>
5:13 pm - Wednesday April 19, 5995

ዶ/ር አብይ አህመድ  በ‹ፈርዖን› ፊት (እንዳለጌታ ከበደ)

    ከአንድ ዓመት በፊት፣ ‹እርካብና መንበር› በሚል ርዕስ፣ ‹ዲራአዝ› በሚል ደራሲ  ስም  የወጣ መጽሐፍ ላይ እንዳነበብነው፣ መሪነት ድንገት ላያችን ላይ የምንጭነው አክሊል፣ ወይም እግረ መንገዳችንን እንደ ዘበት አንስተን የምናጠልቀው ቆብ መሆን የለበትም ፡፡ስንመኘው፣ ስንጠብቀው፣ በትንሹ ስንለማመደው የነበረ፣ ለራሳችን የምናበረክተው፣ የምንፈተንበት፣ እኛን ብሎ የሚመጣው አሳር እንዲያርሰን የማንፈቅድበት፣ በገባነው ቃል ልክ ለማስተዳደር የምንሟገትበት መሳርያ ነው፡፡ ቁልፍ ነው፡፡
      እንዲህ ይላል – መጽሐፉ፡፡ ‹‹ መሪ መሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ‹ከዕለታት በዚህ ቀን መሪ እሆናለሁ› ከሚል የቅዠት እስር ቤት መውጣት አለበት፡፡ ምክንያቱም ከዕለታት አንድ ቀን የሚባል ቀን የለም፡፡ በህይወት ውስጥ የተሰጠችን እምር ዕድሜ ዛሬ፣ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ እንጂ ከዕለታት አንድ ቀን አይደለም፡፡…እነዚህ (መሪ መሆን የሚፈልጉ) ሰዎች መሪ ለመሆን የግድ ምርጫን አይጠብቁም፡፡ አዳዲስ ልምዶችን ሀሳቦችን በማፍለቅ ሌሎች ሊከተሉት የሚፈልጉት ዓይነት ሰው ሆነው ይገኛሉ፡፡ ገና መሪ ከመሆናቸው በፊት ራሳቸውን እንደ መሪ ይቆጥራሉ፡፡…ሌት ያለ ሃሳብ ሲኖርህ እነዚህን ሃሳቦች ዕውቅና እንዲያገኙ ለማድግ ሚዲያዎችን ተጠቀምባቸው፡፡…የመሪ ህይወት እንኳን ወደ ትግሉ መጣህ በሚል ተጀምሮ ጉዞውን መጨረስ በመቻልህ እድለኛ ነህ በሚል ማሳረጊያ  የሚገባደድ ነው፡፡››
         እንደኔ እምነት፣ ‹እርካብና መንበር› ውስጥ እንደምናገኘው ሃይማኖታዊ  ምሳሌ፣ አቢይ አህመድ (ዶክተር)ና መሰሎቻቸው በምሳሌው መሰረት፣ የሙሴን  ባህርይ እየኖሩትና ነገ ከነገ ወዲያም ሊኖሩት  የሚመኙት ይመስለኛል፡፡ ሙሴ  ፈርዖን  ቤት ያደገ  ጉብል ነው፡፡ የወገኖቹን መበደልና  መገፋት ያስተዋለ፣ አስተውሎም የተንገሸገሸ ነው፡፡ ሙሴ  ከሩቅ የመጣ አይደለም፡፡ የሆነ መታደስ፣ መለወጥ  ያለበት ነገር እንዳለ የገባው ከሩቅ ሆኖ አይቶ አይደለም፡፡ እዚያው ሆኖ ነው – የፈርኦን አገዛዝ መበስበሱን፣ ቋቱ  በዘረኝነት  መሞላቱን፣ በመወነጃጀል፣ የራስን ጥቅም በማሳደድ ላይ የተመሰረተ  መሆኑ የተገነዘበው፡፡
