Winners (አሸናፊወች)
1. የአማራ ህዝብ
የአማራ ህዝብ ስልጣን ይገባኛል እኔ ጠቃላይ ሚኒስቴር ካልሆንኩ ሞቼ እገኛለዉ አላለም፡፡ ፍትሃዊ የሆነ የፖለቲካ፤ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስርአት እንዲኖር፤ማንነቱ እንዲከበርለት ነዉ እየጠየቀ ያለዉ፡፡የተሻለ መሪ ነዉ ብሎ ካሰበ የአማራ ህዝብ የግድ ከራሴ ይዉጣ የማይል፤ብሄርና ዘር ሳያጥረዉ ብቁ መሪና ህዝብን አክባሪ ከሆነ ያለምንም ማመንታት የሚደግፍ ነዉ፡፡
2. ኦህዴድ
ኦህዴድ ገፍቶ ወደፊት በመምጣት ህወሃትን አስጨንቆ የጠቅላይ ሚኒስቴርነቱን ቦታ ተቀብሎታል፡፡ ህወሃት ብዙ ቢጥርም የኦህዴድን የስልጣን ፍላጎት ሊያስቀረዉ አልቻለም፡፡ኦህዴድ ጠቅላይ ሚኒስቴር ካልሆነ ይፈርሳል ብየ ነበር፡፡ ስለዚህም ኦህዴድ ጠቅላይሚኒስቴር መሆኑ ህልዉናዉን እንዲታደግ አድርጓል፡፡ የታሰሩበት ሰወችም ይፈታሉ መዋቅሩም እንደነበረዉ እንዲያዉም ከነበረዉ ተሸሎ ይቀጥላል ተብሎ ይገመታል፡፡
3. ገዱ አንዳርጋቸዉ
ህወሃትን እያነከሰ በከዘራ እንዲሄድ ካደረጉት ሰወች ዉስጥ ገዱ የመጀመሪያዉ ነዉ፡፡ አቅም በነበረዉ ጊዜ ህዋሀትን እንገዳግዶታል፡፡ ኦህዴድ ህዋሀትን ማንገራገር የተማረዉ ከገዱ ነዉ፡፡ በዛ አላበቃም ኦህዴድን ባህርዳር ድረስ በመጋበዝ ግንኙነቱን አጠናክሯል፡፡ ህዋሀትም መርህ አልባ ጉድኝነት ብሎ ስም ሰቶታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በመጀመሪያዉ በ17ቱ ቀን ስብሰባ ለማና ዶ/ር አብይ ላይ ህዋሀት አስራለዉ ብሎ ሲያንገራግር ነዉር አንደሆነና እንደማይባል ነግሯቸዋል፡፡ ህዋሀቶች እሱን ለማዉረድ አንድ ሚሊየን ጊዜ ሞክረዋል፡፡ አልሆን ሲል አባይን እናዉርደዉና እሱንም በዛዉ ሰበብ ማዉረድ ይቻላል ብለዉ ቢሞክሩም አልተሳካም፡፡
ለማ የሊቀመንበርነቱን ቦታ ለዶ/ር አብይ መልቀቁ ትክክል የነበረ ሲሆን ሊቀመንበር ያልሆነ ሰዉም መመረጥ ይችላል በማለት ህወሀቶች ለማታለል ቢሞክሩም ሴራቸዉን አክሽፎታል፡፡ ለማ ከመጀመሪያዉ እስከመጨረሻዉ በአቋሙ ጸንቶ ህወሃትን እየተገዳደረ እስከዚህ ደርሷል፡፡ ሊረብሹ የሚችሉ ሽማግሌ አባላቶችን አስወግዷል፡፡ የኦህዴድ አመራር ሙስና ዉስጥ እየተዘፈቀ ሲያስቸግረዉ ብዛት ያላቸዉን ሴቶች በመመልመል ሙስና በስፋት አለባቸዉ የተባሉ ከተሞች ላይ ከንቲባ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ አባዱላን አከብርሃለዉ ነገር ግን ከምትሰራዉ ስራ ተቆጠብ አሁን ላለንበትና ለደረስንበት የኦሮሞ ህዝብ ትግል የሚመጥን ስራ አይደለም በማለት ማስጠንቀቂያ በመስጠት እንዲያርፍ አድርጎታል፡፡ በኦህዴድ ስብሰባወች ላይ በተደጋጋሚ የአማራን ህዝብ ሳንይዝ ለዉጥ እናመጣለን ማለት መቃዠት ነዉ ብሎ ለአንዳንድ የኦነግ አክራሪዎች እንቅጩን ነግሯቸዋል፡፡
