>
5:18 pm - Saturday June 16, 0356

የህወሐት "ክልል" ለወልቃይት ጠገዴ ጥፋት ወይስ ልማት!!  (ከመኮነን ዘለለው-- የቀድሞ የህወሓት አባል) 

ወልቃይት ጠገዴ ክልል የሚባል አስተዳደር ሳይፈጠር በጎንደር ክፍለ ሀገር ውስጥ የሚተዳደር ህዝብ ነበር። ወልቃይት አማርኛ እና ትግርኛ የራሱ ቋንቋ በማድረግ ሀሳቡ ባህሉ ማንነቱ የሚገልጽባቸው ቋንቋዎቹ ናቸው። ሁለቱ ቋንቋዎች ለወልቃይት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽ ናቸው ቢባል ስህተት አይደለም። ዛሬ ግን በህወሐት/ኢህአዴግ ስርዓት ዘመን አገር በቋንቋ የተከለለበት ጊዜ በመሆኑ ትልቅ ችግር ገጥሞታል “የትግርኛ ቋንቋ ስለምትናገር ወደ ትግራይ ተከልለህ የትግርኛ ቋንቋ የስራ ቋንቋ አድርገህ ትኖራለህ” ተብሏል የወልቃይት ህዝብ ትግርኛ ቋንቋ ይናገር እንጂ ትግራይ ነኝ ብሎ አያምንም የትግራይነት ስሜት የለውም።
 .
ከሁሉ በላይ የሚሰማው ኢትዮጵያዊነት ስሜት ነው። እንደ ወልቃይቴ የሚጠቀመውም አማርኛ እና ትግርኛ ነው ሀዘኑም ደስታውም ወኔውም የሚገልጸው በነዚህ ቋንቋ ብቻ ነው። አማርኛ በተለይ ለወልቃይት ህዝብ የኢትዮጵያዊነት ምልክቱ ነው። የሥራ ቋንቋው አድርጎ ለዘመናት እየተጠቀመ የኖረ ህዝብ መሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ምስክሩ ነው። አንዳንድ ትግርኛ የሚናገሩ የትግራይ ሰዎች ”የወልቃይት ህዝብ ትግርኛ እየተናገረ ለምን ትግራይ አይደለንም ይላል?“ በማለት ይጠይቃሉ። የህወሐት ድርጅትም ስህተት ከዚህ ስለሚነሳ የጥያቄው መልስ በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል። መልሱ አንድ እና አንድ ነው። የወልቃይት ህዝብ ትግርኛ መናገሩ እንጂ ትግራይ ነኝ ብሎ አያምንም የትግራይነት ስሜት የለውም ይህ አሻሜ የማያስፈልገው አራት ነጥብ ነው።
.
የህወሐት ድርጅት የስህተት መሰረት የወልቃይት ህዝብ ትግርኛ ስለሚናገር ትግራይነኝ ብሎ እንኳ ባያምንም ባይቀበልም የግድ ትግራይ ነኝ እንዲል ማስገደድ ወደ ትግራይ ክልል ማስገባቱ ነው። አንዳንድ አማርኛ ተነጋሪ ሰዎች የወልቃይት ህዝብ የሚናገረው አማርኛ ነው ከአንዳንድ ትግርኛ ተናጋሪ ስደተኛ አግኝተው የሚናገሩ ጥቂት በተከዜ አካባቢ ሊኖሩ ይችላሉ የሚሉ አሉ። ይሄ አገላለጽ የወልቃይት ህዝብ ለሚያወቅ ስድብ ነው። ወልቃይቴ የተባለ እዛ ተወልዶ ያደገ በሙሉ ትግርኛ የማይናገር የለም። ወልቃይት አማርኛ እንጂ ትግርኛ አይናገርም ማለት በግልባጭ ካየነው ይህ አባባል ህወሕት ድርጅት ወይም የሱ አሽከር ብአዴን ከሚለው አይለይም። የዚህ ህዝብ ችግር የጌታ ምርጫ አይደለም የመብት የነጻነት ፍላጎት ነው።
.
