>

የወያኔ የጠ/ሚ ምርጫ ሴራ ሲጋለጥ (ኦልማ ኦሮሚያ ፔጅ)

ወያኔ ‘የጠቅላይ ሚኒስቴሩ ምርጫ ይቆየንና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በውክልና እየሰሩ ይቆዩ’ የሚል አቋም አንጸባርቃ ከነ ኦቦ ለማ ወገን ከፍተኛ ተቃውሞ አስተናግዳ እንደነበር ሰምተናል፡፡ ይህ ሀሳብ ያለምንም ትንታኔ ሀገሪቱን በወታደራዊ አገዛዝ እንምራት የሚል አንባገነናዊ ፍላጎት የታጀለበት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ስልጣናቸውን ሲለቁ አፋጣኝ እርምጃ ወስዶ ክፍተቱን እንደመሙላትና በውስጥም ሆነ በውጭ የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም እንደመዘጋጀት ‘አብሲት ጥዬ- ጎምን ቀቅዬ’ እያሉ ህዝብን እንዳይረጋጋ ማድረግ ለህዝብ ያለን ብርቱ ንቀት በግልጽ ከማሳየት የዘለለ ሌላ ትርጉም የለውም፡፡

እራሱን እንደ ወያኔ ቃል አቀባይ አድርጎ የሚቆጥረው ዳንኤል ብርሀኔ ያው በተለመደው መሰርያዊ አካሄዱ የአጉራሾቹን ምኞት ይነግረን ጀምሯል፤ ደመቀ ጠቅላይ ሚኒስቴር- ሽፈራው ምክትል አይነት የጅል ሴናርዮ፡፡ ይህ የመሆን እድሉ ሲበዛ ጠባብ ይመስለኛል፡፡ በራሱ በኢህአዴግ መንገድ ብናሰላው እንኳ ብአዴን 27 አመት ሙሉ የምክትሉን ቦታ ሲዘውረው ኖሮ አሁንም ዋናውን ወንበር እንዲይዝ ማድረግ ይሄ ለኦሮሞ ህዝብ ምን ትርጉም እንደሚሰጠው መተንበይ ከባድ አይደለም፡፡ ደኢህዴን ከብዶኛል ብሎ ስልጣኑን በለቀቀ ማግስት ሌላ ደኢህዴን (ያውም ሽፈራውን) እንደገና ሞክረው የሚል ውሳኔ መወሰን አሁንም ለኦህዴድ እና ለኦሮሞ ህዝብ ያለን ንቀት ከማሳየት የዘለለ ይሄ ነው የሚባል ፋይዳ አይኖረውም፡፡
የእህትማማቾቹን ድርጅቶች ሊቃነ መናብርት የህዝብ ተቀባይነት፣ የአካዳምያዊ ብቃት፣ የመሯቸውን ተቋማት ስኬት ….. ወዘተ ብንመለከት እንኳ ዶክተር አቢይን ቀድሞ ሊቆም የሚችል እንደሌለ ዳንኤል ብርሀነም ሆነ ጌቶቹ በግልጽ ያውቁታል፡፡ ወያኔ ‘እንደው ከውስጤ ሰው ባጣ እንኳን ከግንቦት ሰባትም ቢሆን ጠቅላይ ሚኒስቴር አመጣለሁ እንጂ ለኦህዴድ እና ለኦሮሞማ የጠሚውን ወንበር አልሰጥም’ ካላለ በስተቀር ጊዜው የኦህዴድ የጠቅላይ ሚኒስቴርነት ጊዜ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ እንግዲህ ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ ነው ነገሩ……
Filed in: Amharic