋሉ? መፍትሄው ቀላል ነው፡፡ ሲወስቡ፤ ሌላ ነገር ያስቡ፡፡ ለምሳሌ ስለ ጸረ-ሽብር ሕጉ ያስቡ፡፡ ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስቡ፡፡

ይህንን ካደረጉ በፍጥነት የሚረጩት እንባዎትን ብቻ ነው፡፡ ለፍተሻ ምኝታቤትዎ የሚገባው ፖሊስ “ለዛሬው ይበቃል “ብሎ ማጅራትዎትን ጨምድዶ እስኪያላቅቅዎ ድረስ ከፍቅረኛዎት ገላ ላይ አይወርዱም፡፡

መንግሥትን “ እኛ ወደ ቤተመንግሥትህ ድርሽ እንደማንል ሁሉ አንተም ወደ ቤታችንና ወደ መስርያ ቤታችን ድርሽ አትበል! በቃ leave us alone ” ስንለው” ዲሞክራሲ ባንድ ጀንበር አልተገነባም “ ብሎ ይገግምብናል ፡፡

እንደ እግዜር አቆጣጠር አንድ ሺህ ዘመን አንድ ቀን ነው፡፡ እንደ መንግስት አቆጣጠር ሃያ አምስት አመት አንድ ጀንበር ነው፡፡

ሳይታገል የሚያታግለን ፓርቲ በበኩሉ ተነሡ ሲለን ስንነሣለት፤ ተደብደቡ ሲል የቆመጥ በረከት ስንቀበልለት ኖረን “ድሉ የታለ?” ስንለው“ ትንሽ አሥር ዓመት ታገሡ፤ ትግሉ ረጅምና መራራ ነው “ይለናል፡፡

መልካም ነገሮች ለመምጣት ረጅም ጊዜ የሚፈጂባቸውን ያክል ፤ክፉ ነገሮች ከቀጠሮው ሰአት ቀድመው የሚጠብቁን ለምን ይሆን?

ስኬት ድልና ጤና
ዳምጠው እንደሚባለው መኪና
ፈጥነው መቸም አይደርሱ
እድሜና ትግስት ሳያስጨርሱ
ችግር ደዌና አፈና ፤ የክፉ ሰውም ኢላማ
ፍጥነታቸው የብርሀን፤ ባሕርያቸው የጨለማ ፡፡

” አንገብጋቢ ችግር -አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት- አስቸኳይ ጊዜ አዋጂ- ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ደባሪ ነገሮች በሙሉ “ፈጣን”ናቸው፡፡ በፍጥነት መጥተው ደሞ በፍጥነት አይመርሹም ፡፡ ድንኳን ተሸክመው መጥተው ከተማቸውን በላያችን ላይ ሠርተውብን ይቀራሉ፡፡

በነገራችን ላይ ፤ የሽግግር መንግሥቱ ላልተወሰነ ጊዜ ተሸጋገረ የሚባለው ነገር እውነት ነው?በጣም የሚገርመው ነገር፤ በውጭ አገር የሚኖሩ ጮሌዎች የሽግግር መንግሥት ቻርተር ሲያረቁ ይውላሉ፡፡

አገር ቤት የሚኖረው ጮሌ ደግሞ ወደ ፈረንጅ አገር የሚሸጋገርበትን መንገድ ሲያረቅ ይውላል፡፡ እንዴው ምን ይሻላል?

ባለፈው ቅዳሜ በእኩለቀን ላይ አንዱ እዚህ እኛ ሠፈር ፤ ቤቱ ውስጥ ሆኖ፤
“አትነሣም ወይ ?!
አትነሣም ወይ
አትነሣም ወይ ?”
እያለ ቀወጠው፡፡ ከጥቂት ደቂቃ በኋላ አካባቢውን የፖሊስ ብረት ለበስ መኪና ወረረው፡፡ አንድ አየር ወለድ ፖሊስ ባጃጅ ከምታክል አገር- በቀል ሄሊኮፍተር በገመድ ሲወርድ ታየ፡፡ የፖሊስ አዛዡ ተገን ይዞ፤ ባሊ በሚያክል የድምጽ ማጉያ “ ባለመፈክሮች ተከባችኋል፡፡ እጃችሁን ወደ ላይ ሰቅላችሁ ውጡ” በማለት አስጠነቀቀ፡፡

ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጎረቤታችን አቶ ካሣ-ኖቫ ሙታንታ ብቻ እንደታጠቀ ፎጣ ካገለደመች ጨብራራ ሴት ጋር እጁን ዘርግቶ ወጣ፡፡

“ማን አባህን ነው አትነሣም እያልክ የምትቀሰቅሰው ?አለ የፖሊሱ አዛዥ ገና እንዳየው፤
“ብልቴን ነው ጌታየ!ትንሽ ቅሜ ስለነበር አልነሣም ብሎ ገገመብኝ ፡፡

ውድ አንባቢ እስካሁን የጻፍኩት መግቢያ ነው፡፡ አሁን ዋናው መጣጥፍ ይቀጥላል፡፡ ሠአት እላፊ ከየት ወዴት?
በቅርቡ እንደሚታወጅ የተነገረው ሰአት እላፊ ያዲሳባን የ”ምሽት ክለብ“ ወደ ቀትር ክለብነት ከመቀየር ያለፈ ጥቅም ሊኖረው ስለማይችል እንዲቀር ጥሪየን አስተላልፋለሁ፡፡ ትዝ ይለኛል ፤ ልጅ እያለሁ ሰአት እላፊ ተቆጣጣሪዎች ሮንድ ይባሉ ነበር፡፡

