>

በ ታ ኞ ቹ...! ማባዣና ኡዚን ፤ ስቴንስልና አብዮትን ... አገናኝተው የበተኑ...እኒያ ወጣቶች !!! (አሰፋ ሀይሉ)

እኒያ የ60ዎቹ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች እኒያ የ70ዎቹ መባቻ የኢህአፓ ወጣቶች — እኒያ ልባም ትውልዶች ናቸው በታኞቹ፡፡ የእነዚያን በታኞች የታሪክ ትውስታ — ለሰማው፣ ላስታወሰው — ገድላቸው፣ ብተናቸው፣ ሰቆቃቸው፣ ሁለነገራቸው፣ … — 40 ዓመታትን ተሻግሮ… በጎጆአችን ግዙፍ ምስሎቹን ነፍስ ዘርቶ ይከስትልናል፡፡ እነዚያን በታኞቹ አልናቸው፡፡ ቆንጆዎቹ — ገና አልተወለዱምና፡፡ 
እነዚያ የኢህአፓ የ60ዎቹ ወጣቶች — በታኞቹ — የፓርቲያቸው ልሳን የነበረችውን ቤት-ውስጥ ሠራሽ የእጅ መሣሪያ — የጓዳይቱን እፍታ — እንደእናት መቀነት ከድብቅ መቀነት ተፈትታ ለህዝብ ዓይንና ጆሮ የምትዳረሰውን የሃሳብ ሰደድ — ‹ዲሞክራሲያ›ን — ይጠነስሷት፣ ይከትቧት፣ ይተይቧት፣ እና ያትሟት የነበሩት — በተደራጀ የህትመት ሥፍራ ሳይሆን — በዚህች — አጨር ሰውን ራሱ ልታስቆመው በማትችል — በዚህች መሠል ሚጢጢ ዛኒጋባ ሥር ተሸሽገው ነበር — እንዲህ ያትሟት — እንዲህ ይታደሙባት — እንዲህ ያሰራጯት የነበረው፡፡
ያኔ እኮ — አይደለም ዲሞክራሲያን ስታትም ብትገኝ ይቅርና — የዲሞክራሲያን ቁራጭ ራሱ ይዘህ ከተገኘብህ — አለቀልህ — የተራራው ሥር ምርኮኛ — አሊያም ለሰማይ ቤትህ ትኬት  የተቆረጠልህ ሩቅ መንገደኛ መሆንህን — መርዶህ ደረሰ ማለት ነበር፡፡ የወረቀት እና የጥይት እና የሞት … ትንሽ የለውምና — በታኞቹን ከሆንክ — ሁልጊዜም — በሞት ሸለቆ ውስጥ ነው ጉዞህ — ጉዞውና ሌሎች አጫጭር ልቦለዶችን — ራስህ እየጻፍክ ማለት ነው፡፡ ግን ይህ የድርሰትና የደራሲ ዓለም አይደለም፡፡ ይህ የአብዮት ዓለም ነው፡፡ እና የበታኞች ዓለም፡፡
ያኔ ድብቋ የኢህአፓ ቅብዓ-ርዕዮት-ወ-አብዮት — ‹‹ዲሞክራሲያ›› — በአካልም፣ በአምሳልም፣ በትንፋሽም — አንተ ዘንድ ድርሽ ብላ ከተገኘችብህ — በቅድሚያ — ወደ ምድብ ጣቢያህ — ወደ ማዕከላዊ ትወሰዳለህ — ምስጢርህም ከውስጥህ ተዘቅዝቆ እንዲፈስ — በ‹ወፌላላ› ተገልብጠህ — ‹ቶርቸር› ትደረጋለህ፡፡ የጣለብህ ዕለት — አንተ ብጫቂዋን ዲሞክራሲያህን ማን እንደሰጠህ በወፌላላዋ ታጋልጣለህ፡፡ ካጋለጥክ ደግሞ — ያቺን የሰጠህ ሰውም በተራው — ካለበት ታድኖ ተይዞ — አንተ በተገለበጥክበት ‹አባቶር› (የድብደባ ላብራቶር!) ይገባል — እና እሱም በተራው ያንተኑ የስቃይ ሂደት ያልፍባታል፡፡ ሲያልፍ — እርሱም — ላንተ የበጨቃትን ዲሞክራሲያ — እርሱ ራሱ ከማን እንዳገኘው ካጋለጠ ደግሞ — ያኛውም ሰጪ እንደስጦታው መጠን — እርሱም ሶስተኛው ባለተራ — ያኛውም — የሰጠበትን የእጁን ያገኛል — ሞቱን፣ እና ግርፋቱን፣ እና ስቃዩን፣ እና ከታደለ — እስሩን፡፡