        ሙሴን ሙሴ ያደረገው አሮን ነው፡፡ የሁለቱ መተባበር ፈርኦንን አስጎንብሶታል፤ መንገዱን አስለውጦታል፤ ፈርኦኑ የማይቻልና የማይደፈር በመሰለው ድልድይ ላይ ተመላልሶበታል፡፡ ሁለቱ የነጻነት አርበኞች እጅ ለእጅ ተያይዘው፣ ወገኖቻቸውን ከበደል አረንቋ እንዲወጡ አድርገዋል፡፡ ይህ ማለት ግን ከባርነት ነጻ እንዲወጡ ያደረጓቸው ወገኖቻቸው፣ እስከመጨረሻው ድረስ በመፈንደቅ ብቻ ተከተሏቸው ማለት አይደለም፡፡ የቀደመ ባርነታችን ይሻለን ነበር ያሉ፣ ያጉተመተሙ፣ የጥላቻ ፊት ያሳዩ ነበሩ፡፡
         ዶክተሩ ሕወሃት ኢህአዴግ እግር ስር ሆነው፣ የአገዛዙን  መሻገት ብቻ ሳይሆን፣ አየሩ  መለወጥ፣ መታወክና መታጠን እንዳለበት መገንዘባቸውን ያስገነዘቡን፡፡ የተበከለው በዘረኝነት መሆኑ ሲነገር የቆየ ነው፡፡ ራስን የማስቀደም፣ የሌላውን ሕመም ለመታመም ዝግጁ ያለመሆን ክፉ በሽታ ነው፡፡ ‹በሀገሪቱ ውስጥ ቁጥር አንድ ተበዳይ እኔ ነኝ!› የሚል የከሳሽነት ስሜት ነው፡፡ ይህን አየር የሚያጸዳ ሙሴ እንደሚጣ ስንመኝ ነበረ፡፡ ምኞታችን ተፈጻሚ እንዲሆንም ተስፋ ስናደርግ ነበረ፡፡ አሁን ያሉት ወጣት አመራሮች፣ ቀደም ሲል የጀመሩትን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙት አጠናክረው እንደሚገፉበት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
      የለውጡ ደወል መሰማት አለበት፡፡ነበረበትም፡፡ Steven Grosby የተባለ ተመራማሪ ‹NATIONALISM› በተሰኘ መጽሐፉ፣ ልማዶች ይሻራሉ፤ የሻገቱት ይጣላሉ፤ ቀደም ሲል ለዘመናት ዕውቅና የተሰጣቸው አሰራሮች፣ ሁነቶችና ክዋኔዎች ሁሉ ቦታ ይነፈጋቸዋል ብሏል፡፡ይህ እንዲሆን ደግሞ ሰው ይፈልጋል፡፡ሰው ማለት ሰው የሆነ ነው ሠው የጠፋ ዕለት፡፡ እሳቸው ቦታውን ስለፈለጉት ብቻ ሳይሆን፣ ቦታውና ዘመኑ እንደሳቸው ያለ ሰው ይፈልግ ስለነበረ ነው፣ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በዓለ ሲመት ሰሞን ደስተኞች ሊበዙ የቻሉት፡፡ መንበሩና መሪው ስምሙ ሲሆኑ ነው፣ የተከረቸሙ በሮች የሚከፈቱት ተብሎ ስለሚገመት፡፡ መዝረክረክ ነበረ፡፡ ሁከት ነበረ፡፡  እናም፣ሕይወት ተፈራ፣ Tower in the sky/ ‹ማማ በሰማይ› በሚለው መጽሐፏ እንደገለጸችው፣ ‹እረብሻና ግርግር በተፈጠረ ቁጥር አንድ መሪ ብቅ ማለቱ  የማይቀር ነው፡፡›