ደ/ር አብይ በህወሃት ደህንነቶችና አክቲቪስቶች የተሰነዘረበትን ፕሮፖጋንዳ ቻል አድርጎ እስከመጨረሻዉ መጽናቱና በመጨረሻም ስልጣኑን ማግኘቱ አሸናፊ ያደርገዋል፡፡ አባዱላ በሳምንት ሶስት ቀን ቢሮዉ እየሄደ የኦህዴድን ሊቀመንበርነት እኔ ልዉሰድ ጠቅላይ ሚኒስቴርንቱን ካንተ ዉጪ ለሌላ የኦህዴድ ሰዉ አንሰጥም ብለዋል እያለ ቢለማመጥም ጀሮ ሳይሰጠዉ እሱም ማስጠንቀቂያዉን አከናንቦታል፡፡ ዶ/ር አብይ ማስጠንቀቂያ የሰጠዉ ለአባዱላ ብቻ ሳይሆን ከሱ ጋር ነገር የሚያመላልሱትንና ዉጪ ካሉ ተቃዋሚዎች ጋር መስመር ለፈጠሩ ባለሃብቶች ሁሉ ነዉ፡፡ እነዚህ ባለሃብቶች ዶ/ር አብይ ቢሮዉ አስጠርቶ ማስጠንቀቂያዉን ከሰጣቸዉ በኋላ አርፈዉ ተቀምጠዋል፡፡ ሌላዉ ዶ/ር አብይ የጃዋርን ፖለቲካ አይፈራም፤አይለማመጠዉምም፡፡ ሌሎቹ ኦህዴዶች ጃዋርን ከህዋሀቶች በላይ ይፈሩታል ይለማመጡታልም፡፡ ይሄ ጉዳይ ነዉ በሁለቱ ሰወች መካከል የመናናቅ ስሜት የተፈጠረዉ፡፡
መለስ ግርማ ብሩን የሽዋ ፖለቲከኛ ነዉ አልወደዉም፤ ከፊቴ ዞር አድርጉልኝ ይል ነበር፡፡ ግርማ ብሩ የተረጋጋ ነዉ፤የፖለቲካ ሁኔታን ሰከን ብሎ የመረዳትና የመገንዘብ ዝንባሌ አለዉ፡፡ ለማንኛዉም ድምጹን አጥፍቶ አሜሪካኖችን ስለኦህዴድና የለማ ቡድን ስለሚባለዉ ማብራሪያ ሰቷል፡፡ ግርማ ከያማማቶ (የጊዚያዊ የአፍሪካ ጉዳዮች) እንዲሁም ከሊንዳ ቶማስ ግሪን ፊልድ (በኦባማ ዘመን የአፍሪካ ጉዳዮች) ጋር ጠበቅ ያለ ግንኙነት አለዉ፡፡ ከዚህ በፊትም ዶ/ር ቴወድሮስ ለአለም ጤና ድርጅት ሲመረጥ እኒህን ሰወች በማግባባት አግዞታል፡፡ እነ አንቶኒ ካሮል የተባሉ የማንችስተር ትሬድ ግዙፍ አለም አቀፍ የቢዝነስ ድርጅት ፕሬዝደንት በተለይም የአፍሪካ መንግስታትን በማማከርና እነሱንም በመወከል የአሜሪካን መንግስት የሚያግባቡ አፍቃሪ ኢሀደጎች ጋር ጥሩ ግንኙነት አለዉ፡፡ አሜሪካኖች ግርማ ብሩን ስለ ለማና ዶ/ር አብይ ጠርተዉ እንዲያስረዳ አድርገዋል፡፡ከግርማ ብሩ ጋር እነዚህ የጠቀስኳቸዉ ሰወች አብረዉ ቀርበዉ ያለዉን ሁኔታ አስረድተዋል፡፡ አሜሪካኖችም ስለ ቡድን ለማ የሚባል በቂ መረጃ ካገኙ በኋላ እምነት ጥለዉባቸዉ ቀጥታ አዲስ አበባ በመሄድ ይሄን ሰዉየ ጠቅላይ ሚኒስቴር አድርጉ ብሎዉ ተመለሱ፡፡ በነገራችን ላይ የህወሃት እጅግ ከመስመር የወጣ ጥላቻና ግምገማ ዶ/ር አብይን ጠቅሞታል፡፡ ብዙዉ የኦህዴድና የብአዴን አባላት በመበሳጨታቸዉ ህወሃትን በመቃወም ብቻ ከ ዶ/ር አብይ ጎን እንዲቆሙ ሁኗል፡፡ ለግምገማ የተዘጋጀዉ ዶክመንት ድርጅትን ሳይሆን ግለሰብ ላይ ያተኮረ መሆኑ እራሱ ብዙወቹን አበሳጭቷል፡፡ ዶ/ር አብይን ከ17ቱ ቀን በተለየ ሁኔታ ሁሉም የኦህዴድ አባሎች ሲከላከሉት ነበር በተለይም ከለማ ቀጥሎ ግርማ ብሩ ከፍተኛ መከላከል አድርጓል፡፡ አሜሪካኖችን አግባብቷል በመጨረሻም ህወሃት ዶ/ር አብይ ላይ ያዘነበዉን ዉርጅብኝ ትክክል አይደለም ብሏል፡፡ እንግዲህ ግርማ ብሩ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠዉ ይሆናል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ የመሆን አድሉ ሁሉ አለዉ፡፡ በነገራችን ላይ አሜሪካኖች ኦህዴዶችን በጣም በቅርብ ግዜ ነዉ ያመኗቸዉ፡፡ አገር ሊገነጥሉ ነዉ ብለዉ ህወሃቶች እየመረጇቸዉ ነበር፡፡ ግርማ ብሩ ይሄን ከእዉነት የራቀ እንደሆን አስረግጦ ነዉ የነገራቸዉ፡፡ ይሄ ጥያቄ ለዶ/ር ወርቅነህም ቀርቦለት ነበር፡፡