የበታኞቹ ሕይወት — በቃ — አበባየሆሽ ነው፡፡ ወረቀትን እንደ አደይ አበባ — አሊያም እንደ ሠርገኛ አበባ — በአዲስ አበባ ከተማ ላይ — ይበትናሉ፡፡ ‹‹ባልንጀሮቼ፤ ቁሙ በተራ!›› እያሉ፡፡ እና የሁሉም የመያዝ፣ የመገረፍ፣ የመታጎር፣ የመረሸን ተራ — ተራ በተራ — ለሁሉም በታኞች — ቀኑን ጠብቆ ይደርሳቸዋል፡፡ ጉዳዩ — የመፍጠንና የመዘግየት ነው፡፡ ማንም በታኝ — ያ አስፈሪ ዕታ ፈንታ — ያ የዙር ተራ — አይቀርለትም፡፡ ብተና ክፉ ነው፡፡ ያውም ጦሰኛ፡፡ በፍፁም ወደው የሚገቡበት እንጀራ አይደለም፡፡ የጠላ ቂጣም አይደለም ኧረ! በታኝነት — ቆርጠው የሚገቡበት — የክፉ ቀን ሥራ ነው እንጂ፡፡ ለጠላትህም የማትመኘው ዓይነት፡፡
በብተና የሚያዝ ሁሉ — ሳይወድ በግድ፣ በግርፋትና ስቃይ ብዛት — ዞሮ ዞሮ ዞሮ ዞሮ— እንደረዥም ሰንሰለት፣ አሊያም እንደሰደድ እሳት — አንዱ አንዱን፣ አንዱ አንዱን እያጋለጠና እያስያዘ — በመጨረሻ — ከሁሉ የከፋው የመጨረሻው የሥቃይና የሞት መቅሰፍት ተሸካሚው — ወይም በሰንሰለቱ መጨረሻ ላይ ሆነው ከሁሉም የከበደውን ቀንበር የሚሸከሙት የመጨረሻዎቹ ሰለባዎች — እኚሁ — አሌ በማትባል ዛኒጋባ ሱቅ ሥር ተጎናብሰው — የሌኒንን ጽሑፍ እያጣቀሱ — የማርክስን መርሆዎች እያነሱ — የዕለቱን አንኳር ክስተቶች እያስተነተኑ — በሻይ ቅጠልና ስኳር፣ በጢስና ቄጠማ ታጅበው — በስቴንስል ወረቀት ታይፓቸውን እየተየቡ በጥቁር ቀለም…. አንዳንዴም በቀይ ቀለም… በል ሲላቸው በሰማያዊ ቀለም . . . የስንብት ቀለማትን የሚያባዙት — ያባዙትን ደግሞ የሚበትኑት — የበተኑትን ምላሽ ደግሞ በግዙፍ ስጋትና በቀጭን ተስፋ የሚጠባበቁት — እኚሁ የፈረደባቸው — የደፋር ደፋር ወጣቶች — በታኞቹ ናቸው፡፡
ልብ በል፡፡ እነዚህ በታኞች — የሚበትኑት አድመኞችን አይደለም፡፡ በታኞቹ የሚበትኑት — ሠላማዊ ሠልፍም አይደለም፡፡ እኒህ — የሚበትኑት — አድማን ራሱን ነው፡፡ አድማን — እንደሠርግ አበባ — በአምባገነኑ ባለጠብመንጃ ላይ — ይነዙበታል — ይበትኑበታል፡፡ የሚበትኑት ውቃቢም — የደርጉን ቀልብ ይበትነዋል፡፡ የእነርሱን ትግል ደግሞ ያበረታዋል፡፡
በታኞቹ — የሚበትኑት — በጣፋጭ ሥዕል የተሞሉ — ምድር ገነት መሆኗን የሚሰብኩ — የአካባቢ ጥበቃ ሽልማት የሚያሳጩ — የይሆዋ ምስክሮችን በራሪ መጽሔቶች እንዳልነበረ ግልጽ ነው መቼም፡፡ እኒህኞቹ በታኞች የሚበትኑት — የመረረ፣ የከረረ፣ ወደኋላን የማያውቅ — ቁርጥ ያለውን — የጭቁኖች የንቁዎች የሳተናዎች የፖለቲካ አብዮት ነበር፡፡ እኒህ በታኞች — በዲሞክራሲያ እትማቸው የሚበትኑት — ለሕዝባችን ይገባዋል የሚሉትን ዲሞክራሲያቸውን ነው፡፡ እና አመለካከታቸውን፡፡ እና ውጥናቸውን ነው፡፡ እና ርዕዮተዓለማቸውን፡፡ እና የትግል መንፈሳቸውን ነው፡፡ እና ተስፋቸውን፡፡ እና ንዴታቸውን፡፡ እና በቃ … ሥርነቀል ሶሻሊስታዊ አብዮታቸውን ነው የሚበትኑት፡፡ የ40 ቀን ዕድላቸው ሆኖ — እህል ላበደረ አፈር ሆኖባቸው — ስንቱን እንዳልበተኑ — እነርሱም — ተበትነው ቀሩ እንጂ!! አይ ይህቺ ሃገር — ‹‹የሞተላትን ወዲያ ብላ፣ ለገደለላት የምታበላ›› ምድር!
