>
5:28 pm - Saturday October 9, 6866

የብሔርተኝነት እና የጽንፈኝነት ልዩነት! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

እንደምታውቁት ብሔርተኝነትንና ጽንፈኝነትን ያመጡብን የጥፋት ኃይሎች (ወያኔ/ኢሕአዴግ፣ ኦነግና ሸአቢያ) ናቸው፡፡ ብሔርተኝነት የሚጎዳ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ብሔርተኝነት ተፈጥሯዊና ጤናማ ስለሆነ፡፡ ብሔርተኝነት ተፈጥሯዊና ጤናማ ከሆነ ከነኝህ የጥፋት ኃይሎች በፊትም አማራ ሀገር ያሥተዳድር በነበረበት ረጅም ዘመናትም ነበረ ማለት ነዋ? ብላቹህ ትጠይቁ ይሆናል፡፡ መልሱ አማራ ብሔርተኝነት ለሀገር አንድነትና ህልውና አደጋ ይፈጥራል ብሎ በመሥጋት  ብሔርተኝነትን ይጸየፍ ይንቅ ስለነበረ ብሔርተኝነትን ያቀነቅን አልነበረም የሚለው ነው፡፡ ያው አማራ ብሔርተኝነትን የናቀውና የተጸየፈው ብሔርተኝነት ተፈጥሯዊ ሆኖ ህልው ስለሆነ እንደሆነ ልብ በሉ፡፡
የሰው ልጅ በተፈጥሮው ለራሱ ለግሉ አሳቢ ቆርቋሪ ነው፡፡ ይሄንን ስሜት አሐዳዊነት ወዳለው ቡድን ስትወስዱት ማለት ነው ብሔርተኝነት ማለት፡፡ ሰው ለራሱ ካሰበ፣ ለራሱ ከተቆረቆረ፣ ነፍሱን ከወደደ ሌሎችን አያጠቃም አይተነኩስም፡፡ ለዚህ ነው ብሔርተኝነት ሊያስጠብቀው የሚፈልገው የቡድን ጥቅም እያለም ጤናማ የሚሆነው፡፡
ጽንፈኝነት ማለት ደግሞ ለኔ ብቻ ማለት ነው፡፡ ስለዚህም የጽንፈኝነት አስተሳሰብ ካላቹህ ጥቅማቹህን ሌሎቹን በማጥፋት ላይ ትመሠርታላቹህ፡፡ ለኔ ብቻ የምትሉ ከሆነ ደግሞ ሌሎቹ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ እናንተን ለማጥፋት እንዲገደዱ ታደርጓቸዋላቹህ፡፡ አሁን የሁለቱን ልዩነት ተረድታቹሀል ብየ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
እዚህ ላይ “አማራ ለኔ ብቻ በማለቱ አይደለም ወይ ሀገሪቱን በብቸኝነት ሲገዛ የኖረው?” ትሉ ይሆናል፡፡ ነገሩን ልብ ብላቹህ ከተመለከታቹህት ግን እውነታው ይሄ አይደለም፡፡ አዎ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ሐቲት ምክንያት ማለትም እግዚአብሔር ለቅዱስ ዳዊት “በትርን (ሥልጣንን) ከዘርህ አላጠፋም!” ብሎ በገባለት ቃል መሠረት በአውሮፓ፣ ዓረቦችን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በእስያ፣ በአፍሪካ የዘር ሐረጋቸውን ከእስራኤሉ ንጉሥ ከዳዊት (ከዳውድ) የሚመዙ ነገሥታት እንደገዙ ሁሉ በኢትዮጵያም ገዝተዋል፡፡ እርግጥ ነው ነገሥታቱ ከአማራ የወጡ ነበሩ፡፡ ይሁንና ይህ ታሪክ ግን ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን የተዋለደው የአንድ ቤተሰብ ታሪክ ነው እንጅ የአጠቃላዩ የአማራ ነገድ ታሪክ አይደለም፡፡ የአማራ ታሪክ የሚሆነው በቀጥታ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ነገሥታቱ የሚሾሙት ከሰሎሞን ጋር የተዋለደው ቤተሰብ ልጅ በመሆናቸው ነው እንጅ ከማንኛውም የአማራ ተወላጅ ተመርጠው አልነበረምና ይነግሡ የነበረው፡፡ በመሆኑን አማራ ለኔ ለብቻየ ብሎ የያዘው ሥልጣን አልነበረም፡፡
ስለጽንፈኝነት ካነሳን ኢትዮጵያ ውስጥ ጽንፈኝነት የሚያስፈልገው ነገድ ወይም በዘልማድ እንደምንለው ብሔረሰብ ካለ በጥቂቱ ሳይበዛ ወይም ገራም የሆነ ጽንፈኝነት የሚያስፈልገው ለአማራ ነው፡፡ ለሌሎቹ አያስፈልግም፡፡ ካስፈለጋቸው የሚያስፈልጋቸው ብሔርተኝነት ነው፡፡ ምክንያቱም አማራ እንደምታዩት ለሀገር ህልውናና አንድነት ሲል ጥቅሙን በእጅጉ አሳልፎ መስጠትን ከመታገሱም በላይ በጥፋት ኃይሎች የታወጀበትን የዘር ማጥፋትና ማጽዳትን አረመኔያዊ ጥቃት ተቀብሎ እንደመሥማዕት በግ በዝምታ የትም በመታረድ እያለቀ ነውና ነው፡፡
ይሄንን የአማራን አለቅጥ የበዛ የኃላፊነት ስሜት (የዋህነት) ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማመጣጠንና ለሀገሩ ብቻ ሳይሆን ለራሱም አሳቢ ማድረግ የሚቻለው አማራን ከብሔርተኝነት ባለፈ የጽንፈኝነትን ክኒን በጥቂቱ ማቅመስ ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም የጥፋት ኃይሎች የጥፋት ሥራና የታሪክ አጋጣሚዎች የአማራን ጥቅም በብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ብቻ እንዳይመለስ እንዳይጠበቅ አድርገውታልና ነው፡፡ በመሆኑም አማራ ያጣውን ጥቅሙን ማስመለስ ማስጠበቅ ካለበት ገራም የሆነ ጽንፈኝነትም የግድ ያስፈልገዋል፡፡ አማራ እንዲህ ሲያደርግ ብቻ ነው የሀገሪቱ ችግር ሊቀረፍ ሊፈታ የሚችለው፡፡ ስለሆነም ጊዜ ሳንሰጥ ሁሉም ቀና አሳቢ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለዚህ በርትተን እንሥራ እላለሁ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
Filed in: Amharic