>

የዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጲያ ላይ የፖሊስ ለውጥ አዝማሚያዎች (ሃዊ ዳራ)

በአለፉት 27 አመታት ዩ ኤስ አሜሪካ ዋነኛዋ የወያኔ አገዛዝ አጋር ነበረች። በአፍሪካ የአሜሪካ ረድኤት ተቀባይ ከሆኑ አምስት አበይት አገሮች ውስጥ አንዷ ኢትዮጲያ ናት። አሁን ግን ይህ የትላንት ታርክ ወደ መሆን ተቃርቧል። ለዚህ ማሳያ አራት ነጥቦችን አስቀምጣለሁ
1 የአሜሪካ በ2017/18 የበጀት አመት ለኢትዮጲያ ለመስጠት በዕቅድ የያዘችው 132·1 ሚሊዮን ዶላር የኢኮኖሚ ረድኤት ብቻ እንደሆነ የስቴት ዴፓርትመንት የበጀት ሰነድ ያሳያል። ይህ በፊት በአመት በአማካይ 530 ሚሊዮን ዶላር ከነበረው ጋር ሲነጻፀር በጣም የወረደ ሆኖ ይገኛል። በየአመቱ 98 ሚሊዮን ዶላር የነበረው የልማት እርዳታም ሙሉ በሙሉ ቆሟል። ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊስ ማስፈፀሚያ ሶስት ስልቶች አንዱ economic assistance fund እንደሆነ ልብ ይሏል
2 ሌላው የአሜሪካ ዲፕሎማቶችና የስቴት ዴፓርትመንት ባለስልጣናት ከወትሮው የዲፕሎማሲ ብሂል በአፈነገጠ የአገዛዝ ስርአቱን በልደት ስሙ “ minority ethnic regime” እያሉ መጥራት መጀመራቸውና ስርአቱ እንዳበቃለት በገረረ ቋንቋ “TPLF, game is over ” እያሉ መጻፋቸው ነው። ዲፕሎማቶች ‘ቆማጣን ቆማጣ’ የሚሉት በመጨረሻው ሰአት ነው፤
3 የሰብአዊ መብት እንዲከበርና ሁሉን አቀፍ መንግስት እንዲቋቋም የሚጠይቀው ኤች አር 128 የህግ ረቅቅ የወያኔንን ጉትጎታና ልመናን ቸል ብለው ለምክር ቤት ውሳኔ እንዲተላለፍ ማድረጋቸው ሶስተኛው ነው። ልብ በሉ! በ97 ምርጫ ማግስት በእነ ኮንግረስማን ክሪዝ ስሚዝ የተዘጋጀው ረቅቅ ለድምፅ ውሳኔ አላለፈም።
4 ምንአልባትም በጣም የተለየውና ብዙ አንደምታዎች ሊሰጠው የሚችለው ዛሬ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ረዳት ሚንስትር የአፍሪካ ጉዳዮች ሀላፊ ዶናልድ ያማሞቶ ሚኒሶታ ድረስ ሄደው ከኦሮሞ ኮምንቲ ጋር መወያየታቸው ነው። ከኮምንቲው አባላት ጋር የሚኒያፖሊስ ከንቲባ ሄዶ ቢወያይ ምንም አያስገርምም ነበር። ይሄ ለኦሮሞ ህዝብ ትግልና በኢትዮጲያ ፖለትካ ውስጥ የኦሮሞ ህዝብ የአለውን ወሳኝ ሚና እውቅናን የመስጠት ያህል ነው። ኧረ ሰውዬው “ የአገዛዝ ስርአቱ ለለውጥ ዝግጁ አይደለም፤ ድምፃችሁን ማሰማታችሁን ግፉበት…” ሁሉ ብለዋል አሉ።
በፖለትካ ትግል አንዱ የትግል መስክ ዲፕሎማሲ ነው። በዚህ መስክ የኦሮሞ ህዝብ ቤሄራዊ ንቅናቄ ከአሁን በፊት ፍሬያማ አልነበረም። አሁን ግን ሁኔታው በዐይናችን ስር እየተለወጠ ነው፤ እድሜ ለህዝባችን ትግል። ይህ የቀረውን አዝመራ ለመሰብሰብ ትግል አማራጭ የሌለው መሆኑን የሚያስረዳንም ነው። ለነጻነት፣ ለፍትህና ለብሄራዊ ክብራችን የተያያዝነው ትግል ይቀጥላል። የኦሮሞ ልጆች ደምና የእናቶቻቸው እምባ በምንጎናፀፈው ነጻነት ይታበሳል።

Filed in: Amharic