እነዚያ በታኞች — ልባሞቹ ወጣቶች — እያንዳንዷ ደቂቃ — የደቀነችባቸው የሚያስጨንቃቸው አደጋ — ሁሌም መንታ መንታ ሆኖ በላያቸው እንዳንዣበበባቸው ነው፡፡ ሞት አሞራ ሆኖ . . . አብዮት ጠባቂው ጭልፊት ሆኖ — ‹‹አሞራ በሰማይ ሲያይሽ ዋለ!›› እያለ ሲያንዣብብባቸው የሚውል — ከሞት ጋር ልፊያን የለመዱ — ሌት ጨለማን የሚመርጡ — ብዕረኞች፣ ህልመኞች፣ ተፋላሚዎች፣ ጠያይም ግላዲያተሮች ናቸው — እነዚያ በታኞች፡፡
በታኞቹን የሚያንዣብብባቸው አደጋ — ከራሳቸው ዛኒጋባ ድብቅ ምሽግ — ካሁን ካሁን የቀለም ሽታ፣ አሊያም የትየባ ድምጽ፣ አሊያም የጠቋሚ ጣት፣ ካሁን አሁን መጣብን የሚል በእነርሱ ላይ በቀጥታ የተነጣጠረ ድንገተኛ አደጋ ብቻ አልነበረም፡፡ በድንገት መወረርና መያዝ ሁሌ የማይቀር አደጋ ነው እሱ፡፡ ግን የከፋው — እና በቅርብ ሆነህ ‹ድም ድም ድም›› ሲል ዳናውን የማትሰማው — እና ከአንተ በሩቁ ሆኖ አንተን የሚያነፈንፍህ አደጋ — ከብዙ ሺህ ወጣት አባሎቻቸው በአንዱ ላይ — ወይም በአንዲቱ ላይ የተደቀነች አደጋ ሁሉ ነች— በእነርሱም ላይ ጥላዋን የምታጠላባቸው፡፡
አንድ የዲሞክራሲያን ቁራጭ የያዘ — ይለፍልህ ያላለው ምስኪን አብዮተኛ ወጣት — በማንኛዋም ቅፅበት ሊያዝ ይችላል አይደል? ግን ተያዘ ማለት — በቃ — በእነዚህ የቤት ውስጥ አታሚዎች — በበታኞቹ ላይ — የሞትን ድግስ የሚጋብዝ — አራጆቻቸውን ሊያመጣባቸው የሚችል ታላቅ ጠንቅ ነው፡፡ የአንድ ሰው መታሰር — ለሁሉም — የመልዓከ-ሞትን መለከት የሚነፋ — ወደ እነርሱ አቅጣጫ የተነጣጠረ — ተምዘግዛጊ ሚሳይል በሠማይ በምድር እያመጣባቸው እንደሆነ የሚጠቁም — ከደቂቃ ደቂቃ አሳቃቂ ድምጹን የሚያስተጋባ — ታላቅ የአደጋ ደወል ነው፡፡ እና በዚህ የተነሳ — አንዱ ራሱን ብቻ ሳይሆን — ሌላውንም ይጠብቃል፡፡ እያንዳንዱ ለሁሉም — ሁሉም ለእያንዳንዱ ናቸው — በታኞቹ፡፡
ግን እንዲያም ሆኖ— በየዕለቱ የሞት ደውልም እየተደወለባቸው — በጽሞና ዲሞክራሲያቸውን ያባዛሉ በታኞቹ፡- እንዲህ ኡዚያቸውን ከጎናቸው፣ እስክሪብቷቸውን በአፍሯቸው፣ ታይፓቸውን ከፊታቸው፣ ሱረታቸውን በጉያቸው፣ ማባዣቸውን በጓዳቸው፣ . . . አድርገው! ካልመጣባቸው ለመጻፍ እና ለመበተን — ከመጣባቸው ደግሞ የጀግና ሞትን ለመሞት የተዘጋጁ ቆራጥ ወጣቶች ናቸው በታኞች የምልህ እኮ — ለዚህ ነው፡፡ አይ ልብ! አይ ወኔ! አይ ዓላማ! አይ ጭንቅላት! አይ አጻጻፍ! አይ አበታተን! ማን እንደ እነርሱ??!!
