>

ሠዳም ሁሴን… !!! (አሰፋ ሃይሉ)

• ‹‹ሠዳም ሁሴን.. የሞት ፍርድን ከተቀበሉ..  12ኛ ዓመቱ!!!›
– ‹‹ሠዳም ሁሴን.. ሃያ አምስት ዓመታትን ለሚጠጋ ጊዜ.. ኢራቃውያንን ሠጥ ለጥ አርገው.. በአረመኔያዊ የአምባገነንነት ክንድ ገዙ፡፡ ሁሉም ነገር ግን መቼም እንዳማረበት አይቀር፡፡ የተጀመረም ማለቁ ያለ ነው፡፡ እና የሣዳምም አምባገነናዊ የሥልጣን ዘመን በ2003 እ.ኤ.አ. አከተመ፡፡››
– ‹‹እኚህ አምባገነን መሪ – በስተመጨረሻቸው – እንደ ሼኽ ሁሴን ጂብሪል – ትንቢተኛ ሆነው አለፉ ማለት ነው?? ምኑን አውቀነው እኛ?…‹‹አላሁ ይወቅላቸው!›› እንጂ!!! ››
ሠዳም ሁሴን በፉከራቸው ይታወቃሉ፡፡ አሜሪካ ላይ ይፎክራሉ፡፡ እስራኤል ላይ ይፎክራሉ፡፡ ‹‹ቁመቱ የስልክ እንጨት፤ ስፋቱ የበርሜል›› ነው የተባለለትን ‹‹ስከድ ሚሣይል›› በእራኤል ቴላቪቭ ላይ ተኩሰዋል፡፡ ‹‹አሜሪካውያንና አጋሮቻቸው ኢራቅን እንወራለን ብለው ቢሞክሩ.. አለቀላቸው፤ ሪፐብሊካን ጋርዴ… አንገታቸውን እየቀነጠሰ.. በራሳቸው የደም ባህር ይዘፍቃቸዋል!›› ሲሉ በድፍረት ባደባባይ ፎከሩ፡፡
ትልቁ ጆርጅ ቡሽ አጋሮቻቸውን አስተባብረው ‹‹ዘመቻ-ለኢራቅ-ነፃነት›› (ማለትም፡- ‹‹ዘመቻ-ለኢራቅ-ማንበርከክ›› ብንለውስ!).. ብለው ዘመቱባቸው፡፡ ታሪቅ አዚዝ የሚባሉ ኮሚክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበራቸው – ሠዳም ሁሴን፡፡ እና የእነአሜሪካ ጦር አብዛኛውን ባግዳድን ተቆጣጥሮታል፡፡ ሠዳም አብቅቶላቸዋል፡፡ ኮሚኩ ታሪቅ አዚዝ ግን ጋዜጠኞችን በባዶ አስፋልት ላይ እየመሩ.. ‹‹እየውላችሁ.. አንድም ባግዳድን የረገጠ የአሜሪካኖች ጦር የለም – ቢኖርማ ታዩት ነበር!›› እያሉ ድራማቸውን ለጋዜጠኞች ያሳያሉ፡፡ በመጨረሻ ኢራቅ ከኩዌይት ለቀቀች፡፡ ሠዳም ሁሴን ግን በሥልጣን ተረፉ፡፡
የሚገርመው እነ ኮሊን ፓወልና ጆርጅ ቡሽ በውሸት መረጃ ወደኢራቅ ዘምተዋል ተብሎ የትችት ናዳ ወረደባቸው፡፡ ጆርጅ ቡሽ በ2003ቱ የአሜሪካ ፕሬዚደንታዊ ውድድር በወጣቱ ተቀናቃኛቸው በቢል ክሊንተን በምርጫ ተዘረሩ፡፡ ሠዳም ታዲያ ማንም አልቀደማቸውም፡፡ በባግዳድ አደባባይ.. ታላቁ ኃውልታቸው በቆመበት ሥፍራ.. ደጋፊዎቻቸውን ጠሩ፡፡ ከዚያ ሕዝብ በተሰበሰበበት እንዲህ አሉ፡- ‹‹ዛሬ አላህ ትልቅ ነገርን አሣይቶኛል! ሊጥሉን ያሰቡትን ዓይናችን እያየ ጣለልን! ዛሬ በኛ ላይ የዘመተብን ጆርጅ ቡሽ ተሸነፈ! እን?ን ደስ ያላችሁ!›› ካሉ በኋላ.. እዚያው በመድረክ ላይ እያሉ በወገባቸው የታጠቁትን ሽጉጣቸውን መዘዙ.. ከዚያ ወደሰማይ አከታትለው ሶስት ጊዜ ተኮሱ – ቡሽ ስለተሸነፉ!!! ሰዉ በሠዳም ድርጊት ተገረመ፡፡