     ከቅርብ ጊዜ ወዲህ፣ እኔ እንዳስተዋልኩት፣ አዳዲስ ነገሮች እየተደመጠ ያለው ከወጣቶቹና ከትጉሃኑ የኦህዴድ አመራሮችና ከአንዳንድ የብአዴን አመራሮች አንደበት ነው፡፡ ሌሎቹ  አሁንም በነባሩ የ‹ታጋዮች መንፈስ› ነው የተሞሉት፡፡ አዲሱን ትውልድ አያውቁትም፡፡ ከዘመኑ ጋር እኩል መራመድ አልቻሉም፡፡ ከሚተቹባቸው ጉዳዮች ጋር ተላምደዋል፡፡ አሁን የሚደነግጥ መሪ ያስፈልገናል፡፡ የሕብረተሰቡ ድንጋጤ የሚጋባበት፡፡ ተጋብቶበትም መፍትሔ የሚያመጣ፡፡ ወይም መፍትሔ አመጣለሁ ብሎ ቃል የሚገባ፡፡
ሙሴ ፈርኦን ፊት በቀረበ ቁጥር፣ መልሶ መላልሶ የሚናገረው፣ ‹ሕዝቤን ልቀቅ!› የሚለውን ቃል ነበር፡፡ አሁን ሕዝቡ መለቀቅ አለበት፡፡ ታስሯል፡፡ ታፍኗል፡፡ ‹ልቀቁኝ!› እያለ ነው፡፡ ‹አስለቅቁን!› እያለ ነው፡፡ ሲፈለግ የቆየው ‹ሕዝቤን ልቀቅ!› የሚል የግፉዓንና ምንዱባን ‹ተወካይ› ነው፡፡ መሪ፡፡ ሕዝቡ ከመለቀቁ በፊት ወዴት መሄድ እንደሚፈልግ ተናግሯል፡፡ አብይ አህመድ (ዶክተር)ና መሰሎቻቸው፣ እድንቁርና ፊት፣ እዘረኝነት ፊት፣ እስንፍና ፊት፣ እመንፈስ ውድቀት ፊት  በጽንዓት ቆመው፣ እተበከለው  ክፉ መንፈስ ፊት ቆመው ‹ሕዝቤን ልቀቅ!› ማለት እንደሚጠበቅባቸው አይጠፋቸውም የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገው አዲሱ መሪ የገቡለትን ቃል እንዲፈጽሙለት ነው፡፡ትምሕርታቸው በሰላም፣ በደህንነትና በግጭት አፈታት ላይ የተመሰረተ ነውና የተማሩትን ኖረው እንዲያሳዩት!
       ሕወሀትና  አጋሮቻቸው  በሚመሯቸው  ክልሎች የታወቁ  መጻሕፍትና ጋዜጣ አከፋፋዮች ቁጥጥር፣ ውክቢያና ድንጋጤ  ሲወድቅባቸው፤ የአማርኛ  ቋንቋና ሥነ ጽሑፍ  ‹መገለልና አድልዎ› ሲደርስበት፣ ከቅርብ  ጊዜ ወዲህ ግን ኦህዴድ ዐርነት መውጣቱን የሚያሳዩ ምልክቶች ሲያሳየን ቆይቷል፡፡  ሃያ ሰባት ዓመት የተገነባ የመሰለውን ነገር  በሃያ ሰባት ወራት  እየናደው ይመስላል፡፡ መታወቂያ ላይ የብሔር ስም መጻፍ ቀረ ተባለ፡፡ ኢትዮጵያዊነትን መውደድ  እንደ ኢየሱስ ስደት፣ እስርና መከራ የሚያሸክም ብቻ  መሆኑ ቀርቶ ኢትዮጵያዊነት ሱስ መሆኑ ተነገረ፡፡ ባህር ዳር ዩኒቨርስቲ በኦሮምኛ ቋንቋ ትምህርት ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አበሰረ፡፡ እርስ በርስ መናበብ ተጀመረ፡፡ አንድነት ሆነ የመዝሙራቸው አዝማች፡፡ ይሄ ስሜት ሊቀጥል ይገባዋል፡፡ ስሜቱ ጤዛ መሆን የለበትም፡፡ ስሔድ አገኘኋት፤ ስመለስ አጣኋት ዓይነት ነገር፡፡ ቡቃያው አብቦ ዋርካ ካለከለ ለምን ተተከለ?
