>

- አሜሪካና ሩሲያ ሊመክሩን÷ እየመከሩልን ወይስ እየመከሩብን?… (ዶ/ዴንሳ አያኖ)

– አሜሪካና ሩሲያ ሊመክሩን÷ እየመከሩልን ወይስ እየመከሩብን?… ይልቅ እኛው አገራችንን እንታደግ።
 – “የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ውስጥ የሽግግር መንግስት ይቋቋም ብለዋል! (ማክሰኞ የካቲት 27, 2010)
ታላቅ ዲፕሎማሲያዊ ድል!
ዶ/ዴንሳ አያኖ
የህዝባችን ትግል ማሸነፉን ያመነችው አሜሪካ የፖሊሲ አቋም ወስዳለች። በአሜሪካን ድጋፍ ተንጠልጥላ የኖረችው ወያኔ ቅርቃር ውስጥ ገብታለች።
ከአንድ ሳምንት በፊት በአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ መምሪያው ትልቁ ባለስልጣን የሆኑት ዶናልድ ያማሞቶ የወያኔ ባለስልጣናትን አስጠርተው በአናሳ ቡድን የሚመራው የህወሃት መንግስት በዚሁ ሊቀጥል አይችልም የሽግግር ስርአት መደረግ አለበት ብለዉ ነበር።የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ሬክስ ቲለርሰን ዛሬ ማክሰኞ ወደ አፍሪካ እንደሚያቀኑ መስሪያቤታቸው አሳውቋል።”
Look at BBC Amharic : “የአሜሪካን ባለሥልጣናት እንዳሉት ቲለርሰን ከኢትዮጵያ መሪዎች ጋር ስለሽግግር ሂደትና በበርካታ የሃገሪቱ ክፍሎች ስለተስተዋሉት ግጭቶች አንስተው ይወያያሉ።”
አሜሪካና ሩሲያ ሊመክሩን÷ እየመከሩልን ወይስ እየመከሩብን?… ይልቅ እኛው አገራችንን እንታደግ።
እውነቱን የሚያውቀው አንድዬ ብቻ ነው። አሜሪካና ሩሲያ ግን ተስማምተው እንደአገር ያቆሙት አገር አለ? የምታውቁ ካላችሁ ንገሩኝ። በዚህ በኖርኩበት እድሜ ስለነዚህ ሁለት ታላላቅ አገሮች ፉክክርና ደባ÷ አንዱ ሌላውን (የሌላውንም ወዳጅ ጭምር) የማጥፋት ሴራ ሲሸርቡ እንጂ ተማክረው ሲታደጉ ያየሁት አገር ትዝ አይለኝም።
እውነት ለመናገር እነርሱ በጋራም ሆነ በተናጥል ተከታትለው የገቡበት ሁሉ ሲጠፋፋ ነው የሚታየው። ዩጎዝላቪያ ዛሬ አምስት ትንንሽ ሆናለች። ሶማሊያ ሦስት ከግማሽ ሆና ወይ አትቀዘቅዝ ወይ አትቃጠል እኛንም ወላፈኑ እየገረፈን ነው።  