>
5:13 pm - Friday April 19, 8374

ብአዴንን ያመነ ጉም የዘገነ. . .  (አቻምየለህ ታምሩ)

ትናንት ወይንም ታሪክ ሁልጊዜ  ጠባሳውን ወይንም አሻራውን ትቶ ያልፋል። ስለሆነም ትናንት የዛሬን ቁልፍ ይዟልና ተመልሶ መጪ መሆኑ   መዘንጋት የለበትም።  የትናንት ታሪክ ዛሬ ላይ የሚያሳድረው ጠባናሳ አሻራ ብአዴን የሚባለውን የወያኔ ፍጡርም ይጨምራል። ብአዴን የፋሽስት ወያኔ  ነውረኛ ድርጅት እንጂ የአማራ ሕዝብ አካል አይደለም። ብአዴን ኢሕአዴግ የሚባለው  የማታለያ ጭንብል የጠራውን  አውጫጭኝ ረግጦ ቢወጣ እንኳ  ረግጦ ሊወጣ የሚችለው  የአማራ ሕዝብ ተበደለ ብሎ ሳይሆን ፋሽስት ወያኔዎች  አከርካሪውን ሰብረን ትክሻውን ለእስክስታ ብቻ አስቀርተን ገድለን ቀብረነዋል ያሉት አማራ ተነስቶ  ሕወሓትን መጋተር በመጀመሩ  የተነሳ ሳይከለስ፣ ሳይበረዝ ለሃምሳ አመታት እናስቀጥለዋለን ያሉት የመለስ ሌጋሲ አደጋ ላይ በመውደቁ ነው።
ከኤርትራዊው በረከት ቀጥሎ  የብአዴን የማዕከላዊ ኮምቴ አባል የሆነው ብናልፍ አንዷለም «ነጻ ያወጡን ሕወሓቶች አይደለም ወልቃይትና ጠገዴን ጎጃም ደጋ ዳሞትን እንኳ ቢወስዱ ሲያንሳቸው ነው» ሲል የተናገረ ጉድ ነው። ሌላው የማዕከላዊ ኮምቴ አባል አለምነው መኮነን «ሕወሓት በሕዝባዊ አመጽም ሆነ ሆነ በትጥቅ ትግል  ከስልጣኑ ቢወገድ፤ ሕወሓትን መልሼ  ወደ ሥልጣን ለማምጣት አብሬያቸው ደደቢት እንደገና እወርዳለሁ» የሚል ወደር የማይገኝለት ባንዳ ነው።   Nigussu Tilahun የሚባለውን የብአዴን ቃል አቀባይ ማንነትም  በዘረኛ ትግሬዎች የሚረግፉት አማሮችን  ሞት ሟቾቹን ራሳቸውን  ተጠያቂ  በማድረግ  ሲከስ  የሚውል ሕሊና ቢስ እንደሆነ  እዚህ ፌስቡክ ላይ ሲለጥፍ የሚውለውን  የአማራ ክልል ተብዬውን  መግለጫ  የምናየው ነው።
ላለፉት ሀያ ስድስት  አመታት ፋሽስት ወያኔ  በአማራ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለው ግፍ የሚያንገበግባቸው፤ ብአዴንንም   የአማራ ሕዝብ አካል የሆነ መስሏቸው የተቀላቀሉት  ወጣትቶች፤   ጉርፋርዳ እና ቤንሻንጉል አገራችሁ አይደለም ተብለው አማሮች ከኖሩበት ቀየ ተፈናቀለው ሜዳ ላይ የመውደቃቸው ድርጊት የእግር እሳት ሁኖ የሚለበልባቸው ብዙ ልጆች ነበሩ። በዚህ ሁኔታ ያዘኑና የተቆጡት ወጣቶች «ድርጅታችን ብአዴን» ቆሜለታለው የሚለው ፍትህ የት አለ?  እኩልነትስ ከወዴት አለ?  ኢትዮጵያስ የሁላችን አገር ነች የምትባለው መገለጫው ምንድ ነው?  እያሉ የብአዴንን ስራ አስፈጻሚ ሞግተው ነበር።
ሆኖም ግን እነዚህ የሕዝብ ጥያቄዎች በወጣቶቹ  ህሊና  መካከል መመላለስ ሲጀምሩ «ብአዴን ተዳክሟል» ተብሎ ግምገማ እንዲያካሂድ በወያኔ ትዕዛዝ  ተላለፈለት።  እነአለምነው መኮነን «በባዶ እግርህ የምትሄድ ድሀ፣ ልጋጋም፣ ሰንፋጭ ንግግር የምትተፋ፣ ወዘተ» ብሎ ሕዝቡ ላይ የተሳለቁበት በወጣት የብአዴን አባላት መካከል የህዝቡ ችግር በመነሳቱ «ብአዴን ተዳክሟልና ግምገማ ያስፈልገዋል» ብሎ ወያኔ ባዘዘው መሰረት በተጠራው ጉባኤ ላይ ነበር። ልብ በሉ! የአማራ ጉዳይ በብአዴን ዘንድ የውይይት አጀንዳ ሆኖ ሲቀርብ በሕወሓት ዘንድ ብአዴን እንደተዳከመ ይቆጠራል። የአማራ ችግር በመነሳቱ «ብአዴን ተዳክሟል» ተብሎ በተጠራው ጉባኤም   የአማራን ጉዳይ ያነሱ ወጣት የብአዴን አባላት  ትምክህተኞችና የድሮ ስርዓት ናፋቂዎች  ተብለው በነአለምነው  ውርጅብኝ  ዘነበባቸው።