እኒያ — ወይ ‹‹ሕዝባዊ መንግሥት አሁን!›› እውን እስኪሆን — አሊያም ‹‹የገዛ ሞታቸው አሁን›› እውን እስኪሆን — በደርግ አሳሾች አፍንጫ ሥር፣ በደህንነት፣ አብዮት ጠባቂዎች፣ ወታደሮች፣ ካድሬዎችና አቃጣሪዎች ማጀት ሥር ሆነው — ሊመጣ ያለውን በቁርጠኝነት የሚጠባበቁ — ያመኑበትን በልበ ሙሉነት የሚከውኑ — እጅግ አስገራሚ ልበ-ሙሉዎች — እኒያ የኢህአፓ በታኝ ወጣቶች — እስካሁንም — በኢትዮጵያ ምድር ዳግመኛ አልተፈጠሩም — አይፈጠሩምም — እጅግ ይገርሙኛል፡፡ የቁርጠኝነታቸው መጠን ያስቀናኛል!!!
ብዙዎቹ በታኞች እኮ ደግሞ — በግራ ጎናቸው ማለዳውን በተነሱበት በአንደኛው ጎዶሎ ቀን — ቁራጭ ጋዜጣ በፍተሻ ወይ በጥቆማ ተይዞባቸው — በወፌላላ ቢገለበጡም እኮ፣ በጋለ ብረት ቢተለተሉም፣ በብረት ሰደፍ ቢቀጠቀጡም፣.. ምን ስቃይ ቢደርስባቸው ምን — ለስቃይ እጅ ሰጥተው — ፈጽሞ ፈጽሞ የቁራጯን ዲሞክራሲያ ጌታ የማያጋልጡ… ሳያጋልጡም የተቀደሰ ሞታቸውን የሚጎነጩ ዓይነቶች ይበዙ እንደነበር — ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል፡፡ በዚያ ዓይነት ቁርጠኝነት — ከስቃይ ጎርፍ ጀርባ — ከእንጦርጦስ ባሻገር — ልበሙሉነታቸው ሳይከዳቸው — ከነዓላማቸው — ከነፅናታቸው — በማራኪዎቻቸው እጅ እንዳሉ — ወደ መቃብራቸው የወረዱ — እጅግ ብዙ ብዙ ሰማዕት ሆነው ሃውልት ሊቆምላቸው የሚገቡ — ባንደኛው ሌት ከነወረቀታቸው ወጥተው የቀሩ — ከነቀለማቸው እሳት የበላቸው — በርካታ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች — የዲሞክራሲያ በታኞች — ወጣት የትግል ሃዋርያት እንደነበሩ — ብዙዎቻችን የምንሰማው ነው፣ የነበሩበት በሃዘን ትዝታቸውን ያወሱናል፡፡ ይህ — የበታኞቹ — ደረቅ እውነት ነው፡፡
በእኔ አስተያየት — እነዚያ — የ60ዎቹ የኢትዮጵያ በታኞች — በልባቸው የተቀጣጠለው የሃገር ፍቅር ስሜት — የሚጓዙበትን የሞት ሸለቆ ያስረሳቸው እነዚያ ህቡዕ የኢህአፓ ወረቀት በታኞች ወጣቶችም —  አንድ አባላቸው በተያዘባቸው ቁጥር፣ አንድ አባላቸው በተገደለባቸው ቁጥር፣ አንድ አባላቸው በተገረፈባቸው ቁጥር፣ አንድ አባላቸው በተሰወረባቸው ቁጥር — እነርሱም — ይበልጥ ትንታግ እየሆኑ — ይበልጥ ኃይልን እየተላበሱ የሚሄዱ — ይበልጥ እየተፋጁ — ይበልጥ እየጀገኑ — ይበልጥ እየቆረጡ የሚመጡ — ልክ እንደ ንስር አሞራ ኃይላቸው ከዘመን ዘመን እየታደሰ የሚሄድ — አስገራሚ በታኞች ነበሩ እላለሁ፡፡ ነበሩም፡፡ እነዚያ በታኞች የሚያዘንቡት የቃላት ኃይልና ናዳቸው ራሱ የሆነ መብረቃዊነት አለው፡፡ የፀሐፊዎቹን የሚንተገተግ ወላፈን ያሳያል፡፡ ምሬታቸውን፣ ቁርጠኝነታቸውን ካገር አገር ያሰራጫል፡፡
