>

ለማና አብይ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው በሒደትም የሕዝብ ጥያቄ ሊመልሱ ይችላሉ" (ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ)

አቶ ለማ መገርሳ በሁላችንም ልብ ውስጥ ያሉ መሪ ናቸው። ዶክተር አብይ አህመድም የለውጥ ሰው ናቸው ያሉት ጄኔራሉ ሁለቱ መሪዎች የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው ሲሉ ለሁለቱም ያላቸውን ድጋፍና አክብሮት ገልጸዋል። በሐገር መከላከያ ሚኒስቴር የምህንድስና መምሪያ ሃላፊ የነበሩትና በአሁኑ ወቅት በጡረታ ላይ የሚገኙት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ከኦ ቢ ኤን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ አቶ ለማ መገርሳና ዶክተር አብይ አህመድ የኦሮሚያ ሕዝብ ትግል ውጤት መሆናቸውን ገልጸዋል። ሕዝባዊ አክብሮት ያገኙ መሪዎች ሆነው መውጣታቸውንም መስክረዋል። በቅርቡ የተደረገውን የአመራር ሽግሽግ በተመለከተም በሀገራችን ታሪክ ያልታየ ነው ያሉት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ አቶ ለማ ለጠቅላይ ሚኒስትርነት ተወዳደሩ ሲባሉ መድረኩን ለዶክተር አብይ በመልቀቅ ከድርጅት ሊቀመንበርነት መነሳታቸውን አወድሰዋል። አቶ ለማ መገርሳ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ ትልቅ ክብር ማግኘታቸውንም ገልጸዋል። እንዲህ ያለ ሰው ለሀገራችን ያስፈልጋል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። “ዶክተር አብይ ጥሩ አንባቢ ነው።በጥልቅ ለማወቅ የሚፈልግና በጥልቀትም የሚያውቅ ሰው ነው።” በማለት ለዶክተር አብይ አህመድ ምስክርነት የሰጡት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ “አብይ የለውጥ ሰው ነው” ሲሉም አክለዋል። ለማና አብይ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፣ሁለቱም ግዜ ሊሰጣቸው ይገባል፣በሒደትም የሕዝብ ጥያቄ ሊመልሱ ይችላሉ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
Filed in: Amharic