~ መንግሥት በሪፖርተር ጋዜጣ በኩል የዋልድባ አባቶች ክስ ተቋርጧል ብሎ ያውጃል ። በጉን ድግሞ ፍርድቤት ሥራውን በመነኮሳቱ ላይ ቀጥሏል ። እኔ የማዝነው ኦርቶዶካሲዊ ሆኖ የህወሓት ፣ የኢህአዴግ አባል ለሆነ ዜጋ ነው – ውሸት ጌጡ።
#ETHIOPIA | ~ አዲስአበባ ~ ቂሊንጦ ~ ዋልድባ
~ እነ አባ ገብረ ኢየሱስ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሓላፊዎች እያደረሱባቸው ያለውን በደል ለፍርድ ቤቱ አቤት በማለታቸው ምክንያት ነበር ፍርድ ቤቱ አቤቶታ የቀረበበትን የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ምላሽ እንዲሰጥ ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረው ።
~ ማረሚያ ቤቱ እንደተለመደው አይኑን በጨው ታጥቦ ሽምጥጥ አድርጎ ክዷል ። ምንም አላደረኩም ። አባቶች ያቀረቡት ውሸት ነው ብሏል ። የሚገርመው ውሸት የኢህአዴግ መንግሥት የባህሪ መገለጫው መሆኑ ነው ። ከሚንስትር እስከ ካድሬ ውሸት ። ሐሰት ። አቤት እግዚኦ.!
~ አባ ገብረ ኢየሱስ ግን ለፍርድ ቤቱ እንዲህ አሉ ። መንግሥት እኔን ከያዘኝ አንድ ዓመት ከሁለት ወር ሆኖኛል። ነገር ግን ከተያዝኩ ጊዜ ጀምሮ በአንድ የምንኩስና ልብስ ነው ያለሁት ። ቅያሪ ልብስ እንዳይገባልኝ ተከልክያለሁ ። በዚህም ምክንያት በተባይና በሌሎች ተዛማጅ በሽታዎች እየተጠቃሁ ነው ። እናም ፍርድ ቤቱ ልብስ እንድቀይር እንዲያዝልኝ እጠይቃለሁ በማለት አመልክተዋል።
~ ማረሚያ ቤቱ ይኼንንም ሸምጥጦ ለማለፍ ቅሽሽ እንኳ አላለውም ። ፍርድቤቱም ልብሳቸውን የመቀየር መብት አላቸው በማለት ወሰነ ።
~ አባም እንግዲያውስ ልብሴን እዚሁ ችሎት ውስጥ እረከብ ዘንድ ፍርድ ቤቱ ይዘዝልኝ አሉ ። ማረሚያ ቤቱም አይ እዚያው ይምጣ ቢልም የግራ ዳኛው አይተ ዘርዓይ ግን ዛሬ ልባቸው ራርቶ አይሆንም እዚሁ ይቀበሉ በማለታቸው አንድ ወጣት ለአባ በፍርድ ቤቱ ውስጥ ችሎቱ ላይ ሁሉም እያየ የሚቀይሩትን ልብስ ለአባ አስረክቧቸዋል ። ምንም እንኳ ፍርድ ቤቱ የጨቋኞች መሳሪያ መሆኑ ቢታወቅም ዳኛው ልብሱ ለአባ እንዲሰጣቸው በፈቀዱ ጊዜ አባ ዳኛውን ያመሰገኑበት ፣ ፍርድ ቤቱን ያመሰገኑበት መንገድ ” የአባቶቻችንን የትህትና ጥግ ” አመልካች ነበር ተብሏል ። ዳኞቹም በአባ ትህትና ሲረበሹና ሲጨነቁ ታይተዋል ።
እንዴት ግን አንድ እስረኛ 1ዓመት ከ2 ወር እየተገረፈ ፣ እየተቀጠቀጠ ፣ መሬት ላይ እየገጎተተ ፣ የበጋው ፀሐይ ሙቀቱና ላቡ እየተፈራረቀበት ፣ በተባይ ፣ በታይፈስ ተጠቅቶ በበሽታ እንዲሞት ይፈረድበታል ። በእውነት እነዚህ ኢትዮጵያን የሚመሩ ሰዎች ስለ እውነት የትግራይ ተወላጆች ናቸው ወይ ? የአክሱም ጽዮን ፣ የደብረ አባይ ፣ የደብረዳሞ አረጋዊ ፣ የአብርሃ ወአጽብሐ ልጆች ናቸው ወይ ? እኔ ግን አይመስሉኝም ። እነ አህመዲን ጀበልን የፈታ የህወሓት መንግሥት የዋልድባ አባቶችን ለመፍታት ምን እጁን ያዘው?