በጊዜው አንድ ልጅ ተወልዶ የማይረባ ሆኖ ከተገኘ“አንተ በተጸነስክበት ቀን ምናለ አባትህ ሮንድ ቢያድር ኖሮ”ይባል ነበር፡፡

ብዙ አባዎራዎች ለእናታገራቸው ሰላምና ደህንነት ሲሉ ከሚስታቸው እቅፍ ተለይተው እንቅልፋቸውንና ምቾታቸውን ሲሰው ያድራሉ ብለን እናደንቃቸው ነበር፡፡

ዘግይቶም ቢሆን እንደተሸወድን ገብቶናል፡፡ አንዳንዱ አባዎራ ሮንድ አድራለሁ በሚል ሰበብ ቅምጡን አላስቀምጥ ሲል ያድር ነበር፡፡ በሮንድ ሰበብ ከቤት ለቤት እየተዘዋወረ ግብረስጋ ሲያደርግ የሚያደር ሮንድ በህዝብ ዘንድ በጅ-ሮንድ የሚል ማእረግ ይቀዳጃል፡፡

የሆነ ጊዜ ላይ በመንቆረር ከተማ፤ አንድ ሰውየ ሮንድ ለማደር ከዘራውንና ሦስት ጎራሽ ባትሪውን ታጥቆ ወጣ፡፡ ሚስትዮዋም ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ በመጠቀም፤ ከጎረቤት የሚኖረውን ውሽማዋን ሰበር ግብዣ አደረገችለት፡፡ በሽቶ ሳሙና ተጣጥባ ሦስት ማእዘኗን ተለጫጭታ ጠበቀችው፡፡

ውሽምየውም መጥቶ፤ በዱባ ወጥ ራቱን በልቶ፤ ዙርያ ገባውን እየተመለከተ ቀጥሎ የሚያደርገውን በማሰብ ተጠመደ፡፡

መጀመርያ፤ጭድ ፍራሹ ላይ የእንግላል አደርጋለሁ ፤ቀጥየ አጎዛ የለበሰውን ሳንዱቅ አስደግፌ ጫንቃ- ሰበር አስከትላለሁ ፤ቀጥየ ብሎ ሳይቀጥል የኮቴ ድምጽ ከደጃፉ ግድም ተሰማ፡፡ ባልየው ብርዱ ጸንቶበት መመለሱ ነው፡፡

ሚስትዮዋ በጣም ከመደንገጧ የተነሣ ውሽምየውን እንደፋሲካ ዶሮ ቅርጫት ደፍታበት ቁጭ አለችበት፡፡ከዚያም ከፊቷ ያለውን እሳት መሞቅ ጀመረች፡፡

ባልየው ገብቶ ፤ በሚስቱና በምድጃው ፊትለፊት ተጎልቶ፤ በእግሮቿ ማህል አሻግሮ እየተመለከተ ስሜት በተጫነው ወፍራም ድምጽ “ ዛሬ ይሄንን መላጣ ስመልጠው ነው የማድር” በማለት አጉተመተመ፡፡

ቅርጫቱ ውስጥ ያደፈጠው ውሽምየ፤ ባጋጣሚ መላጣ ስለነበር፤ ዛቻው የተሰነዘረው ለርሱ መስሎት ቅርጫቱን ከነሴትዮዋ ገልብጦ ተፈተለከ፡፡ እና አሁን ይሄ ምን ለማስተላለፍ ነው?ሠኣት እላፊ ፤ዜጎች እላፊ ብልት እንዲለምዱ ከማድረግ ያለፈ አስተዋጽኦ አይኖረውም ለማለት ነው፡፡

በመጨረሻ ብዙ አንባቢዎቼ ፤ ከኮማንድ ፖስቱ በኋላ ፤ ምኡዝ ምን ሁኔታ ላይ እንዳለ እንድገልጽላችሁ ጠይቃችሁኝ ነበር፡፡

በቀደም ለታ ምኡዝና ሚስቱ ሄለን፤ በረከቦት ጎዳና ወክ ሲያደርጉ መታጠፍያው ላይ የሆነ ፖሊስ ቆሟል፡፡ ምኡዝ ፖሊሱን ሲያይ መንገድ ቀይሮ ለመሄድ ቃጣ፡፡ ፖሊሱ ትንሽ ጥርጣሬ ስለገባው ምኡዝን አስቁሞ መፈተሽ ጀመረ ፡፡

ሄለን “ ባለቤቴ ከማንም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ግኑኝነት የለውም፡፡ ሺህ ጊዜ ብትፈትሹት ምንም ነገር አታገኙም“ አለች በግብዳ ልበሙሉነት፡፡ ፖሊሱ ከምኡዝ ኪስ ውስጥ ሁለት ፓኮ ኮንደም እየጎለጎለ ሲያወጣ ስታይ ግን አይኗን ማመን አልቻለችም፡፡

“ አንት ሸሌ!አሁንም በኔ ላይ “እያለች የምኡዝን ፊት በጥፍሯ ግልገል ዝንጀሮ የላጠው ቀይሥር አስመሰለችው፡፡ ፖሊሱ እየሳቀ ትንሽ ከገላገለ በኋላ መንገዱን ሊቀጥል ሲል ምኡዝ እየሮጠ ደረሰበት፡፡

ፖሊሱ “ ምን ፈለግህ?” ሲለው ምኡዝ አንጀት በሚበላ ድምጽ ” በዚህ አይነት ሁኔታ ወደ ቤቴ እንድመለስ ከምትፈርድብኝ፤ አንድ ሳምንት በማሠር ለምን አትተባበረኝም ?ብሎ እጁን አመሳቅሎ የተቃውሞ ምልክት አሳየ፡፡

Filed in: Amharic