ወልቃይቴ ሲናገር የኔን ልጅ አንድ አማራ አገባት መለስ ብሎ ደግሞ የእከሌን ልጅ እኮ አንድ ትግሬ አገባት ሲል ይሰማል እስቲ የትኛው አማራ ነው እንዲህ የሚለው።ደግሞስ የትኛው ትግራይ ነው ይህ ዓይነት አነጋገር ያለው? ይሄ ህዝብ ከሁለቱ የለም። ይህ ማለት ከሁለቱ ህዝብ ጋር ተፋቅሮ ተዋዶ መኖር አይፈልግም ማለት አይደለም። ይሄ ህዝብ እንደ ወልቃይቴ ሁለቱን ቋንቋ የራሱ አድርጎ የወሰደ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ የኖረ ህዝብ ነው። ከሁለቱ ቋንቋ አንዱን ጣል ቢባል የማይቀበል ህዝብ እንደሆነ እዛ መሬት ያለ ሁኔታ የሚመሰክረው ሃቅ ነው። ይህ ህዝብ ሁለቱን ቋንቋ እየተጠቀመ ለዘመናት በጎንደር ክፍለ ሃገር ስር ነበር። ጥያቄው እንደ ለመድኩት ልኑር ተውኝ ነው።
.
ባጠቃላይ ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ማሳሰብ የምወደው በዚህ ህዝብ ላይ ክልል የሚባል መስተዳደር የህዝቡ ታሪክ እና ባህል አስተሳሰብ ግምት ውስጥ ሳያስገባ በተጽዕኖ ወደ ማይፈልገው ክልል እንዲገባ መደረጉ ነው። የወልቃይት ህዝብ የፈለገውን ቋንቋ እየተናገረ እየጻፈ ኢትዮጵያዊ ሆኖ እንዳልኖረ አሁን “ኢትዮጵያዊ ለመሆን በመጀመሪያ ትግራይ” መሆን አለብህ ተብሎ ከባድ ችግር ደርሶበታል። ይህን የመሰለ አካሄድ እና አሰራር በታሪኩ ውስጥ ለዚህ ህዝብ የመጀመሪያ ነው።
.
ይህ ህዝብ እንደ ወልቃይቴነቱ በኢትዮጵያዊነቱ ኮርቶ ሁለቱን ቋንቋ እየተጠቀመ ሲኖር የግድ ትግራይ ሁን ወይም አማራ ሁን ብሎ የጠየቀውና ያስገደደው መንግሥት አይቶም ሰምቶም አያውቅም ነበር። ያልሆነውን ሁን በመባሉ ተቸግሯል በጣም አዝኗል ተቀይሟል ቢናገርም ሰሚ የለም። እንዲያው በጥቅሉ ”የለህም እንዳንል ይመሻል ይነጋል አለህም እንዳንል እንዲህ ይደረጋል” በማለት እንባውን ወደ ወጭ ሳይሆን ወደ ውስጥ እያለቀሰ ይገኛል። የህወሐት ድርጅት ካድሬዎች የዚህ ህዝብ ችግር እያወቁ ለችግሩ መፍትሔ መስጠት ሲገባቸው ማንነቱን እንዲጠፋ ሆነ ተብሎ እየተሰራ እንዳለ ከዚህ ባታች ያለውን ዝርዝር ሐተታ መመልከቱ ይበቃል። የወልቃይት ህዝብ የሚኖርበት መሬት ደጋ ቆላ መዘጋ ተብሎ የተከፈለ ነው።
.
