>

«ኢትዮጵያዊ ነኝ» በማለታቸው «አማራ ነህ» ተብለው  ግፍና በደል የደረሰባቸው ጉራጌው አሊ ሁሴን (አቻምየለህ ታምሩ)

መቼም ከፋሽስት ጥሊያን ዘመን ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በጠላትነት ተፈርጆ ግፍና ግድያን በላዩ ላይ ተሸክሞ የኖረው የአማራ መከራ ተቆጥሮ አያልቅም። በርግጥ  ይህንን ሁሉ በደልና መከራ ተሸክሞ  የኖረው ይህ  ታላቅ  ህዝብ  ዛሬ  ላይ በነቂስ ተነስቶ  እየተጋደለ ይገኛል።
አቶ አሊ ሁሴን ካናዳ የሚኖሩ  የጉራጌ ተወላጅ ናቸው። የኢህአፓ ታጋይ ሳሉ  «አማራ ነህ» ተብለው የአማራን ግፍና በደል ተቀብለዋል። አቶ አሊ  ይህንን ግፍና በደል  ዶክመንተሪ   ሰርተው፤ መጽሀፍ ጽፈው፤ በተለያዩ ቦታዎችም  ንግግር  በማድረግ  ለአለም ሁሉ  አሳውቀዋል።
እነ መለስ ዜናዊ  ሞቃድሾ ጽህፈት ቤት  ከፍተው ኢትዮጵያን ሲያጠቁ  በሲያድ ባሬዋ ሶማሊያ እስር ቤቶች ውስጥ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይና አማርኛ አስተርጓሚ ሆነውም  ይሰሩ ነበር።   አቶ አሊም   ከደርግ  እስር  ሸሽተው ወደ ሶማሊያ  ተሰደው  ሚቃዲሾ  እስር ቤት በገቡበት ወቅት  በነመለስ ዜናዊ  ጥቆማ  «አማራ ነህ»  ተብለው በተለየ እስር ቤት እንዲታሰሩ ተደርገው  የተፈጸመባቸውን ግፍ፤  በሌሎች «አማራ ናቸው» በተባሉ ላይ የተካሄደባቸውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ፤  በሴት እህቶቻችን ላይ የደረሰውን ከአእምሮ በላይ የሆነ ዘግናኝ ጭካኔ ዝርዝር በሰሩት ዶክመንታሪና በመጽሀፋቸው  ነግረውናል። በተለያየ ጊዜ በሰጡት ቃለ መጠይቅም  አቶ አሊ ሶማሊያ ውስጥ «ሸለምቦት» በተባለ ቦታ «የአማራ» ተብሎ በተከለለው እስር ቤት ውስጥ ስለተፈጸመው ግፍ ዛሬም ድረስ ህመሙ እየተሰማቸው  ይናገራሉ።
እኒህ የአማራ ባለውለታ ላለፉት ሰላሳ በላይ አመታት  ስለ አማራ ሲጮሁ  ኖረዋል።   ከነቤተሰቦቻቸው  በአማራ ላይ የተፈጸመውን ግፍና በደል  ተናግረው አይደክሙም!  «ኢትዮጵያዊ ነኝ» በማለታቸው «አማራ ነህ»  ተብለው የደረሰባቸው ግፍና በደል የአማራ ድምጽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል! በየተገኙበት መድረክ ሁሉ አጥንታቸው ድረስ የሚሰማቸውን የአማራ ግፍና በደል ከፍ አድርገው ይናገራሉ! በደልና ግፍ የህይወቱ  ገጽታ የሆነው አማራ ይነሳ ዘንድም  ከአመታት  በፊት እንዲህ  ሲሉ ተቀኝተዋል፤
የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ ነበረ ተረቱ፣
ምነዋ ዘንድሮ ተወጊው ሲረሳ ወጊ አለመርሳቱ፤ 
ከዚያም አልፎ ተርፎ የተወጊው ጉዳይ የከበደው ነገር፣
በደሉን ረስቶ የወጋውን ጩቤ ልሶ ስሞ ማደር! 
አቶ አሊ  ዛሬም ስለ አማራ መናገራቸውን አላቆሙም። ባለፈው ለንደን ላይ  በአንድ መድረክ ተገኝተው ”እንቁፍቱ” እና ”ፈርዶበት አማራ!”  በሚል ያቀረቧቸውን ግጥሞች  ከታች አትሜያቸዋለሁ። «እንቁፍቱ»  ሐረር ውስጥ አማራ ከነነፍሱ  የተጣለበት የማይሞላ ገደል ነው።
ክብር ለታላቁ ኢትዮጵያዊ  ለአቶ አሊ ሁሴን! አቶ አሊ  ድምጽ አልባ ለሆነው ወገንዎ  ስላደረጉት ሁሉ  ከመቀመጫየ ተነስቼ  ረጅም እድሜና ጤና  አላህ ይሰጥዎት ዘንድ በጸሎት የሚታገዝ ምኞቴን እገልጽልዎታለሁ።

https://m.facebook.com/story.php?story_fbid=1264711803550766&id=100000358765743

Filed in: Amharic