>
5:29 pm - Thursday October 10, 4340

በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ የሶስት ሀይሎች ሽኩቻ!?! (ፋሲል የኔዓለም)

የዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ መመረጥ ኢህአዴግን ሲያድነው አይታየኝም። አሁን ባለው ኢህአዴግ 3 ሃይሎች እንዳሉ አስባለሁ። አንደኛው ለውጥ ፈላጊው ሃይል ነው፤ ይህ ሃይል በአብዛኛው የምዕራቡን የአስተዳደር ስርዓት የመከተል ፍላጎት አለው። ሁለተኛው ሃይል ነባሩ “የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም ሞት” ሃይል ነው። ሶስተኛው ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት የገነባው የኢኮኖሚ ኢምፓየር እስካልተነካ ድረስ የትኛውም የፖለቲካ መስመር ተግባራዊ ቢሆን ግድ የሌለው ሃይል ነው። የዶ/ር አብይ ወደ ፊት መምጣት የመጀመሪያውን ሃይል ቢያጠናክረውም ሁለተኛውን ሃይል አሸንፎ ለመውጣት በሚያስቸለው ቁመና ላይ ግን አላደረሰውም። ሁለተኛው ሃይል በጥቅሙ የማይደራደረውን ሶስተኛውን ሃይል ጥቅሙ እንደማይነካበት በመሳመን አንደኛውን ሃይል አሸንፎ ለመውጣት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ቢሆንም ይህን ሃይል በአንዴ ዘርሮ ስልጣኑን ሙሉ ለሙሉ እንደያዘ ለመቆየት በሚያስቸለው ቁመና ላይ አይደለም። ። አንደኛው ሃይል አሸንፎ ከወጣ የሶስተኛውን ሃይል የኢኮኖሚ ድር እንደሚበጣጥስ በመዛቱ፣ ሶስተኛው ሃይል አንደኛውን ሃይል አምኖ ድጋፍ ለመስጠት ተቸግሯል። ሶስተኛው ሃይል ለውጥ ካልመጣ በስተቀር ተቃውሞ ይቀጥላል የሚል ፍርሃት ስላለውና ተቃውሞው ከቀጠለ ደግሞ የያዘውን የኢኮኖሚ የበላይነት እንደያዘ መቀጠል ስለማይችል ጥቅሙን የማይነካ ተቃውሞ አብራጅ የሆነ ለውጥ ይፈልጋል። በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ሶስቱ ሃይሎች፣ በተለይ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ሃይሎች፣ የመታረቅ እድላቸው እጅግ የመነመነ ነው። አንዱ ሌላውን ለማጥፋት ካራውን ሲስልና ገመዱን ሲገምድ መዋሉ የአደባባይ ሚስጢር ሆኗል። አብይ ከተሳካለት የሚያድነው የመጀመሪያውን የኢህአዴግ ሃይል እንጅ ሁለተኛውን እና ሶስተኛውን ስለማይሆን፣ አብይ ኢህአዴግን ለማዳን የተላከ ሰው አድርጎ መፈረጁ ትክክል ላይሆን ይችላል።
በመጨረሻም አንዳርጋቸው ይፈታ! 
(ከዛሬ ጀምሮ በጽሁፌ ማሳረጊያ ሁሉ አንዳርጋቸው ይፈታ  የሚል መፈክር ይከተላል።)
አንዲ እንዲፈታ የፌስቡክ ዘመቻውን ላስተባበሩት መስከረም አበራ፣ እየሩሳሌም ተስፋውና ለሌሎችም በስም ላላወቅሁዋችሁ ሁሉ አክብሮቴ ይድረሳችሁ።
Filed in: Amharic