ኢራቅ÷ አፍጋኒስታን÷ ሊብያና የመን የማይጠፋ እሳት ላይ ተጥደዋል። ሶሪያን ላስተዋለ ገሀነምን በምድር ማየት ነው። እስቲ አስቡት! አሜሪካና እንግሊዝን ያህል መሰሪና ታላላቅ ሀገሮች አንድ የማይታመን አልባሌ ድንጋይ ግቢያቸው አስቀምጣ መረጃ ምትሰበስብና ውስጣቸውን ዘርግፋ ምታውቅ ሀገር÷  ሊቢያን ለማጥፋት እንደታሰበ ሳታውቅ ቀርታ በተባበሩት መንግስታት ስም ሲያስወስኑ ድምፅን በድምፅ መሻር ትታ አሳልፋ ያስጨረሰቻቸው ሩሲያ አይደለች? ሶሪያ ስትደበደብ ንጉሷን የታደገችው ሩሲያ ለኢራንና ለሶሪያ መሳሪያ ሸጣ ብር እንዳፈሰች አሜሪካም በአንፃሩ  “ሩሲያ መጣችባችሁ!” እያለች ከቱርክ÷ ከሳውዲና ከኢራቅ ደህና ገምጣለች።
አሜሪካ ያላፈረሰችው÷ ሲያሻት ደግሞ ያልሻረችውና ያልሾመችው አገር ብዙ አይገኝም። ተቀናቃኟን ሶቭየት ህብረትን ሳይቀር አስራ አራት ትናንሽ አድርጋ እርሷ ግን 53ቱን አጣምራ ታላቅነቷን ትገነባለች። ሱዳን ወደሁለት መከፈል ሳያንሳት ሶስተኛውን እያስታመመች ሲሆን በሽታዋ ወደኛም እየነፈሰ ገልምጦናል። በህዝባቸው ጥንካሬና በነበራቸው የተሻለ ስነልቦና እንደሀገር ቆመው ግን ውስጣቸው እንደካንሰር እየተበላ ያሉት ግብፅና ዩክሬንም የነዚህ ሁለት ባላንጣዎች ፉክክር ውጤቶች ናቸው።
ስንቱ ይወራል? አንዳንዶች ባኮረፉ ቁጥር መከፋፈልና እያነሱ መሄድ ትልቅ መፍትሄ ይመስላቸዋል። እድሜ ለአሜሪካና ሩሲያ ኮሪያዎች አንድ ህዝብ ሆነው እያለ  ተከፋፍለው ዛሬ ከነርሱ አልፈው ዓለምን እንዳያጫርሱ በቋፍ ናቸው።  እነኮንጎ ተሰንጥቀው የወንበዴ ዋሻ ከመሆን አላረፉም። ከእኛ የተገነጠለችው ኤርትራ ሲንጋፖር እንደምትሆን ሲጠበቅ ህልምና ቅዠት ሆኖ ቀርቷል። ይህንን ነው ምትፈልጉት? እስካሁን እንዳየነው ተከፋፍለው ካነሱት ይልቅ ሲጣመሩ ታላቅነታቸውን ያደራጁት እንደሚበልጡ ነው።
እስቲ ንገሩኝ አሜሪካና ሩሲያ አገሮችን አጣልተውና አፋጅተው ከዚያ ለማትረፍ÷ መሳሪያ ለመሸጥና ለማጨፋጨፍ እንጂ ሌላ ለምን ይደክማሉ? አንዳንዱ ሰው “ኢትዮጵያ ስትራቴጂክ ቦታ ላይ ስላለች÷ ሽብርተኝነት እንዳይስፋፋ÷…  ” የሚል አይነት ትንታኔ እያቀረበ ቆርፋዳ ወሬ ያወራል። ሽብርተኛ ማነው? አሜሪካ አይደለችምን? በሰላም የሚኖረውን የሊብያን ህዝብ ተከፋፍሎ እንዲፋጅ÷ ሀገር ያለመሪ እንዲቀርና ስርዓት አልበኝነት ሰፍኖ ግድያ እንዲስፋፋ ማን ወጠነው? ወገኖቻችን ሲታረዱ÷ በባርነት ሲጋዙና ሲሸጡ÷ በባህር ሲጣሉና በምድረ በዳ የደረሱበት ሲጠፋ ማን ደረሰላቸው? አይሲስ የማን ስሪት ነው? የሚጠቀመው መሳሪያ የአሜሪካ እርዳታ÷ ስልጠናውና ቀለቡ ከዚችው መሰሪ አገር አይደለምን? በኢራቅና በሶሪያ ያለቀው ህዝበ በማን ዳፋ ነው? በአሜሪካና ሩሲያ መሳሪያና አልጠግብ ባይነት አይደለምን?