በታኞቹ — በሉ ሲላቸው — ንዴት ሲያስገነፍላቸው — ከማይታወቁበት ህቡዕ ስፍራ ላይ ሆነው — እንደ ደመና በላያቸው ባጠላባቸው ጨቋኛቸው ላይ — እና እርሱኑ ደግፈው በቆሙት ሁሉ ላይ — የታጠቁትን የቃላት እሩምታ — አውቶማቲክ ላይ ከፍተው — እንደጉድ ያንበለብሉታል —  ‹‹አውሬ!››፣ ‹‹ገዳይ!›› ‹‹አፋኝ!›› ‹‹ፋሺስት!›› ‹‹ሽል!›› ‹‹ጭንግፍ!›› ‹‹ቀማኛ!›› ‹‹በዝባዥ!›› ‹‹አራጅ!›› ወዘተ ወዘተ በሚሉ የትየለሌ አስደንጋጭ ቅፅሎች — ስሙን እየጠሩ — ‹‹በሌሊን ስም!›› ይገስፁታል — ‹‹በማርክስ ስም!›› ያከናንቡታል — ‹‹በሰፊው ህዝብ ስም!›› ያሳቅሉታል — በኢትዮጵያ ስም ይገዝቱታል —  ወደጥልቁ ሊጥሉት — ያን ‹‹በል በለው በል በለው!›› ብቻ የነበረ — የጠመንጃ አምባገነንነት መንፈስ፡፡ የእኒያ ልባም በታኞች መባዘን — አንዳንዴ የምራቸውን ያሳዝኑኛል፡፡ ባለጠመንጃውን አምባገነን — ‹‹ብዔል ዜቡል››ን — ያለጠብመንጃ — ወደ ጥለቁ በቃላት ሊጥሉት ማሰባቸው፣  — እና ብዔል ዜቡልን ለማውረድ እየገሰፁ  — ከነውድ ህይወታቸው ወደ መቃብር መውረዳቸው — አኗኗራቸው፣ እና አሟሟታቸው ያሳዝነኛል!!
ያ ‹‹የሥርቻው ሥር ወጣት ምሁር›› — እኒያ ልበ-ሙሉ ወጣት በታኞች — እኒህ — በዘመናቸው — የኢትዮጵያን ሕዝብ ሥልጣን፣ ብሶት እና ድምፅ በቀማው — እና በአፈሙዙ ቁጥጥር ሥር ባዋለው — እና ‹‹ቀማኛ!›› ብለው በሰየሙት ወታደራዊ አገዛዝ ላይ — ድፍን የኢትዮጵያ ወጣት — ‹‹ሕዝባዊ መንግሥት አሁን!›› (በቅንፍ ‹‹ወይም ሞት!››) — ብሎ እንዲነሣ — በአስገራሚ ልበ-ሙሉነት የብዕር ሠይፋቸውን የመዘዙ — ስሜት ቀስቃሽ በሆኑ መፈክሮቻቸው ያገራቸውን ወጣቶች ለቆራጥ ትግል ያነሣሡ — ታይተው በማይታወቁ አዳዲስ መንገዶች ህዝባቸውን ያነቁ፣ ያደራጁ፣ ያታገሉ — እና ሞትን ሳይሸሹ እውነተኛውን ክቡር ተጋድሎ የፈጸሙ — እና መራራ የሆነውችውን ታላቅ መስዋዕትነት ላመኑበት ክቡር ዓላማ የከፈሉ — በእርግጥም ባስታወሷቸው ቁጥር — ፋናቸው እንደ ንስር ኃይል፣ እንደ ሰደድ እሳት፣ እንደ ፀሐይ ብርሃን — ለብዙዎች ደማማቅ ሃሳቦቻቸውን  የሚከስት — ታላቅ የምስራቅ ከዋክብት ነበሩ — በሌት ታይተው በጀንበር የሚጠፉ — እውነተኛ አብረቅራቂ የኢትዮጵያ ከዋክብት!!! ያሳዝናሉ — በታኞቹ፡፡ ክብር ይገባቸዋል፡፡ በክብርና በቆራጥነት ያረፈውን አጥንታቸውን በያሉበት የምድሪቱ ጌታ ያሳርፍላቸው፡፡ አበቃሁ፡፡ ️
Filed in: Amharic