ደጋውና ቆላው መሬት በእርሻ ያለው ገቢ እንኳ ትንሽ ቢሆን ለሰው ልጅ ምቹ የሆነ የአየር ጠባይ ያለው። ተናዳፊ የወባ ትንኝ የሌለበት ስለሆነ ዘጠና አምስት ከመቶ የሚሆን ህዝብ በዚህ አካባቢይኖራል። ሌላው ጥቁር መሬት እያለ የሚጠራው መዘጋ ነው። ይሄ መሬት ከመዘጋ ዛሬማ ወንዝ እስከ አንገረብ ወንዝ ባህረሰላም ድረስ የተዘረጋ ነው። ዝቅተኛ በጣም ሙቀታማ ተናዳፊ የወባ ትንኝ የበዛበት ስለነበረ ህዝቡ ከመዘጋና ቆላማ ቦታ እየመጣ የሚጠቀምበት ሰፊ ለም መሬት ነው። ይህ መሬት ለወልቃይት ጠገዴ የጀርባ አጥንት ነው ቢባል ፍጹም ሀቅ ነው። በዛሬ ጊዜ የወባ ትንኙ ስለ ጠፋ የህዝቡ ብዛትም እየጨመረ ስለሄደ የዚህ መሬት አስፈላጊነት ወሳኝ ነው።
.
ይህ ህዝብ የዚህ መሬትና የሑመራ ሜዳ እርሻ ባለቤት በመሆኑ ዕድለኛ ነበር ተሰዶም አያውቅም ነበር። ዛሬ ግን ጉድ ፈላበት መሬቱ አስረክቦ እንዲጠፋ ተወሰነበት። እሱም በስንት ችግር አልምቶ ጠብቆ ያቆየውን መሬት በሰፈራ እና በፋብሪካ እንዱስትሪ ልማት ስም ለሌላ ያላንዳች ክፍያ እና ጥቅም እየተሰጠ ባለ መሬት የሆነውን ህዝብ የሚኖርበት አካባቢ ለቆ እንዲበተን እንዲጠፋ ወደ ጋምቤላ ሂድ እየተባለ ኢኮኖሚው መንምኖ ድሀ እንዲሆን ተፈርዶበታል። ማንም ኢትዮጵያዊ በወልቃይት ጠገዴ ህዝብ እየደረሰ ያለው ግፍ ከዚህ በታች በዝርዝር መመልከት ይቻላል፦
.
የህወሐት ካድሬዎች የትግራይን ህዝብ አርሰው ከሚበሉበት ማህል ለሰፈራ ብለው ኑ የበለጠ ሰፊ ለም መሬት እንሰጣችሁ አለን በማለት በወልቃይት መዘጋ ለም ጥቁር መሬት እስከ አንገረብ ወንዝ ባህረ ሰላም ድረስ ያሉ ቦታዎች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ እንዲሰፍሩ አድርገዋል። ከድርኩታን መጉ እስከ ዛሬማ ወንዝ ባለው ሜዳ ጥቁር መሬት ሲኖር የነበረው ያገሬው ሕዝብ ከድርኩታን እስከ ጽልዕሎ እንደ ሰንሰለት በተያያዙት ከፍተኛ ቦታዎች ስር ግርጌ ለም መሬቱን ለቆ እንዲንጠለጠል ተደረገ። ይህ ህዝብ ከዛ የለማ መሬት ላይ እንዲለቅ የተደረገው ለስኳር ፋብሪካ ኢንዱስትሪ መስፋፋት ተብሎ ነው። ይሁን እንጂ በዚህ ሜዳ ማይ ጋባና ዋልድባ አካባቢ የስኳር ፋብሪካ ቦታዎች የተባሉ ሳይጨምር ባለው ሜዳ ልቀቁ ተብለው ተራራ እግር ስር የተንጠለጠሉት እንዲ መለሱ ማድረግ ሲገባ፤ ሌላ ሕዝብ ከትግራይ ማህል አምጥተው 150,000 እስከ 200,000 ህዝብ ከዛሬማ ወንዝ እስከ መጉእ ባለው ለም ጥቁር መሬት መዘጋ በወልቃይት ሕዝብ ላይ አስፍረዋል።
.
ከዚህ በላይ ያለው እንደ ተገለጸው ሁኖ 2ኛ ከማይተመን እስክ አንገረብ ወንዝ ባህረ ሰላም ድረስ የሰፈረው ሕዝብ በጠቅላላ 206,000 ይሆናል። በዚህ ለም መሬት የሰፈረውሕዝብ ለአንድ ቤተሰብ ቢያንስ ከሁለት እስከ 4 ካሬ መሬት እየተሰጠው እንዲሰፍር ተደርጓል። ዝርዝሩ እነሆ
.