ሠዳም ድርጊታቸው ሁሉ አስገራሚና እንግዳ ነው፡፡ ምንም ነገር ሊያደርጉ ካሻቸው የሚመልሳቸው ነገር የለም – በቀልባቸው ነውና የሚመሩት!! ምዕራባውያኑን ደግሞ እንቅልፍ የነሣቸው.. ይኸው የሠዳም ድንፋታ እና ምንም ነገር ከማድረግ ወደኋላ የማይሉ የመሆናቸው ነገር ነበር!! እና ሠዳም በድንገት በእጃቸው.. ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ ቢገባ.. ወይም ደግሞ.. ድንገት.. ባጋጣሚ.. በፔትሮ ዶላራቸውም ሆነ በማናቸውም መንገድ ተጠቅመው.. ድንገት ባቋራጭ.. የሆነ አደገኛ የኬሚካል.. አሊያም የባዮሎጂካል.. አሊያም የኒውክሊየር መሣሪያ እጃቸው ቢገባ.. ሰውየው.. በማንም በተቃረናቸው ኃይልና ሃገር ላይ ‹‹ተኩሥ!!›› የሚል ትዕዛዝ ለመስጠት የሚገዳቸው ዓይነት ሰውዬ ሆነው አላገኟቸውምና.. ምዕራባውያኑን.. እስራኤላውያኑን.. እና ኢራናውያኑንና ሣዑዲዎቹን ሁሉ ሳይቀር.. ፍራት ፍራት አላቸው፡፡
እና በቃ.. ሠዳም ካልተወገዱ… ሠላም የለም ብለው ደመደሙ፡፡ የሠዳም ደጋፊዎችና ያለማቀፍ የሉዓላዊነት አቀንቃኞች ደግሞ.. የአንድን ሉዐላዊ ሃገር መሪና ባለሥልጣናት.. እንደአሸባሪ እያደኑ መደምሰስና መግደል.. ይህ ራሱ… ዓይን-ያወጣ.. አሸባሪነት ነው ባይ ነበሩ፡፡
ብቻ ምንም ተባለ ምንም… የሠዳም ቀናት እየተቆጠሩ መጡ፡፡ ኃያላኑ ሊዘምቱባቸው ተሰናዱ፡፡ ደግሞም ዘመቱባቸው፡፡ ድሮ ሠዳም በደስታ ባደባባይ ተሸነፉልኝ ብለው ሽጉጣቸውን በደስታ ያስተኮሷቸው.. የትልቁ ጆርጅ ቡሽ ልጅ.. ትንሹ ጆርጅ ቡሽ.. እኔም እንዳባባ.. ብለው በሠዳም ላይ ዘመቱባቸው፡፡
ሠዳም እና የገነቡት አምባገነንም.. ጀብደኛም.. ለአረቦቹ ደግሞ መመኪያም የነበረ.. ደመ-መራራ መንግስታቸው.. ሁሉም.. ባንድነት ተገረሰሱ፡፡ ሠዳም ወደትውልድ መንደራቸው ሄደው ተሸሸጉ፡፡ ሴቶችን ከባሎቻቸው እየቀሙ.. ያሻቸውን ካደረጉ በኋላ.. እነርሱ የነኳትን ሴት.. ሌላ ሰው እንዳይነካባቸው ለምልክትነት.. በሴቲቱ መቀመጫ ላይ በጋለ የብረት ማህተም አግለው ምልክታቸውን እስከማተም የደረሱት የተባለላቸው.. ከልካይ ያልነበራቸው የሣዳም ሁለት ወንዶች ልጆችም.. ኡዴና ቁሴ.. መጨረሻቸው በላውንቸር እንዳልነበሩ ሆነው.. አሣዛኝ.. የከፋ ሞት ሆነ፡፡
ታዲያ ሠዳም.. ከፉከራዎቻቸው አንዱ፡- ‹‹እኔ ከሥልጣን ከተወገድኩ በኋላ.. አሜሪካኖችና አጋሮቻቸው በዚህች ሃገር ላይ በሰላም እንኖራለን ብለው እንዳያስቡ… አይተው የማያውቁት ዓይነት ማብቂያ የሌለው የሽምቅ ጦርነት እንደሚጠብቃቸው ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ!!›› ሲሉ ፎክረው ነበር.. ሠዳም ከቲግሪስ ከተደበቁበት ዋሻ ተይዘው.. ወደሞት ፍርዳቸው ከመወሰዳቸው በፊት፡፡ የሚገርመው ከእርሳቸው የሥልጣን መገርሰስና መወገድ ማግስት.. እስካሁን በኢራቅ.. ሠላም የለም፡፡ ሰቆቃውም በዝቷል፡፡ እና እኒህ ሠዳም ሁሴን.. ምናልባት ንግርታቸው ይዞላቸው ይሆን?? አንድዬ ይወቅላቸው፡፡