losers ተሸናፊዎች
1. ህወሃት
ህወሃት የኔ ከሚለዉ ድርጅት ከኢሃዴግ ዉስጥ ለጠቅላይ ሚኒስቴርነት የሚወዳደርን ሰዉ ልክ እንደተቃዋሚ አይንህን ላፈር ማለቱና ዉጤቱም ጭራሽ የልጠበቀዉ መሆኑ ከባድ ተሸናፊ ያደርገዋል፡፡ ሽጉጤን የደህዴን ሊቀመንበር እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት አድርጎ ከዛም ጠቅላይ ሚኒስቴር ለማድረግ ያልፈነቀለዉ ድንጋይ አልነበርም፡፡ ነገር ግን አልተሳካም፡፡ ጭራሽ ይሄ ብልጠቱ ብአዴንን አስኮርፎ ድጋፉን ለኦህዴድ እንዲሰጥ አድርጎታል፡፡ ህወሃት ብአዴን ላይ ሊጫወት ሴራ ሲያሴር ብአዴን ቀደመዉ፡፡ ምርጫዉ ከአንድ ቀን ያነሰ ጊዜ ሲቀረዉ ስለሆነ ደመቀ እራሱን ያገለለዉ ህወሃት ለፕላን ቢ እንኳን ጊዜ አላገኘም ነበር፡፡ የአስለቃሽ ጭስ ቦንብ እንደተወረወረባቸዉ ህወሃቶች ሰኞ ማታ እያለቀሱ ደመቀን ቢለማመጡም ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ህዋሀቶች አስካሁን እንደታመሙ ናቸዉ፡፡
2. የኦህዴድ አክቲቪስቶች
የኦህዴድ አክቲቪስቶች አላስፈላጊ ልመና ዉስጥ ገብተዉ ነበር፡፡ እንዲያዉም ምርጫዉ እየተቃረበ ሲመጣ ህወሃቶች ሽጉጤ እንደሚመረጥ እርግጠኞች ስለነበሩና ደ/ር አብይ አይመረጥም ብለዉ መረጃ ስላሾለኩ አክቲቪስቶቹ የብስጭትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ዉስጥ ገብተዉ ነበር፡፡ እንዲሁም አማራ በሌለበት ሰሙን የማንሳት ሁሉ ነገር ነበር፡፡
3. ብአዴን
ብአዴን 27 አመት ምክትል እየሆነ መጣ አሁንም በዛዉ መንገድ ቀጥሏል፡፡ አድሜ ልኩን እጁን እያነሳ ከራሱ አባል ዉጪ የሆነ ሰዉ እየመረጠ ዉስኪዉን እየተጋበዘ ይመጣል፡፡ በነገራችን ላይ የብአዴን ካድሬወች ራእይ እራሱ የላቸዉም፡፡ የሚያስቡት የሆነ ወረዳና ዞን ማስተዳደር ብቻ ነዉ፡፡ ክልል ከሄዱ በኋላ እንኳን ወደ ዞንና ወረዳ መልሱን እያሉ ሲለማመጡ ነዉ የሚዉሉት፡፡ አዲስ አበባ እማ ያማቸዋል፡፡ አዲስ አበባ ስብሰባ አለ በተባለ ጊዜ አብዛኛዉ የብአዴን አባል ይታመማል፡፡ መኪና ዉር ዉር የሚልበት አካባቢ ያጥወለዉላቸዋል አይመቻቸዉም፡፡ ነገ ብአዴንን የዉጮ ጉዳይ ሚኒስቴር አምጣ ብትለዉ ሰዉም የለዉም እሽ ብሎ የሚሄድም የለም፡፡ ዉጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሚሆን የፎገራ ወረዳ የብአዴን ሴል ቡድን መሪ ቢሆን የሚመርጥ ሽህ ብአዴን ነዉ ያለዉ፡፡
3. አባዱላ