        እስካሁን እንዳስተዋልነው፣ የአብይ አህመድ (ዶክተር)  የጽሕፈት፣ የንግግርና የአመራር ችሎታ እጅን አፍ ላይ በሚያስጭን መልኩ የተደነቀ ሆኗል፡፡ እስካሁን በረገጧቸው እርካቦችና በተቀመጡባቸው መንበሮች  አሻራዎቻቸውን አሳርፈዋል፡፡ የጋመውን ሲያበርዱ፣ የዘመመውን ሲያቀኑ፣ መክረማቸው ሲነገር ተሰንብቷል፡፡ አሁን ወደ ዋናው፣ የተመልካች ዓይንና ጆሮ ወደ ሚጎርፍበት  መድረክ እየወጡ ነው፡፡ ይፈትናል፡፡ መጠበቅ በራሱ አደጋ አለው፡፡ ማድረግ ይገባኛል ብዬ የማምንበትን ላድርግ? ወይስ ሰዉ እንዳደርግለት የሚፈልገውን ላድርግ? እንኳንስ መሪ ማንም ሰው ራሱን መጠየቅ ያለበት ጥያቄ ይመስለኛል፡፡ ጥያቄው የትኛው ዘለቄታዊ ምላሽ ነው፣ የትኛውስ ጊዜያዊ? ‹የቱ ይቅደም? የትኛውስ ይከተል ነው ችግራችን›  ይል የለ፣ ‹እያዩ ፈንገስ›….
        በበኩሌ፣ ቶሎ በሆነ የምለው፣ የተጀመረው  የአንድነት መንፈስ እያደር እንዲያብብ  መበርታቱ ላይ ነው፡፡ መስፍን ሃብተማርያም (ሠዓሊው) አንድ ግጥም አለችው – ‹የዕድል ጸሎተኞች› የምትል፡፡ እዚያ ግጥም ውስጥ የሚከተሉት መስመሮች ማለት ምፈልገውን ብለውለኛል፡፡
                        እኔና አንቺ 
                        ድስት ውስጥ ያለን ቅመሞች ነን
                        ባለመቀየጣችን ያልጣፈጥን፡፡
                        ልጃችን፤
                        ደባልቆ ያጣፍጠናል
                        አሳምሮ ያጣፍጠናል፡፡
       አሁን በዚህ ዘመን፣ ባለመቀየጣቸው ያልጣፈጡ፣ ባለመጀመራቸው ያልተጨረሱ፣ ባለመንኳኳታቸው  ያልተከፈቱ  ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ መንግሥት እውነቱን ለመቀበል ወይም ተቀብያለሁ ብሎ ለመናገር ቢተናነቀውም፣ ከሕዝብ ጋር ያለው ትዳር ውሃ ውሃ ብሎ ነበር፡፡ ትዳር በባልና ሚስት መካከል የሚደረግ ህጋዊ ውል ብቻ አይደለም፡፡ መንግሥትና ሕዝብም ትዳር ይመሰርታል፡፡ የሕዝቡ ልብ በነውጥና ለውጥ መታመስ ሲጀምር ግን ፍቺ ይፈጸማል፡፡ አሁን ሕዝቡ ከመንግሥት ጋር መፋታት ፈልጓል፡፡ መንግሥት ግን ‹እያንዳንድሽ እግርሽ እስኪቀጥን ትኳትኚታለሽ እንጂ እኔን የመሰለ  አታገኚም› ባይ ባል መስሏል፡፡ ያለው አማራጭ አንድ ነበር፡፡ ስለዚህ መንግሥትና  ሕዝብ  አልጋ  ለዩ፡፡  የሚጋሩት – ከላይ ብርድ ልብስ፣ ከስር አንሶላ – አንድ ወጥ የሆነ ጨርቅ አልከለላቸውም፡፡ ጠረን ለጠረን ከተለዋወጡ ቆዩ፡፡ አንድ ድስት ውስጥ ያሉ፣ ግና ያልተዋሃዱ፣ ልባዊ ቋንቋ ያልተነጋገሩ፣ ቢታመሙ የማይፈዋወሱ  ሆነዋል፡፡ ይህ ህመም የሚታከመው፣ ወጡ ወጥ፣ ትዳሩ ትዳር የሚሆነው፣ መደባለቅ ሲመጣ ነው፡፡ አሳምሮ የሚያጣፍጠው  ደግሞ ቅመም ሆኖ መገኘት ብቻ አይደለም፡፡ የቅመማቱ ዋጋ፣ የጥፍጥናው ደረጃ  የሚታወቀው፣ እንደ ብዙኃኑ እምነት ልጅ ሲመጣ ነው፡፡ ፍትህ ወይም የህግ የበላይነት፣ ትክክለኛ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በሚመሰርተው  የተቀደሰ ትዳር ውስጥ የሚገኝ የአብራክ ክፋይ ነው፡፡ ይህን የአብራክ ክፋይ ለመውለድ፣ ወልዶም ለማሳደግ፣ አሳድጎም ለቁም ነገር ለማብቃት ፈተናው ብዙ ነው፡፡ ምነው ቢሉ ፈርኦን አለ፡፡ ፈርኦን አድብቶ ይጠብቃል፡፡ ፈርኦን ፍትሕ የሚጸነስበትን መንገድ የዘጋ፣ እነ ሙሴ ወደ አርነት አምባ እንዳይወጡ በእሾህ ያጠረ፣ ልቡ የደነደነበት አምባገነን ነው፡፡ በየጎዳናው፣ በየጓዳው፣ በየጎድጓዳው ደህንነቶቹን ቢያሰማራም መሸነፉ አይቀርም፡፡ የሙሴ ዘመኑ ፈርኦን ምን ሆነ? መነምነ፡፡ ኃይሉን አጣ፡፡ ተንገዳግዶም ወደቀ፡፡ ፈጣሪውም ለተዘባባቾች አሳልፎ ሰጠው፡፡ ከሸፈ፡፡ ከጉያው ጠላቶች በቀሉበት፡፡
       ስጠቀልለው፣ ደበበ ሰይፉ ‹….የጣልኩብሽ ተስፋ እኔን ይዞ ጠፋ…..› እንዲል በአንድ ግጥሙ፣ በአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የጣልነው ተስፋ  ራሳቸውንንም ሆነ እኛን  ይዞ እንዳይጠፋ እመኛለሁ፡፡ ትግል፣ትንቅንቅ ይጠብቅባቸዋል፡፡ ትግሉ ከሁለት አቅጣጫ ይመጣል – ከውስጥና ከውጭ፡፡ በሁለት ገመዶች ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች እንደ መጎተት ነው፡፡ ሕዝቡ የተገባለትን ቃል ሲፈጸም ማየት ይፈልጋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ደግሞ ‹እንዴትና ወዴት መሄድ እንዳለብህ እነግርሃለሁ፤ ብቻህን አይደለህም፤ አንተ ውስጥ እኛ አለን› ይላል፡፡ ይሄ ይመስለኛል ከባዱ ፈተና፡፡ የተተራመሰው፣ የተተረማመሰው ብዙ ነውና ሥራው ቀላል አይሆንም፡፡ ሥራው በባለ መንበሩ ቀስቃሽነትና ወስዋሽነት  ይነጻል ይጸዳል የተባለው ዘመን የወለደው በሽታ ብቻ አይደለም፡፡ የቆየም አለ፡፡ ከትውልድ ወደትውልድ እየተንከባለለ የመጣ፡፡ አሁንም ያለ አለ፡፡ ወደፊትም የሚመጣ…..
       መንበሩ እንደ ጋን ነው፡፡ ጋኑ ጽዱ አይደለም፡፡ የፍትህ  ወይን ጠጅ እንዲጣልበት ነበር – ሕዝቡ የተመኘው፡፡ ነባሩ ወይን ጠጅ  ቆምጥጦአል፡፡ ዋጋ የለውም፡፡ ሃያ ሰባት ዓመት አየነው፡፡ ተገደን የተጋትነውና የምንጋተው ሆኗል፡፡ ለረብሻ እንጂ ለፌሽታ ምንጭ አልሆነንም፡፡ አላዋደደንም፡፡ መለያየትን ነበር የሰበከን፡፡ በገዛ አገራችን የእንግድነት ስሜት እንዲሰማን የሚፍጨረጨር ክፉ ጠረን አየሩን ሞልቶት ነበር፡፡ ፈርኦናዊ ነበር አገዛዙ፡፡ ስለሆነም፣ በጋኑ ሌላ አዲስ  ወይን ጠጅ  መጣል አለበት፡፡ መጀመርያ አተላውን መድፋት – ቀጥሎ በሕግ የበላይነት በሚያምኑ አጋሮቹ – ጋኑን ማስጽዳት – ከተበከለው አየር ይነጻ ዘንድ ማሳጠን – ቀጥሎ አዲሱን ከዘረኝነት፣ ከአፈና፣ ከምን ታመጣለህ ስሜት የጸዳ የወይን ጠጅ መጣል፡፡

Filed in: Amharic