ተ.ቁ —— ቦታ —————– የሰፋሪው ብዛት
1. ማይተመን እና ማይቀይሕ———- 22,000
2. ምግላብ ፈረስ እና ዓድጎሹ አከባቢ— 21,000
3. እንዳይቀዳሽ እና ግይጽ አከባቢ—— 30,000
4. ደጋጉም እና ዘርባቢት አከባቢ——- 25,000
5. ዕድሪስ እና ጎብለል አከባቢ——— 40,000
6. ባዕከር እና ላዕላይ ሩዋሳ አከባቢ—- 18,000
7. ከህወሐት የተባረሩ ታጋዮች ድቭዥን
እየተባለ በሚጠራው ስፍራ ———— 30,000
8. ማይደሊ እና ለዕለይ ሰረቋ አከባቢ——9,000
9. መኮዞ እና ተሐናነቅ አከባቢ———–11,000
ጠቅላላ ድምር——————–206,600
.
3ኛ. ከዚህ በላይ የተጠቀሰው ሳይ ጨምር በሑመራ አካባቢ ሜዳ ለም መሬት ላይ የሰፈሩ ደግሞ እንደሚከተለው ተመልከቱት:
.
ተ.ቁ ——-ቦታ——————የሰፋሪው ብዛት
1. እንዳ ኳጃ አካባቢ—————-18,000
2. ማይ ካድራና አካባቢ————-.45,000
3. ሮደም————————-.15,000
4. በረከት————————-20,000
5. ላይ መቻች———————10,000
6. ታች መቻች———————–5,600
7. ሸለላ—————————10,000
8. ሸሪፋ ሐማድ———————-5,000
9. ታች ሩዋሳ————————5,000
10. ማይሰገን ባህረሰላም ግጨውና
ገረር ውሃ አካባቢ——————–15,000
11. ዓብደል ራፊዕ እና አከባቢዋ———2,000
 ጠቅላላ ድምር—————150,600
.
በወልቃይት ጠገዴ ለም መሬት የሰፈረው ሕዝብ በጠቅላላ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ እንደሆነ ዝርዝሩ ያሳያል። በሌላ በኩልም በጥቂቱ ለመግለጽ ከዋልድባ የሱካር ፋብሪካ በተጨማሪ የሕይወት እርሻ መካናይዝድ በሑመራ አከባቢ የያዘው መሬት 640 000 ሄክታር እንደሆነ ይታወቃል። ሌላም ብዙ መሬት በህወሐት ድርጅት የተነጠቀ እንዳለ መጥቀስ ይቻላላል።
.
እንግዲህ ከወልቃይት ጠገዴ ለም መሬት ተወስዶ ለእርሻ አገልግሎት ተሰጥቶት የሰፈረው ህዝብ በጠቅላላ ከግማሽ ሚልዮን በላይ ይሆናል። ይህ የህዝብ ቁጥር በግምታዊ ጥናት የተገኘ ስለሆነ የሰፋሪው ቁጥር ሊያንስም ሊበዛም ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን ያህል ሰፋሪ በወልቃይት ሕዝብ ላይ ማፍሰስ ዓላማው ምን ይባላል? አንድ ህዝብ አጥፍተህ በቦታው እንዴት ሌላ ህዝብ አምጥተህ እንዲሰፍር ታደርጋለህ? መሬቱ ነው እንጂ ህዝቡ አይፈለግም ማለት ነው? ምንስ አደረገ? መብቴ ይከበር፣ ድምጼ ይሰማ በማለቱ መልሱ ይሄ ነው ወይ? የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ሁሉ ይህንን ተግባር እየተፈጸመበት ዝም ብሎ መጥፋት የለበትም ለህልውናው መታገል አለበት። በቅርብ ጊዜ በጎንደር የተደረገው እንቅስቃሴ የሚያበረታታ ነው። መቀጠል አለበት ብልጭ ብሎ ተመልሶ የሚጠፋ መሆን የለበትም። ቁጭ ብሎ መምከር መደማመጥ ያስፈልጋል። ማንም ወልቃይቴ የተለየ የፖለቲካ ድርጅት ተቋም ደጋፊም ወይም ገለልተኛ ሊሆን ይችላል ነገር ግን በወልቃይት ጠገዴ ላይ የሚደርሰውን ችግር እቃወም አለሁ መታረም አለበት ብሎ እስካመነ ድረስ ባለው አቅም እንዲሳተፍ ማድረግ ተገቢ ነው እላለሁ። የህወሐት አባል ነን የምትሉ የወልቃይት ጠገዴ ሰዎች በህዝባቹህ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ተገንዝባቹህ ድርጅታቹህን ህወሐት እንዲያስብበት መጎትጎት አለባቹህ። እንደ የድርጅት አባልም እኮ የህዝባቹህ ችግር በደል አቅርባቹህ ለማስፈጸም ትክክለኛ መልስ ለማግኘት መጋፈጥ አለባቹህ የተበደለው ህዝብም ከናንተ ጋር ይቆማል።
 .
