>

ወያኔ/ኢሕአዴግ የገጠመውና ሊያስታርቀውም የማይችለው የርዕዮተዓለሙ ቀውስ!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
አይይይ! በጣም ያሳዝናል! አላዋቂ ሳሚ ምን ይለቀልቃል አሉ! ያለ ዕውቀት ያለ የጠራ ግንዛቤ የሚሠራ ሥራ ሁሉ ስሕተት መሆኑና ለከባድ ኪሳራ መዳረጉ፣ ነገሮችን እንዳይሆኑ አድርጎ ማበላሸቱ የይቀር ነገር ነው፡፡
እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ስሕተቱ የሚፈጸመው በሀገርና ሕዝብ ላይ መሆኑ፣ ሀገርና ሕዝብ ለከባድ ጉዳት ተዳርገው የደናቁርት መማሪያ መሆናቸው፣ በደናቁርቱ ስሕተት ሀገርና ሕዝብ አሳራቸውን ማየታቸው አበሳቸውን መቁጠራቸው ነው፡፡ በሌላ በኩህ ስናየው ጥቂቶችን አጥፊዎችን ጉልበተኛና አራጊ ፈጣሪ ያደረጋቸው ከሕዝብ በላይ ኃይልና አቅም ኖሯቸው ሳይሆን የእኛ የሕዝቡ ዝምታ ነውና እንደፈለጉ እንዲፋንኑብን ያደረጋቸው ይበለን ያሰኛል፡፡
ወያኔ እየተከተለው ያለው ርዕዮተዓለም ማለትም ብሔረሰቦች ወይም ሕዝብ እንደ የሰው ልጅነታቸው ምንጫቸው አንድ እንደመሆኑና ከአንድ እናትና አባት የተገኙ እንደመሆናቸውና አንድ ደም እንዳላቸው ሳይሆን ልክ የተለያዩ ፈጣሪዎች (እግዚአብሔሮች) እንዳሏቸው የተለያዩ ፍጡሮችና በደም ፈጽሞ እንደማይገናኙ አድርጎ ልዩነትን ሲሰብክና ሲከፋፍል መኖሩ ጣጣ እንዳመጣ፣ ችግር እንደፈጠረ ሲያውቅ በየብዙኃን መገናኛውና በየመድረኩ በባለሥልጣናቱና በአፈቀላጤዎቹ በኩል “…ብሔርተኝነት ጎልቶ መውጣቱ፣ ብሔርተኝነት መራገቡ፣ በልዩነታችን ላይ ብዙ በመሠራቱ፣ አንድ በሚያደርጉን ነገሮች ላይ ባለመሠራቱ፣ አንድ ለሚያደርጉን እሴቶች ትኩረት ባለመሰጠቱ ነው እርስበርሳችን እንደ የተለያዩ ሀገር ሕዝቦች እንድንተያይ ያደረገን፣ ሀገር ልትረሳና ጠባብ ብሔርተኝነት ሊሰፍን የቻለው፡፡ በሌላ በኩልም የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ችግር ፈጠረ ተብሎ ብሔርተኝነት ተረስቶ ወይም ዝቅ ብሎ ሀገር ጎልታ መውጣት አይኖርባትም፡፡ የብሔር ጭቆና ተወግዶ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን ለማስከበር ብዙ ዋጋ ተከፍሎበታልና፡፡ ለሁለቱም እኩል ትኩረት መስጠት፣ ሁለቱንም እኩል አመጣጥኖ ማስኬድ ችግሩን ይቀርፋልና በዚህ ላይ በርትተን መሥራት ይጠይቀናል፡፡ ይሄንን በማድረግ  የተጋረጠብንን አደጋ ማስወገድ ይቻላል!” እያሉን ይገኛሉ፡፡
