>
5:21 pm - Wednesday July 20, 3436

የኢህአዴጉን ልጅ ማረክነው እንጅ አልማረከንም ወሰድነው እንጅ አልወሰደንም  (ፋሲል የኔአለም)

እንደኛ ሆነ እንጅ እንደሱ አልሆንም። 

አንዳንድ ወገኖች “አብይ አህመድ አሁንም የኢህአዴግ አባል ነው፣ ዝም ብላችሁ አታሞጋግሱት” ይላሉ። ልክም ናቸው ልክም አይደሉም። አብይ አህመድ በአካሉ ኢህአዴግ ነው። በአስተሳሰቡ ግን ከኢህአዴግ ተለይቷል። በመንፈሳዊ ቋንቋ “ሪኢንካርኔት” አድርጓል ማለት ይቻላል፤ በነባሩ አካሉ ላይ አዲስ አስተሳሰብ አስገብቶበታል። የአብይ ድርጅት አሁንም ኢህአዴግ ነው ነገር ግን ዋናው ትግል የአስተሳሰብ ( የርዕዮተዓለም) እንጅ የድርጅት አይደለም። ከኢህአዴግ ጋር ያለው ጠብ እኮ ኢህአዴግ ለምን ተደራጀ የሚል አይደለም። ትግላችን ይህ ድርጅት በተበላሸ አስተሳሰብ አገሪቱን እየመራ በመሆኑ እንዲለወጥ ወይመ እንዲፈርስ ነው። አብይ ከዚህ የተበላሸ አስተሳሰብ ጋር መፋታቱን በንግግሩ አሳይቷል። አብይ አካሉ ከኢህአዴግ ጋር ቢሆንም መንፈሱ ግን ከነጻ አውጭው ጋር ነው። ሁለት ምሳሌዎችን ላንሳ። ህወሃት ኢትዮጵያን አፈራርሶ እንደገና በአምሳሉ ለመገንባት የሄደበት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ አብይ በንግግሩ አመላክቷል። የአገሪቱን ታሪክ ተቀብሎ በዛ ላይ መገንባትን ለመምረጥ መወሰኑን ገልጿል። ህወሃትን ጨምሮ ይህ ሁሉ ብሄር ተኮር ድርጅት የተፈለፈለው እኮ “ታሪክ ተበላሽቷልና ማቃናት እንፈልጋለን” በሚል ትርክት ነው። አብይ ይህንን ትርክት አምኖ በተቀበለበት ድርጅት ውስጥ ቢያድግም፣ ትርክቱ ኢትዮጵያን ሲያፈራርስ እንጅ ሲያድን ባለማየቱ፣ ከዚህ ትርክት ወጥቶ የኢትዮጵያን ታሪክ እንዳለ ተቀብሎ በዚህ ላይ መገንባትን መወሰኑን ገልጿል።   ይህ ሃሳብ ደግሞ የአንድነት ሃይሉ ሲያቀነቅነው የነበረው ነው። አብይ ወደ ተቃዋሚዎች አስተሳሰብ መጣ እንጅ፣ ተቃዋሚዎች ወደ አብይ አስተሳሰብ አልሄዱም። አብይ የተቃዋሚዎች አስተሳሰብ ምርኮኛ ሆነ እንጅ፣ ተቃዋሚዎች የአብይ አስተሳሰብ ምርኮኛ አልሆኑም፤ እነሱ ቀደም ብለው ለያዙት ሃሳብ ምርኮኛ ሊሆኑ አይችሉም።  አብይ አስተሳሰቡን በድርጅት ደረጃ ማስረጽ ከቻለ ደግሞ ኢህአዴግ ወደኛ መጣ እንናለን እንጅ እኛ ወደ ኢህአዴግ ሄድን ልንባል አንችልም። 