መነኮሳቱ ዐማራ መሆናቸው እንዳስጠቃቸው ይሰማኛል ፣ የዐማራ ክልል መንግሥትን የሚመሩት ደግሞ አማረደኛ ተናጋሪ ትግሬዎች ስለሆኑ ጉዳያቸው አይደለም ። ቤተክህነቱም እንደሚታወቀው ነው ። የዐማራ አገልጋዮች ለዘበኝነት እንኳ አይፈለጉም ። ይኼ ነገር ደግሞ ጣጣው ወደፊት ለሀገሪቱ መልካም አይደለም ።
~ ይኽ በእንዲህ እንዳለ በዛሬው ችሎት የሚገርመው ለላንቲካ የተቀመጡት የመሃልና የቀኝ ዳኞቹ ታኮ ሆኖ የተመደበላቸውን የግራ ዳኛው አይተ ዘርአይ የሚሉትን ከማድመጥ በቀር ሌላ አቅም እንደሌላቸው ያስታውቅ ነበርም ይላሉ ምንጮቼ ።
~ አባ ገብረ ኢየሱሰ ለፍርድ ቤቱ ሌላ አቤቱታም አቅርበዋል ” አሁንም በቂሊንጦ ዞን 5 በሚባል አደገኛ የእስር ዞን ውስጥ እየተሠቃዩ መሆኑን ገልጸው ፣ ያጣፋሁት ጥፋት ካለ ይነገረኝ እና ቅጣቴን አምኜ ልቀበል ወይ ደግሞ ከዚያ አስወጡኝ ፣ ቀይሩኝም ፣ ሻይም ሆነ ምግብ የሚመጣልን ከሌላኛው ዞን ስለሆነ ለሁለት ሰው የሚመጣው ምግብ እየተበላሸ ነው ። ሶፍት እንኳን ለመግዛት ከ10 ብር ላይ እላፊ 1 ብር እየከፈልንም ነው ። አንድ ብር ለእኛ በጣም ትልቅ ጥቅም አላት ሲሉ በተዳከመ ድምጽ ፍርድቤቱን ጠይቀዋል ፡፡ [ ይኼን በሰማሁ ጊዜ ምእመናን ለአዲስ አበባ አብያተ ክርስቲያናት በሚሰጡት ሙዳየ ምጽዋት እነ ዳዊት ያሬድ የከፈቱት ቡናቤት ፣ እነ ጎይቶም የገነቡት ቪላቤት ፣ የሰዓሊተ ምህረቱ ጃኩዚና ሻኪሶ ትዝ ትዝ ብለው ናፈቁኝ።
~ ለዚህም አቤቱታ ምላሽ ማረሚያ ቤቱ ጨለማ ቤት የሚባል የለም፡፡ እምነት እኩል ነው ። እነሱ ግን አመጸኞች ናቸው የሚል የጽሑፍ መልስ ነው በአይተ ዘርዓይ በኩል በጽሑፍ እንዲነበብ ያደረጉት ።
~ ፍርድቤቱም ለዛሬው የእነ አባ አቤቶታና የማረሚያ ቤቱ የሰጠውን ምላሽ መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት የፊታችን ረቡዕ መጋቢት 5/2010 ዓም ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ሰጥቶ የፍርድ ቤት ውሎው ተጠናቅቆ እነ አባ በመጡበት አኳኋን ወደ ቂሊንጦ ተመልሰዋል ።
~ በዛሬው ችሎት ሁለት የዋልድባ መነኮሳት የእነ አባን የፍርድ ሒደት ለመከታተል በችሎቱ ተገኝተዋል ። ቅዱስ ፓትሪያርኩ በተገኙበት በቀደም ዕለት በተሰበሰበው የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ አንዳንድ አባቶች የመነኮሳቱን ጉዳይ ለማንሳት ሞክረው በፍርሃት ምክንያት ሳይገፉበት እንደቀሩ ተሰምቷል ።
~ ቂሊንጦ ድረስ በመሔድ አባቶችን በመጠየቅ በረከት የሚቀበለው የአዲስአበባ ነዋሪ ቁጥሩ እጅግ መጨመሩም ተነግሯል ። በእውነት በጣም ደስስ ይላል ።
~ እነ አባ ከታሰሩ ጀምሮ በማረሚያ ቤቱ ንስሀ የሚገባውና በነፃ የሚለቀቀው ታሳሪ ቁጥር ጨምሯል ። እስረኞች ለአባቶቻችን የሚያሳዩት አክብሮት የሚገርም ነውም ተብሏል ። መርማሪ ፈልጓቸው እነ አባ ሲጠሩ ” አብሯቸው እስከ ቢሮው ድረስ የሚያጅቧቸው እስረኞችን ማየት የተለየ ስሜት ይፈጥራል ይላሉ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የሚሰሩ የመረጃ ምንጮቼ ።
~ ዛሬም የአዲስ አበባ ህዝብ በሚፈለገው መጠን ባይሆንም ከባለፈው በተሻለ መጠን ቁጥሩ ከፍ ያለ ህዝብ በችሎቱ መገኘቱን የመረጃ ምንጮቼ ነግረውኛል ። መጋቢት 5 እንዳትቀሩ ።
~ በተረፈ ሰሞኑን የመንግሥት የሥጋ ዘመድ የሆነው ሪፖርተር ጋዜጣ ያወጣውና እነ አባ ይፈታሉ ባለው ዘገባው ላይ የሰጠሁትን የራሴን የግሌን አስተያየት ዛሬም እደግመዋለሁ ። ” ካልታዘልኩ አላምንም አለች ሙሽራ ፣ ኢህአዴግን ማመን ቀብሮ ነው አሉ ኢህአፓ ፣ ኦነግ ፣ ገንቦት 7 እና ሻአቢያ ” ።
~ መንግሥት በሚንስቴር ደረጃ ስለሚዋሽ የሚያምነው የለም ። ሰው ሱፍ ለብሶ ፣ ዘንጦ ፣ በቴሌቭዥን ቀርቦ ፣ ሚስቱ ፣ ልጆቹ ፣ ጓደኞቹ ፣ ዘመዶቹ ፣ ቄሱ ፣ ሼኩ ፣ እያየው ሀገር ሁሉ እየተመለከተው የሚዋሽበት ሀገር ቢኖር ኢትዮጵያ ብቻ ናት ።
~ የሚበጀን እወነት አርነት እስክታወጣን መጠበቅ ብቻ ነው። መጽሐፍም እንዲሁ ነው የሚለው ። ” በእውነት አርነት ትወጣላችሁ። ” ዮሐ 8 ፣36