አባዱላ በእርጅና እንደ ዠዋዠዌ እየተጫወተ ሳያምርበት ሊሞት ነዉ፡፡ ከነክብሩ እንደለቀቀ እዛዉ ጡረታዉን መዉጣት ሲችል ተመልሶ ለእነ ለማ እራስ ምታት ሆኖባቸዉ ነዉ የከረመዉ፡፡ አሁን ደግሞ ሽፈራዉና ሃይለማሪያም አሳስተዉኝ ነዉ ይቅርታ አድርጉልኝ እያለ ነዉ፡፡ ምናልባትም ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከሆነ በኋላ ግለሰቦች ላይ አላተኩርም ካላለ በቀር በሚቀጥለዉ ግምገማ ኦህዴድ የሚያባረዉ ሰዉ ቢኖር አባዱላ ነዉ፡፡ እሱ ብቻ አይደለም ዶ/ር አብይን መሄድ ባለበት እርቀት ሄዶ ዲፌንድ አላደረገዉም፡፡
4. ሽፈራዉ ሽጉጤ
ሁለቴ የደህዴን ምክር ቤት አልመርጠዉ ብሎ በህወሃት ትግል በጉልበት ሊቀመንበር በመሆን ጠቅላይ ሚኒስቴር ለመሆን ቋምጦ ቢመጣም ቂም የያዙበት የራሱ ድርጅት አባላት እንኳን ድምጽ አልሰጡትም፡፡
5. ዶ/ር ወርቅነህ
ኦሮሞ አይደለህም እየተባለ ከሱ ለተሻሉ ኦሮሞች ሲባል ሁሉ ምክትል ሊቀመንበርነትን እንዲያጣ ተደርጓል፡፡ እንዲህ ሁኖ ስራዉ እራሱ እንዴት እንደሚሰራዉ ግራ ይገባል፡፡ ለነገሩ ዉጪ ጉዳዩንም ዶ/ር አብይን ህወሃት አልቀበልም ካለ በኋላ ነዉ እንደ ሁለተኛ አማራጭ ቀርቦ የተሰጠዉ፡፡
6. በረከት ስሞን
በረከት በ17 ቀኑ ስብሰባ እነ ለማንና አብይን ለመከላከል ሞከረ፡፡ የቁርጥ ቀን ሲመጣ ግን ዶ/ር አብይ ከተመረጠ እኔ ኢህአዴግን ለማፍረስ ሌት ተቀን እሰራለዉ በማለት ዶ/ር ደብረጺወንን ጠቁሞም መርጦም ወጣ፡፡ በረከት እሳት ሲሉት ዉሃ-ዉሃ ሲሉት እሳት የሚሆን ሰዉ ነዉ፡፡ ዶ/ር አብይን አክርሮ በመቃዎም እንዲያዉም የወረደ ግላዊ ጉዳይ ሁሉ በማንሳት ከራሱ ከኦህዴድ ሰወች ጋር ሊቃቅረዉ ሞክሯል፡፡
7. የኦሮሞ ተቃዋሚ ድርጅቶች
ኦህዴድ አሁን የኦሮሞ ተቃዋሚዎችን አጀንዳ ሙሉን ይዞታል፡፡ የስልጣን ጥያቄ ነበር ህወሃትን አስገድዶ በመድፈር ወስዷል፡፡ የቋንቋ ጉዳይም እሰራበታለዉ ብሏል እሱንም በቅርብ አመታት ያስፈጽማል፡፡ የኦሮሚያ ህዝብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ቀስ በቀስ የኢኮኖሚ አዉታሮችን እየተረከቡ ስለሆነ የተሻለ ይሆናል፡፡ በተለይም የዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚኒስቴር መሆን በቀጥታ ለኦሮሞ ህዝብ ባይጠቅምም እንኳን ለማ በሚያገኘዉ ነጻነት፤ ጉዳዮችን በጓሮ በር ለማስፈጸም ቀላል ስለሚሆንለት፤ የህወሃት ጣልቃ ገብነትም ስለሚቀንስ የክልሉ ህዝብ የሚጠይቃቸዉን ጥያቄወች ቢያንስ አብሮ ስለሚያራግብ ተቃዋሚዉ ቦታ አይኖረዉም፡፡ ስለዚህም አንዳንድ አክቲቪስቶችና ተቃዋሚዎች ስራ አጥ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እንግዲህ ፒ.ኤች ዲ ጀምሮ ያቋረጠ እሱን መቀጠል፤ ሌላ ስራ ማፈላለግ ሳያስፈለግ አይቀርም፡፡
(መረጃ እና ፖለቲካዊ ትንታኔ ብቻ ነዉ የጸሃፊዉን የፖለቲካም ሆነ የግል አቋም አይግልጽም፡፡)