የሚገርመው ግን.. አንድ ያሜሪካኖች ድርጊት ነበር፡፡ እርሳቸውን ከተደበቁበት ዋሻ አድኖ የሚይዛቸው ወታደር ልክ እንደያዛቸው ማንነታቸውን ለማወቅ አፋቸውን በግድ አስከፍቶ.. ትንፋሻቸውንና የጥርሳቸውን አቀማመጥ ወሰደ፡፡ ከዚያ እርሳው መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ እንዲነግራቸው የተሰጠው አንድ ጥብቅ ቃል ነበረ፡፡ እና ልክ ሰውየው ሠዳም መሆናቸውን እንዳረጋገጠ እንዲህ ነበር ያላቸው፡-
‹‹ሠዳም ሁሴን፤ እነሆ የአሜሪካው ፕሬዚደንት ጆርጅ ቡሽ፤
የከበረ ሠላምታቸውን አድርሰውልዎታል፤
እንኳን ወደኛ እጅ በሠላም መጡ!››፡፡
ያስገርማል፡፡ አያድርስም ነው፡፡ ሠዳም ሁሴን.. ሃያ አምስት ዓመታትን ለሚጠጋ ጊዜ.. ኢራቃውያንን ሠጥ ለጥ አርገው.. በአረመኔያዊ የአምባገነንነት ክንድ ገዙ፡፡ ሁሉም ነገር ግን መቼም እንዳማረበት አይቀር፡፡ የተጀመረም ማለቁ ያለ ነው፡፡ እና የሣዳምም አምባገነናዊ የሥልጣን ዘመን በ2003 እ.ኤ.አ. አከተመ፡፡
ታሪከኛውና ጀብደኛው ግዞተኛ ንጉስ ሠዳም ሁሴን የዛሬ 10 ዓመት፤ በዲሴምበር 30 ቀን 2006 እ.ኤ.አ.፤ ዘግናኝ በሆነ አኳኋን.. በሲባጎ ታንቀው ሲሞቱ ለዓለም እየታየ… የሞት ፍርድ ተፈፀመባቸው!! ሠዳምም ላይነሱ ሥልጣናቸውንና ይህችን ምድር ተሰናበቱ፡፡ የሠዳም ኃውልቶችም ከያሉበት በውርደት ተገረሰሱ፡፡ ያች የሜሶፖታሚያ ጥንታዊ ምድር – ኢራቅ እና ሕዝቦቿም – በዚያች ዕለት ከአምባገነኑ የጭካኔ መዳፍ እፎይ አሉ፡፡
የሚገርመው ግን – ያች – ከግብዓተ-መሬታቸው በኋላ – ታይቶ የማይታወቅ ማብቂያ የሌለው የሽምቅ ጦርነት እንደሚጠብቃት – በራሳቸው በሠዳም አንደበት – አስፈሪ ትንቢት የተነገረላት ኢራቅ – እንዳለመታደል ሆኖ – አሁንም – በጦርነትና ሽብር መናጥ አልቀረላትም፡፡ እኚህ አምባገነን መሪ – በስተመጨረሻቸው – ባለቀ ሠዓት – እንደ ሼኽ ሁሴን ጂብሪል – ትንቢትን ተናጋሪ ሆነው አለፉ ማለት ነው?? – ምኑን አውቀነው እኛ?!!…‹‹አላሁ ይወቅላቸው!›› እንጂ!!!
ሠላም ለዓለም ይሁን፡፡ አበቃሁ፡፡
Repost:
Photograph:
“British Coalition Soldiers Posing at Crumbled Monument of Saddam Hussein, 2003, Baghdad.”
Filed in: Amharic