ተቃዋሚዎች ከልማት በፊት መብት ይከበር ወይም ሁለቱም ጎን ለጎን ይሂዱ እያሉ ሲጮኹ፣ ኢህአዴግ ልማት ከዲሞክራሲ ይቅደም ብሎ መብትን ሲረግጥ ቆዬ። በዚህ አስተሳሰብም አገራችን ከሁለት ያጣ ጎመን ሆነች። አብይ ከልማት በፊት ወይም ከልማት እኩል ዲሞክራሲም ያስፈልገናል የሚል ንግግር አቀረበ። ይህም አብይ በተቃዋሚዎች መማረኩን እንጅ ተቃዋሚዎች በአብይ መማረካቸውን አያሳይም። ኢህአዴግ የተቃዋሚዎችን አጀንዳ ቀምቷል ቢባል እንኳን፣ አብይም የአጀንዳ ነጠቃው ተባባሪ ሆኗልም ቢባል  እሰየው ይባላል እንጅ ሊወገዝ አይገባም፤ ዋናው ነገር አጀንዳውን ማን ያዘው የሚለው አይደለም። አጀንዳውን ማንም ያንሳው ማን፣ ትልቁ ቁም ነገር ተቃዋሚዎች የሚታገሉለት አጀንዳ መሬት ላይ ወርዶ ሲተገበር መታየቱ ነው። አንድ የመርህ ሰው ሊከተለው የሚገባው መርህም ይህ ይመስለኛል። ኢህአዴግ ዶ/ር አብይ የተናገራቸውን በትክክል የሚተረጉም ከሆነ፣ ከኢህአዴግ ጋር የሚኖረው ጦርነት የተለዬ ይሆናል። ጦርነቱ በሁለት ርእዮተ አለማት መካከል መሆኑ ቀርቶ በአንድ ርዕዮተ አለም ውስጥ በሚኖሩ ጥቃቅን ልዩነቶች ላይ ይሆናል ማለት ነው። ልክ እንደ ምዕራባውያን የፖለቲካ ስርዓት ማለት ነው። የምዕራባውያን የፖለቲካ ስርዓት መሰረታዊ በሚባሉት የሰውን ልጅ መብቶች በሚያስከብሩ ጉዳዮች ሁሉም ፖለተከኞች ስምምነት አላቸው። ልዩነታቸው በአብዛኛው ጥቃቅን በሆኑ መብቶችና የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ላይ ነው። መሰረታዊ በሚባሉት መብቶች ለምሳሌ ሃሳብን በመግለጽ፣ በመደራጀት ፣ በነጻ ምርጫ፣ በህግ የበላይነትና በመሳሰሰሉት ጉዳዮች ዙሪያ ሁሉም ፖለቲከኞች አስተሳሰባቸው አንድ ነው። ልዩነት ቢኖራቸው በግብረሰዶም ፣ በስደተኞች፣ በአንዳንድ ባህሎች ፣ በታክስና በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ነው። በእኛ አገር ግን በተቃዋሚዎችና በኢህአዴግ መካከል ያለው ገደል ሰፊ ነው። 

ኢህአዴግ ቆዳው እንጅ ውስጡ እኮ ኮሚኒስት ነው። ስልጣን ወይም ሞት የሚል ድርጅት ነው። ተቃዋሚዎች በተቃራኒው በነጻ ምርጫ ያልተገኘ ስልጣን አፈር ድሜ ይብላ የሚሉ ናቸው። በአጭሩ ምዕራባውያን ባረጋገጡዋቸዉ መሰረታዊ በሚባሉት መብቶች ዙሪያ ስምምነት የለም፤ አልተከበሩምም። ተቃዋሚዎች እነዚህ መብቶች በቅድሚያ ዋስትና እንዲያገኙ ይፈልጋሉ። እነዚህ መሰረታዊ መብቶች ከተከበሩ፣ ፍትጊያው በጥቃቅን መብቶች ላይ ይሆናል። አብይም እነዚህን ሁሉንም የሚያስማሙትን መብቶች እንዲከበሩ እጥራለሁ ብሎአል። በዚህ አነጋገሩም የተቃዋሚዎች አስተሳሰብ ምርኮኛ መሆኑን አረጋግጧል። ቅዱስ ምርኮኛ መሆን ደግሞ ሃጢያት አይደለም። ዋናው ጥያቄ በኮሚኒስቶችና ዘረኞች የተከበበው ይህ ሰው የተናገረውን መሬት ላይ ይተገብረዋል ወይ የሚለው ነው። በዚህ ጥያቄ ላይ መወያየቱ ትክክልም ተገቢም ነው። ከዚያ ውጭ ግን አብይ ኢህአዴግ ስለሆነ አታሞግሱት የሚለው አባባል፣ በመርህም ይሁን በስትራቴጂ ደረጃ ትክክል አይደለም። በአንድ በኩል አብይ የተናገረውን እንዲተገበር እየነዘነዝክና እያስገደድክ በሌላ በኩል ደግሞ የዛገውና የማይለወጠው የህወሃት/ኢህአዴግ ነባር አመራር እንዲወገድ እየጠየቅክ ትግልህን ብታፋፋም ታተርፋለህ እንጅ አትከስርም።

 የመጽሃፍ ቅዱሱ የጳውሎስ ታሪክ ከአብይ ሁኔታ ጋር የሚመሳል ነገር አለው። ጳውሎስ የተባለው ሳውል እየሱስ ክርስቶስን የሚደግፉትን ሁሉ በማሳደድ ይታወቅ ነበር። በእየሱስ ማመን ሲጀምርና ሲሰብክ የእየሱስ ደቀመዛሙርት ሳይቀሩ ፈሩት። አላመኑትም። እምነቱን በተግባር ማሳየት በጀመሩ ግን በመጨረሻ ብዙ ተከታዮችን አፈራ። መጽሃፉ እንዲህ ይላል “ ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት።” ዶ/ር አብይም በንግግሩ የኛን ሀሳብ ይደግፋል፤ በምግባሩ ደግሞ ከኛ መሀል እንዳለ እንደ አንድ ሰዉ እንድንቀበለዉ ደግሞ እንደ ጳውሎስ በተግባር እስኪያሳየን እንጠብቃለን።

Filed in: Amharic