ወያኔ ጭንቅ ብሎታል! በአንድ በኩል “አላሠራ ያለኝን የጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) አሥተዳደርን ወዲያ ጥየ ኢሕአዴግን ወደ ውሕድ ፓርቲ በማምጣት አሐዳዊ የመንግሥት አሥተዳደር ሥርዓት መሥርቸ ሌላ የአገዛዝ ዘመን ብፈጥርስ?” ብሎ ያስባል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ዓይነት አሐዳዊ አሥተዳደር መመሥረቱ ወያኔ የተመሠረተበትንና የታገለበትን የአስተሳሰብ መሠረት ማለትም “የብሔር ብሔረሰቦች መብትን ማረጋገጥና የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት የማድረግ ትግል ስሕተት ነበረ!” ብሎ ማመን ስለሆነበት ተቸግሮ መንታ መንገድ ላይ ተገትሮ በመቁለጭለጭ ላይ ይገኛል፡፡ በዚሁ እንዳይቀጥልም ሉዓላዊ ሥልጣንን የተጎናጸፈው የጎሳ ፌዴራሊዝም ከአዲስ አበባ የማስፋፊያ ዐቢይ አቅድ (ማስተር ፕላን) ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ሕዝባዊ ዐመፅና ተቃውሞ የጎሳ ፌዴራሊዝሙ (የራስ ገዙ) የአሥተዳደር ሥርዓት የልማት እንቅፋት እየሆነ፣ ለሰላምና መረጋጋት ጠንቅ እየፈጠረ አላሳልፍ ብሎታል፡፡
ያውም እኮ ሉዓላዊ ሥልጣንን እንዲጎናጸፉ አድርጌያቸዋለሁ የሚላቸው ብሔር ብሔረሰቦች ወያኔ በሚናገረው ደረጃ ሥልጣኑንና መብቱን ሳያጎናጽፋቸው በጥቂቱ መጥኖ በሰጣቸው መብትና ሥልጣን እኮነው ይሄ ሁሉ ችግር የተከሰተው እንጅ ሙሉ በሙሉ በሕገ መንግሥታቸው እንዳሠፈሩት መብቱንና ሉዓላዊ ሥልጣኑን ቢጎናጸፉና የወያኔ ሞግዚትነት ባይኖርማ ኖሮ ችግሩ ከዚህም እጅግ የከፋ በሆነ ነበረ እኮ፡፡ እናም ወያኔ መላው ጥፍት ብሎት እጅግ ተቸግሯል፡፡ ደንቆሮው መለስ ዜናዊ እንዲህ ዓይነት መውጫ በሌለው ትብትብ ውስጥ ከቷቸው ሔዶ ወያኔ/ኢሕአዴጎች የሚያደርጉትን አጥተው በመቁለጭለጭ ላይ ይገኛሉ፡፡
አሁን እኔ ላሳያቹህ የፈለኩት ዐቢይ ጉዳይ የወያኔ ባለሥልጣናት እያሉት እንዳለው እውን ለብሔርተኝነትና ለሀገር እኩል ትኩረት በመስጠት፣ እኩል በማስኬድ ብሔረሰቦችን የአንድነት ስሜትንና ብሔራዊ መግባባትን እንዲፈጥሩ ማድረግ ይቻላል ወይ? የሚለውን ጉዳይ ነው፡፡ መልሱ ባጭሩ ፈጽሞ አይቻልም ነው፡፡ እንዴት? ለምን? የሚለውን እንይ፦
ሁላችንም አንድ ለሚያደርገን የጋራ ጉዳይ ማለትም ለሀገር ብልጫ ካልሰጠንና እዚያ ላይ ካልተገናኘን፣ አብረን ካልቆምን በስተቀር ልንተሳሰር፣ በጋራ ልንቆም፣ የአንድነት ስሜትና መግባባት ልንፈጥር አንችልምና ነው፡፡ በጋራ ለመቆም፣ አንድነትን ለማምጣት የግድ ሁላችንም ብልጫ ትኩረት የምንሰጠው፣ ሁላችንም ይበልጥ የምንሳሳለት የሁላችን የምንለው አንድ ጉዳይ መኖር አለበት፡፡ ሁላችንም አብልጠን የምናየው የጋራችን የምንለው ነገር ከሌለና የየብቻችን የምንለው ነገር ካለ አንድነትና ብሔራዊ መግባባት ፈጽሞ ሊመጣ አይችልም፡፡
