>

ግልፅ ደብዳቤ ለጃዋር መሀመድ (ከፍቅሩ ቶሎሳ) 

ሰላምታዬ ባለህበት ይድረስህ፡
ለአመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንዳንዴ እንደ አክቲቪስት፣ አንዳንዴም እንደ ፖለቲካ ተንታኝ፣ አልፎ አልፎም የሚስጥራዊ መረጃዎች ምንጭ በመሆን ዋነኛ ተሳታፊ ሆነህ ቆይተኻል፡፡ የግል ጊዜ የሌለህ እስከማይሰመስል ድረስ ሌት ተቀን ስትተጋ ነበር፡፡ የልፋትህ ውጤቱ ምንም ይሁን ምን ትጋትህ ሳይደነቅ አያልፍም፡፡ ውጤት ላይ ስንመጣ ግን አንድ ወሳኝ ጥያቄ ይነሳብሃል… እኔም እሱን መሰረት አድርጌ ይሄንን ደብዳቤ ፅፌልሃለሁ፡፡
የአገራችን ፖለቲካ እንደተከታታይ ፊልም ማብቂያ አጥቶ ለብዙዎቻችን በተስፋና ቀቢፀ-ተስፋ መካከል እንድንሰቃይ አድርጎናል፡፡ ይሄም የተሻለ ነው እንድንል የሚደርጉን ሁኔታዎችም ተፈጥረዋል፡፡ ትግሉ በተደረጀና ስልታዊ በሆነ መንገድ ባለመመራቱ ምክንያት ምስኪን ህዝብ እያለቀ ነው፡፡ ይሄን ደግሞ የፈጠረው የግለሰቦች ግትርነት እንደሆነ ሲታሰብ አንጀት ያደብናል፡፡ የወያኔ እብሪትና ግትርነት ማረጋገጫ የማያሻው ፀሀይ የሞቀ እውነት ነው፡፡ ስለዚህ ስለእነሱ እብሪት በማውራት ጊዜዬን አልገድልም፡፡ የእነሱ ግትርነት፣ የእነሱ እብሪት ብዙ ሰዎች ላይ እየተጋባ ሄዷል፡፡ ለዚህ ምስኪን ህዝብ ማለቅ መንስኤ ከሆኑት ግትሮች መካከል አንተም አንዱ ነህ፡፡ እንዴት ማለት ጥሩ….
ባለፉት ሁለት አመታት በኦሮሚያ ክልል አንፃራዊ ለውጥ ታይቶ ብዙዎቻችን ተደስተናል፡፡ እንደምታውቀው ጭቆናን ለማጥፋት “መቃወም” እና ጭቆናን ለማጥፋት “መልካም ለውጦችን ማምጣት” ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ ተቃውሞ በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡ ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ ፈልገህ ከሚጨቆነው ህዝብ ጫንቃ ላይ የመከራን ቀንበር ማንሳቱ ግን ብልህነትን ይጠይቃል፡፡
ኦሮሚያ፣ ስር የሰደዱ ችግሮች፣ የጭቆና ኔትዎርኮች የተስፋፉበት ክልል ነው፡፡ ለዘመናት የተገነባው ይሄንን የተበላሸ ስርዓት ለመበጣጠስ ዘመናትን እንደሚፈልግ ግልፅ ነው፡፡ በኢንቨስትመንት ላይ ያለው ብቻ ብታነሳ ምን ያህል ቆሻሻ እንደነበረና ይሄንን ለማስወገድ ምን ያህል ብልህነት እንደሚጠይቅ እንኳን መተግበሩ መገመቱም ይከብዳል፡፡ የለማ ቡድን ግን በአንድ አመት ውስጥ እውን አድርጎታል፡፡ ታዲያ፣ አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው እንዳይመስልህ፣ ከዱርዬ ስርዓት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቀው፣ ግንባራቸውን ለጥይት አጋልጠው እንደሆነ ስታስብ ከዳር ቆሞ መቃወመ ተራ ይሆንብሃል፡፡
ህዝብን “አድሙ፣ መንገድ ዝጉ፣ አቃጥሉ፣ ጥይት ከያዘ ስርዓት ጋር በቡጢ ተጋጠሙ” ማለት ብልህነት አይደለም፡፡ ለእኔ ብልህነት፣ እንደ መሪ ለተጎሳቆለ ህዝብ የሚታይ መልካም ለውጦችን (positive change) ማምጣት፣ በተራዛሚውም ሳይፈሩ በተሻለ ብልጠት ስርዓቱን ፊት ለፊት መጋፈጥና እንዳያንሰራራ አድርጎ ማስወገድ ነው፡፡ መጀመሪያ ሰሞን አንተም ይሄንን አካሄድ እንደምትደግፍ አሳይተህ ነበር፡፡ የሚታዩ ለውጦች ሲመጡ፣ ወያኔም መፍረክረክ ሲጀመር፣ የለማ ቡድን ባሳየው ብለህ አካሄድ ህዝቡም እምነቱን ማሳደር ሲጀምር ድንገት ስሜታዊ የሆንክበት ምክንያት ሊገባኝ አልቻለም፡፡