የትግራይ ህዝብም በተለይ ይህ ድርጅት ሰላም ብልጽግና የሃገር አንድነት እኩልነት ያመጣል ብለህ በማመን ያለህን እስከ ሕይወትህ ድረስ ሰጥተህ እዚህ እንዳደረስከው ከማንም ይበልጥ አንተ ታውቀው አለህ ስለዚህ የተመኘኸውን አላገኘህም። አሁንም ከመከራ ከስደት አላመለጥክም ሰላም የለህም አገር ተቆርሷል ኢትዮጵዊነትህ አንድነትህ እየተናደ ነው በስምህ እየተነገደ ነው ተጨቁነሃል ከጭቁኖች ጋር ቁም ተነስ ትብብርህ አስፈላጊ ነው። ለሰፈራ በህወሐት ድርጅት መጥታቹህ የሰፈራቹህ ሁሉ ህዝብ አጥፍቶ ህዝብ ማኖር አይቻልም ይህ ጸረ ህዝብ ድርጊት ነው በወልቃይት ህዝብ ጫንቃ ላይ እንደሰፈራቹህ ተገንዝባቹህ የህወሐት ድርጅት እንኳ ስህተቱን ቢሰራው ትክክል እንዳልሆነ ህሊናቹህ ይገንዘብ። የተሰጣቹህ መሬት ሕይወታቹህ እንዳልቀየረው ግልጽ ነው እና የህወሃት ድርጅት ከፋፍለህ ግዛ ተቃውማቹህ ከወልቃይት ህዝብ ጎን እንድት ሰለፉ ህዝቡ ጥሪውን ያቀርባል።
.
በጠቅላላ ለኢትዮጵያ ህዝብ በወልቃይት ጠገዴ ላይ የደረሰው ችግር ክልል የሚባል ሕወሐት/ኢህአዴግ ያመጣው አሰራር ነው። በወልቃይት ጠገዴ እየደረሰ ያለ ችግር በጣም ከባድ ቢሆንም ክልል ያመጣው ጣጣ ግን በሞላው ኢትዮጵያ እያጋጨና እየበተነ ያለው ችግር መሆኑ ግልጽ ነው። ለምሳሌ በወለጋና ጎጃም በኦሮሞ እና ሶማሌ በዓፋርና ሶማሌ በትግራይና በዓፋር በትግራይና በወልቃይት ጠገዴ በትግራይና ሰሜን ጎንደር ወሎ በጋምቤላ በቤንሻንጉል ወዘተ ችግሩ ሲከሰት ይታያል። በቋንቋ ብቻ አገር መከፋፈል እየጠቀመ ያለው ለጠባቦችና ብሎም ኢትዮጵያ አገራችን ለመበታተን ለሚፈልጉና በውጭ ጠላቶቻችን ለሚታለሉ ሃይሎች መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ስለዚህ የወልቃይትጠገዴ ህዝብ ጥያቄ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ነው።
.
ህዝብ ሁሉ እጁን ያንሳ! ይተባበር የተባበረ ህዝብ ያሸንፋል።
Filed in: Amharic