ስለዚህ የአንድነት ስሜትንና ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ሁላችንም የምንገበገብለት፣ የምንሳሳለት፣ አብልጠን የምናየው የሚያስተሳስረን የጋራ ሀብት እንዳለን ልናውቅና ልንፈቅድ ወይም ሊኖረን ይገባል ማለት ነው፡፡ ይህ የምንሳሳለት የምንገበገብለት የጋራ ሀብት ሊኖረን የሚችለው ደግሞ ሁላችንም ካለን ነገር ሁሉ ይበልጥ የምንወደው የምናከብረው ሲሆን ነው፡፡ ይሄ ከሁላችንም በተዋጣ ፍቅር የሚወደድ የጋራ ሀብት እንዳለን ካላመንንና ካልተቀበልን በስተቀር አንድነትና ብሔራዊ መግባባት የሚባል ነገር ከቶውንም ሊኖረን አይችልም፡፡
ቀላል ምሳሌ ልስጣቹህ፦ 
አንድ ዓለምአቀፋዊ ሃይማኖትን ውሰዱ፡፡ በዚህ ሃይማኖት ውስጥ ያሉ የተለያዩ ብሔረሰቦች፣ የዘር ዓይነቶችና የተለያዩ ሀገራት ሰዎች እንዴት አንድነትና የጋራ መግባባት ሊኖራቸው የቻለ ይመስላቹሀል??? ሁላቸውም ያን ሃይማኖታቸውን ከየብሔረሰቦቻቸውና ዘራቸው ጥቅም አብልጠው በማየታቸውና በዚህም በመግባባታቸው ነው ሌላ አይደለም፡፡
ሀገርም እንዲሁ ናት፡፡ ሀገራችንን ከየብሔረሰባችን ጥቅም ይልቅ አብልጠን ማየት ካልቻልን በስተቀር በሀገር ጉዳይ ላይ የአንድነት ስሜትና ብሔራዊ (ሀገር አቀፍ) መግባባት ሊኖረን አይችልም፡፡ ሀገርና ሃይማኖት ብቻ ሳይሆኑ ሌላም አንድነት እንዲታይበት የሚፈለግ ነገር ቢኖር በዚያ ነገር ላይ የአንድነት አስተሳሰብን ማምጣት ካስፈለገ በዚያ ነገር ላይ አንድነት እንዲኖራቸው የፈለጉት አካላት ለዚያ ነገር ብልጫ መስጠታቸውንና ለዚህም መግባባታቸውን ማረጋገጥ መቻል ይኖርባቸዋል፡፡ እንዲህ ካላደረጉ በስተቀር የፈለጉትን አንድነትና መግባባት ማምጣት አይችሉም፡፡ እንግዲህ አመክንዮየ ይሄው ነው፡፡ እርግጠኛ ነኝ ያልኩት ሁሉ ገብቷቹሀል፡፡
ሲጠቃለል የርእሰ ጉዳዩ አስኳል ነጥብ የወያኔ የጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) አሥተዳደር እና አንድነት ፈጽሞ የማይግባቡ፣ የማይጣጣሙ፣ እንደ ዘይትና ውኃ ሊዋሐዱ የማይችሉ ነገሮች ናቸው ማለቴ ነው፡፡ የወያኔ የ27 ዓመታት አገዛዝ ውጤት ያረጋገጠልን እውነታ ቢኖር ይሄንን ነው፡፡ ሁለቱንም ማጣጣም ካስፈለገ ሉዓላዊ ሥልጣኑን ለብሔር ብሔረሰቦች ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ መስጠት የግድ ይላል፡፡ በቡድን መብት ሳቢያ የተጨፈለቀውን የግለሰብ መብትንም ታድጎ ከቡድን መብት ጋር እኩል ማረጋገጥ የግድ ይላል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም እንደ ባቢሎን ሰዎች የወያኔ የደነቆረ የጎሳ ፖለቲካ ብትንትናችን ሳያወጣው ፈጥነን በወያኔ ቆዳ ከፍነን መቅበር ይኖርብናል!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
Filed in: Amharic