መቼስ የፖለቲካ ትግል በእውቀት እንጂ በስሜታዊነት መመራቱ ህዝብን እንደሚያስጨርስ ጠፍቶህ አይመስለኝም፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚል የጅምላ መጨፍጨፊያ ህዝብ ላይ ካወጁት ወያኔዎች ባልተናነሰ፣ ወጣቱን በጥይት ለማስጨረስ “ይሄንን ተቃውማችሁ ውጡ” ብለህ የጠራኸው አንተ ጥፋተኛ ነህ፡፡ ይሄ ብልህነት አይደለም…
ከአክቲቪስቶች አንዱ የተናገረው ነገር የበለጠ ገዥ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ እንዲህ ይላል…
“ትግሉ በእውቀት፣ በስሌትና በድርጅት እንጂ በስሜት የሚመራ መሆን የለበትም። ትግሉ መንገድ ላይ ወጥቶ ከመሞት የጀብደኝናት ስነልቦና መውጣት አለበት። በጠላት ላይ የኢኮኖሚ፣ የፓለቲካና የስነልቦና ኪሳራና ጉዳት ማድረስ እና ወገንን ከጥቃትና ከሞት መከላከልና ህዝባችንን ለድል ማብቃት የሚወጡት ህዝባዊ የትግል ስልቶች ሁሉ ግንባር ቀደም ተልዕኮና አለማ መሆን አለባቸው።”
አየህ፣ ለህዝብ ስታስብ ትግልን እንኳ በእውቀትና በብልሃት እንጂ በእብሪትና በግትርነት አታካሂድም፡፡ በነገራችን ላይ ባለፈው በጠራኸው የሶስት ቀን የገበያ አድማ የተጠቀመው ማንም አይደለም… ወያኔ ብቻ ነው፡፡ የኦሮሚያ ልጆች ግን ሞተዋል፡፡ እነ ኦቦ በቀለ ገርባና የመሳሰሉት መፈታታቸው ትርፍ ነው እንዳትለኝ ብቻ… ወያኔ የፖለቲካ እስረኞችን እንዲፈታ እጁን ተጠምዝዞ ባለበት ሰዓት ነው 3 ቀን አድማ የተጠራው፡፡ 9 ሰው ሞቶ መፈታታቸውን እነሱም የሚወዱት አይመስለኝም፡፡ አንተ አሁን በስሜታዊነት ለወያኔ እየተመቻቸህለት ነው፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞ መቼም መሪ እንዳይኖረው ማድረግ ነው አላማቸው፣ ያ እንዲሳካ በለማ ቡድን ላይ ህዝብ ጀርባውን እንዲሰጥ እያነሳሳህ ስለሆነ፡፡ እነኦቦ ለማ መገርሳና ዶ/ር አብይ አህመድ ትግሉን በእውቀትና በብልሃት እየመሩት ወያኔ ላይ የፖለቲካ ኪሳራ ከማድረስ በዘለለ እንዲያ የሚተማመንበትንና ህዝብ የሚጨቁንበትን ስልጣን በክልል አሳጥተው ከፌደራልም ሊነጥቁት በተዘጋጁበት ሰዓት ውሃ እየቸለስክበት እንደሆነ ወይ አልገባህም አለበለዚያም እንዲገባህ አልፈለግክም፡፡ ይሄ አንድ ነገር ይጠቁማል፣ እቆረቆርለታለሁ ላልከው የኦሮሚያ ህዝብ ከልብህ የምትቆረቆርለት አይመስለኝም፡፡ የኦሮሚያ ጥቅም ከተረጋገጠ እኔ ትኩረት አጣላሁ የሚል ከፍተኛ ፍራቻ ውስጥ ወድቀሃል፡፡ አንተ ትኩረት ማጣትህን ስትፈራ ህዝብ ግን አይተኬ ህይወቱን እያጣነ ነው፡፡ ከቻልክ የመልካም ለውጥ አቀንቃኝ ከሆነው #teamLema ጋር ቁም፣ ካልሆነ ግን ከመንገዳቸው ገለል በል፡፡ ልክ እንደጎርፍ ወያኔ ባሰመረልህ ቦይ አትፍሰስ፡፡ እንደነለማ መገርሳና አብይ አህመድ ወንዝ መሆን ይበጃል፡፡
ሌላው፣ ዶ/ር አብይ ፓርላማ አለመገኘቱን እንደ ትችት ስታቀርበው ነበር፡፡ ይሄ ስህተት ነው፡፡ ለተበላ እቁብ መፍትሄው እጅ ማውጣት ወይም አለማውጣት እንዳልሆነ ልብህ ያውቀዋል፡፡ አብይ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የህዝብ ተወካዮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚፀድቅበት እለት ፓርላማ ባለመገኘት ቢቃወሙት ይሻል ነበር፡፡
Filed in: Amharic