>
5:14 pm - Saturday April 20, 5405

ህዋሃት እና የቀለም አብዮት ፍረጃው (አምራን ሚ)

“በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች የተፈጠረው አለመረጋጋት የቀለም አብዮት መልክ እየያዘ መሆኑን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ገለፀ” ፋና
የቀለም አብዮት (color revolution) የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ የተወለደው በ20ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ በፊልፒንስ ሲሆን የወቅቱ የሃገሪቱ አምባገነን መሪ የነበሩት ፕሬዝዳንት ፈርዲናድ ማርከስ ያሰፈኑት የጭቆና ስርአትን በመቃወም የተጀመረ ነበር። በወቅቱ ታላላቅ ሰላማዊ ሰልፎች፤ አድማዎች እና ተቃውሞች የተካሄዱ ሲሆን ፈላጭ ቆራጭ የነበረው ገዥው ፓርቲ በቢጫ ቀለም አብዮት ሳይወድ በግድ ከ21 አመታት አምባገነናዊ አገዛዝ በኋላ ሊወድቅ እና በፊሊፒንስ ዲሞክራሲያ ስርአት ሊመሰረት ችሏል።
ከፊልፒንስ በኋላ ወደ ምስራቅ አውሮፓ በተለይም በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት እና በባልካን ሃገሮች በተደረጉ ህዝባዊ አብዮቶች ላይ ዋነኛ መሳሪያ ሆኖ ሊያገለግል ችሏል። በዩጎዝላቪያ፤ ጂኦርጂያ (ሮዛማ አብዮት)፤ ዩክሬን (ብርቱካናማ)፤ ምስራቅ ጀርመን ፤ ፖርቱጋል እና በቤላሩስ እንዲሁም በአረቡ አለም አምባገነኖችን አውርዶ በዲሞክራቶች ተክቷል። የቀለም አብዮት ከሌሎች የትግል ስልቶች የሚለየው ያለ ምንም ደም መፋሰስ አምባገነናዊ ስርአትን በማንበርከክ ለዲሞክራሲ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ ነው። በህዝባዊ እምቢተኝነት፤ በሰላማዊ ሰልፍ፤ በአድማ እና የመንግስትን ስራ በማስተጓጎል የሚገለጽ ውጤታማ የሆነ ትግል ነው።
ህዋሃት ለባለፉት 3 አመታት የገጠመውን ህዝባዊ እና ሰላማዊ ተቃውሞ ነው እንግዲህ የቀለም አብዮት ብሎ የፈረጀው። ለነገሩ ይህ የመጀመሪያው ፍረጃ አይደለም። በ1997 አም በነበረው ታሪካዊ ምርጫ በቅንጅት እና ህብረት ሲዘረር ስልጣን ማስረከብ ባለመፈለጉ የፖለቲካ አመራሮችን ”የቀለም አብዮተኞ፤ የኢንተር ሃሞይ አራማጆች“ ሲል ፈርጆ ነበር። እንግዲህ ከ13 አመት በኋላ መሆኑ ነው ያንኑ የመለስ ዜናዊ ፍረጃ ዛሬ የደገመው።
እርግጥ ነው በኢትዮጵያ አብዮት እየተካሄደ ነው። ነገር ግን ህዋሃት እንደሚለው ”በነውጥ፣ በአቋራጭና በውጭ ሃይሎች ተፅዕኖ“ የተነሳ እየተካሄደ ያለ እምቢተኝነት ሳይሆን ህዝቡ ለ27 አመታት ያማረረው የዲሞክራሲ ፤ የእኩልነት፤ የፍትህ እና የነጻነት ጥያቄ መሆኑን መረዳት አለበት። ህዝቡ ያለምንም ማቋረጥ እየተቃወመ ያለውም ማንም ጎትጉቶት ሳይሆን ራሱን በራሱ አደራጅቶ ራሱ መስዋዕትነት እየከፈለ ነው! የህዝባዊ እምቢተኝነት ጥያቄም ህዋሃት እንደሚለው ”በግልጽ ስልጣን የመፈለግ አዝማሚያ“ ሳይሆን የአንድ ብሄር የበላይነት የሚያከትምበት እና ህዝቦች በእኩልነት እንዲሁም በነጻነት የሚኖሩበት ስርአት መገንባት ነው።
የሩስያ እና የቻይና አምባገነን ኮሙኒስት መሪዎች የቀለም አብዮትን አይወዱትም። ምክንያታቸው ደግሞ በቀለም አብዮቶች ጀርባ በዲሞክራሲ ስም የአሜሪካ እና የአውሮፓ ረጅም እጆች አሉ ብለው ስለሚያስቡ። ህዋሃትም ይህንን ህዝባዊ ተቃውሞ በቀለም አብዮትነት ለመፈረጅ ሰበብ ከሆኑ ምክንያቶች አንዱ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት በግድ የተጣለውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አምርረው ስለተቃወሙት መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው!
ለማንኛውም ከቀለም አብዮት ጋር ተያይዞ ፈገግ የሚያደርግ አንድ ነገር ላካፍል እና ላብቃ።
የቀለም አብዮት ከተካሄደባቸው ሃገሮች አንዷ ቤላሩስ ነች። ከ20 አመት በፊት የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበረው ቪክቶር ጎንቻር በመንግስት ሃይሎች ይታፈናል። አምባገነናዊ መንግስቱም የተቃዋሚ ፓርቲውን ቀይ እና ነጭ ባንዲራ በየትኛውም መድረክ እንዳይውለበለብ ያግዳል። በዚህ ድርጊት የተበሳጨው እና በወቅቱ ዙብር በሚባለው የወጣቶች ህዝባዊ ንቅናቄ አባል የሆነው ወጣቱ ሚኪታ ሳሲም የለበሰውን የጂንስ ቲሸርት አውልቆ ”ከዚህ በኋላ የእኛ ባንዲራ ይህ ነው“ በማለት በአደባባይ ይናገራል። ወሬውም በመላ ቤላሩስ ናኘ። በ2006 እኤአ ለተካሄደው እና ከ45ሺህ በላይ ተቃዋሚዎችን አደባባይ ያስወጣው ተቃውሞም የጂንስ ቀለም አብዮት (jeans revolution) ተብሎ እንዲሰየም ምክንያት ሆነ!
ህዋሃትን እያብረከረከው ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በየትኛው ቀለም መወከል እንዳለበት ለጊዜው አልታወቀም
Filed in: Amharic