>

የዶ/ር አብይ አህመድ ፈተናዎች (ክንፉ አሰፋ)

    ከልክ በላይ ለጥጠው‹፤ እንደ ልብ አንጠልጥል ፊልም ያቆዩትን ፍትግያ ትናንት በዜና ሲሰብሩት ደስታቸውን ይገልጹ የነበሩት ዜጎች ጥቂት አልነበሩም። ወትሮውን በስብሻለው ከሚለን ስራዓት አዲስ ነገር የሚጠብቅ ተስፈኛ ቢደሰት ብዙም አይደንቅም። የጠቅላይ ሚንስትር እንጂ የስራዓት ለውጥ መች ተመለከትን? ዶ/ር አብይ አህመድ በዚህ ቀውጢ ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ መመረጡ ግን ከክብሩና ከስልጣኑ ይልቅ ፈተናው ያመዝናል።

ለሶስት ቀናት ተብሎ የተጀመረው ግብግብ ይሉት ክርክር  በተነገረለት ቀን መቋጨት ያለመቻሉ በራሱ የሚነግረን ነገር ነበር። አወዛጋቢው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ፣ ፓርላማ ላይ በጸደቀበት ወቅት  ዶ/ር አብይ  በስፍራው ባለመገኘታቸው የህወሃት ሰዎች ክፉኛ እንደተበሳጩ አይተናል። ይህንን ቅሬታ በብሎገሮቻቸውም ሳይቀር ሲገልጹልን ነበር።

ደስታቸውን ከልክ ባለፈ መንገድ እየገለጹ ያሉት ወገኖች ይህንን አጋጣሚ  እንደ ምክንያት ሳይሆን እንደ መዳረሻ ካዩት ግን በህዝብ ትግሉ የተከፈለው መስዋእትነት ሁሉ ከንቱ ነበር ማለት ያስችለናል።  የጠቅላይ ሚንስትርነት ስፍራ የለውጥ ማራመጃ ሳይሆን እንደ አንድ ትልቅ  ግብ ስናየው ነው ስህተቱ።

ማህደረ ትውስታችን አጭር ካልሆነ በስተቀር ሊያሳስበን የሚገባው አዋጁን ተከትሎ የበታች አመራሮች በሙሉ እስር ቤት መታጎራቸው እንጂ የኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር  መሆን አልነበረም። ስሜታችንን ሊነካ የሚችለው  ስደት፣ አፈና እና ግድያው እንጂ በወታደሩ ክርን ውስጥ ያለች ሃገር ጠቅላይ ሚንስትር መሆን አልነበረም።

ግራም ነፈሰ ቀኝ ዶ/ር አብይ ተመርጠዋል።  ይህ ደግሞ ያለ ህወሃት በጎ ፈቃድ ከቶውንም ሊሆን አይችልም። ምርጫ፣ ብልጫ፣ ደብረጽዮን ሁለት ድምጽ፣ አብይ 108 ድምጽ፣ ምናምን የሚሉት ትርክት እኛን ትንሽ ፈገግ ቢያደርገንም ፈረንጆቹን ያሳምን ይሆናል።ምን አይነት ታኮ እንዳሰቡ ባይታወቅም፣  ምርጫቸው ሳይፈልጉት የሚውጡት መድሃኒት አይነት ይመስላል።  እንደ ኮሶ እያንገሸገሻቸው ዶ/ር አብይን በስፍራው አስቀምጠውታል።   ለዚህም አንዱ እሳቤ የኦሮሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን እንቅልፍ እየነሳቸው ያለውን የቄሮ አመጽ ሊያበርደው ይችላል ከሚል ሂሳብ ተነስተው ነው። የሰላማዊው ሽግግር ለውጥ የሚሉት ጨዋታቸው  ደግሞ ለምዕራቡ አለም መሸቀያ ይሆናቸዋል።  የገቡበት አደገኛ ማጥ ፋታ አልሰጣቸውም።  ግዜ መግዛት አለባቸው።

አዲሱ ተመራጭ እርግጥ እንደ መለስ ዜናዊ ባለ ሙሉ ስልጣን ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል? በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈፈረውን ስልጣን ተግባራዊ ያሚያደርግ  ነው ወይ? የሚለው ጥያቄ ግዜ የሚፈታው ጉዳይ ቢሆንም፡ በፊቱ ላይ ሁለት ነገሮች ተደቅነዋል።  እድል እና ፈተና። ምርጫው የሱ ነው።  እንደ አነሳሱ እድሉን ይጠቀምበታል ብለን እናምናለን። ዶ/ር አብይ የህዝብን  ጥያቄ መልሶ እርቅ እና ፍትህን የማስፈን እድል አለው። ይህንን ለማድረግ ደግሞ፡ ይህንን ከማይፈልጉ የህወሃት ጡረተኞች ጋር መፋጠጡ ግድ ይላል።  የህወሃት መርህ የሆነው የዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት በራሱ እንቅፋት ነው። ተግራሮቶቹን እና  እንቅፋቶቹን አልፎ  ይህንን እድል ከተጠቀመ ታሪክ ሰርቶ ያልፋል።  ያ ካልሆነ ግን እንደ ሃይለማርያም ደሳለኝ፣ አሻንጉሊት ተብሎ የሞራልም ውድቀት ይሆንበታል።

ዶር አብይ የአዲሱ ትውልድ ትግል ውጤት ነው። ስለዚህም  ችግሩን ከላይ ሳይሆን ከታች፤  በውስጡ እየኖረ ያውቀዋል።  ከሌሎቹ በበለጠም ይረዳዋል።  እናም ይፈታዋል የሚል እሳቤ አለ። ይህንን ሲያደርግ ብቻውን አይደለም። ለለውጥ የተነሳው ሃይል ከጀርባው እንዳለ ይገነዘባል።

አንደበተ ርቱዕ ነው። አብሮነትን እና ፍቅርን ይሰብካል።  ባገኘው መድረክ  ሁሉ ከዘር ጥበት ወጥቶ ኢትዮጵያን ከፍ የማድረግ አዝማሚያ ይታይበታል።  ይህን ማድረጉ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነትን ከሚያቀነቅኑ ሳይቀር ድጋፍ አግኝቷል። ይህ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ ወታደራዊ አገዛዙ የከረቸመውን በር የመስበር ጡንቻ ይሆነዋል።

“መለስ የጀመረውን ልጨርስ ነው የመጣሁት” ብለው ነበር ሃይለማርያም ደሳለኝ በተሾሙ ወቅት። ዶ/ር አብይም ሃይሌ የጀመሩትን አንዳንድ ነገሮች ከዳር እንደሚያሰርስ ተስፋ አለን። ለምሳሌ ማዕከላዊ ሚዚየም ሆኖ ያስጎበኙናል።

አብይ ስፍራውን የያዘው ኢህድግን ለማዳን ነው ወይንስ ሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ? ግዜ ይጠይቃል። ጥያቄውን እሱ እና የለማ ቲም የሚመልሱት ይሆናል።  … መልካም እድል!

Filed in: Amharic