ኦሕዴድ የወያኔ ፍጡርም ቢሆን «የኦሮሞ ሕዝብ ፍላጎት» በሚል በኦነግ የሚያቀነቀነውን ፕሮግራም  የሚያስፈጽም ድርጅት ነው። ኦሕዴድ እግር አውጥቶ ኢሕአዴግ የሚባለው  የማታለያ ጭንብል የጠራውን  አውጫጭኝ ረግጦ ቢወጣ ፋሽስት ወያኔ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን ጭፍጨፋ ተቃውሞ ነው። ኦሕዴድ ከኦሮሞ ሕዝብ ጎን መቆሙ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም። ኦሕዴድ የሚሸወደው   ብአዴንን የአማራ  ድርጅት አድርጎ   ከጎኔ ቆሟል ብሎ ያሰበ እለት ነው። እያየነው እንዳለው ኦሕዴድ ብአዴንን አጋር  አድርጎ እየቆጠረ ይመስላል። ብአዴን ከኦሕዴድ  ጋር ስብሰባ ረግጦ እስከመውጣትና አጋር መስሎ እስከመታየት ከደረሰ መስሎ ሊታይ  የሚችለው  ኦሕዴድን በሕወሓት ለማስበላት ብቻ ነው።  ኦህዴድ ብአዴን የሚባለው የወያኔ ነውረኛ ድርጅት  ኦሕዴድን ብቻ ሳይሆን ራሱንም  ክዶ ከሕወሓት ጋር የሚቆም ድርጅት እንደሆነ ያሰበበት አይመስልም።
ብአዴንኮ  በሕወሓት ተሰርቶ ብአዴን የሆነው   የአማራ ነስፍ  አድን ድርጅት  መአሕድ  በእጀ መድሃኒቱ ሐኪም በፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ሲያቋቁም  ከመአሕድ የዐማራውን ውክልና ለመጫረት ተፈልኮ  የስም ሕብረ ብሔራዊ ድርጀት የነበረውን ኢሕዴን ክዶ ከሕወሓት ጎን ለመቆም ሲባል ነው። ባጭሩ ብአዴን ብአዴን  የሆነው የአማራን ሕዝብ ለመታደግ ሳይሆን ሕወሓት የታገለለትን አማራን የማጥፋት ፕሮግራም  ወያኔ እንዳሻው ለማስፈጸም እንቅፋት የሚሆንበትን ለአማራ የሚቆረቆረ ድርጅት [መአሕድን] ውጦ ለማጥፋትና አማራን የማጥፋት ፕሮግራሙን «በአማራ» ስም በቀጥታ፣ በስውርና በዘዴ የሚያስፈጽምለት ድርጅት ስላስፈለገ ነው።
 ብአዴን  በሕወሓት ከመሰራቱ በፊት የነበረውን  ኢሕዴንንም ብናይ  ታሪኩ አንድ አይነት ነው። ኢሕዴን በሻዕብያና በወያኔ አዋላጅነት  ትግራይ ውስጥ የተመሰረተው ኢሕአፓን ከድተው ወደ ሕወሓት በገቡ ፋኖዎች ነው። የነእያሱ አለማየሁ ኢሕአፓ ኢሕዴኖችን  «ለወያኔ ያደሩ ከዳተኞች»  ሲል ይጠራቸዋል። የደርጅቱ መሪ የነበረው የዛሬው ፓስተር ታምራት ላይኔ የነእያሱ አለማየሁ  ኢሕአፓ በኢሕዴን ላይ ላቀረበው ነቀፌታ በድርጅቱ ልሳን በማለዳ መጽሔት አስተያየት ሲሰጥ «እኛ ከኢሕአፓ ተለይተን የወጣን ትክክለኛ ኢሕአፓዎች ነን» ብሎ ነበር።  በርግጥ  የፓስተር ታምራት  ላይኔ አባባል ተስፋየ መኮንን «ይድረስ ለባለታሪኩ» በሚለው መጽሐፉ ከፋጸው ታሪክ አኳያ ውሃ የሚቋጥር  እውነት ነው።
የብአዴን ጉድ ተዘርዝሮ አያልቅም። መቶ አለቃ ማሞ አስማረ የሚባል  የአርማጭሆ አማራ በሕዝብ ላይ አንተኩስም በማለቱ ነውረኛው ብአዴን በሕዳር 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ መቶ አለቃውን  ከስራና ከሃላፊነት አንስቶታል።  Muluken Tesfaw የለጠፈው ብአዴን ለመቶ አለቃው የጻፈው የእግድ ደብዳቤ ከታች ታትሟል።  ለብአዴን አማራን አለመግደል የሕወሓትን ግዳጅ አለመወጣት ነው።  ባጭሩ ብአዴን የትግሬ ተወካይ፣ የሆዳምና  ህሊና የሌላቸው ሎሌዎች ቡድንና የሕወሓት ነውረኛ ድርጅት ነው።  ብአዴን  የሚባለውን የፋሽስት ወያኔ ነውረኛ ድርጅት ከአፈጣጠር  ጀምሮ እስካሁን ጀምሮ  ሲኖር ያጠለቀውን የወያኔ ለምዱን አዉልቀን እርቃኑ አስቀርተን ስናየው ከላይ የቀረበውን አይነት ነውረኛ ፍጡር ይመስላል።
Filed in: Amharic