አሁን ወደመጨረሻው የተጠጋን ይመስለኛል። ኢትዮጵያን እግዚአብሔር ይታደጋት። ወይ ሊያጫርሱን አሊያም አምስት ትንንሽ ሊያደርጉን እንጂ እነዚህ የሽብር አባቶች ያለምክንያት እየጎበኙን አይመስለኝም። አንድ ነገር ግን አምናለሁ። ተስፋ የማደርገውም እርሱን ስለሆነ በዚያ ልቋጨው። እግዚአብሔርን ከቀረብነው አይጥለንም።
ኢትዮጵያ እንደሌላው አገር አይደለችም። የህዝቡ ጨዋነትና አርቆ አሳቢነት÷ በእግዚአብሔርም ቃል ባላት ተስፋ የተነሳ እንቀጣለን እንጂ እንደማንጠፋ አምናለሁ። ኢትዮጵያውያን አገዛዞች ባይመቿቸው እንኳን ብዙ ነገር በትእግስትና በመቻቻል ያሳለፉ ሰዎች ናቸው። አሁንም ከጨለማው ወዲያ ያለውን የተስፋ ጭላንጭል እያየን÷ አሁንም በአብሮነታችን ይህን ክፉ ጊዜ እንደምናሳልፍ እርግጠኛ እንሁን።
ራስ ወዳድነትና እልህን ገሸሽ በማድረግ መነጋገርና መደማመጥ ለየትኛውም ችግር መፍትሄ ያመጣል ብዬ አምናለሁ። በብዙ ምክንያት መንግስት አልባ ሆነን ስርዓት እንዳይጠፋ ኢህአዴግ የሌለበትን ሽግግር እንደማያዋጣን ደጋግሜ ፅፌአለሁ። “ህዝብን እሰማለሁ÷ የምታገለው ለህዝብ ነው” የሚል መንግስት ጆሮው የሌባ ጣቱ ላይ የተሰራ እስኪመስል “ግፉ በዛብን” ላለው ሁሉ መሳሪያ መወልወል ሲያበዛ ግን ምን ይሉታል? ሰው እንዴት “በመረጠው” ህዝብ ላይ ሞት ይደግሳል? መተዛዘንና “አንተ ከኔ ትብሱ” ቢቀር መከባበርና መደማመጥ ማንን ገደለ? ይህን እልኸኛ ትውልድ÷ ጣቱን በመቀሰር እንጂ እጁን በመዘርጋት እንዳይታወቅ ለምን ፈረድንበት?
ምን ብዬ እንደምመክር ቃላት አጣሁ። ማንም ከውጭ ቢንጫጫም የሚታገለውም ሆነ የሚያልቀው እዛው ያለው የፈረደበት ህዝብ ነው።  ሁኔታዎችን ለመለወጥ ቁልፉ ግን  አሁንም በኢትዮጵያ መሪዎች እጅ ነው። ኢህአዴግ አሁንም ትልቅ እድል አለው። የእነዚህ ሁለት ታላላቅ አገሮችን ምክር ሲሰማ ሀሳባቸው ውሎ አድሮም ሀገርን የሚያጠፋ ከሆነ እንዳይቀበል እጠይቃለሁ። ከሁሉ የሚሻለን÷ ይበጀኛል ያለውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሹሞ ወደ ተግባር ቶሎ ቢገባ ነው (ኦሮሞ ሆነ ትግሬ÷ ወይም ከየትኛውም አንጃዎቹ በኢህአዴግ ስም እስከተሾመ ለኔ ለውጥ ስለሌለው ነው÷ ተጨባጩን ሁኔታ ካየን ተሿሚው ማንም ይሁን ከፓርቲው ዓላማ ውጪ ተኣምርም አይፈጥርም )። ከዚያ ይመለከተናል የሚሉትን ሁሉ ጉባኤ ይጥራና እርቅ ያውርድ። እኛም አብረን የሁላችንንም አገር የሆነችውን ኢትዮጵያን የማዳን ስራ እንስራ። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃት።
ቸር እንሁን።
 (የካቲት 26÷ 2010 ዓ•ም)
Filed in: Amharic