>
5:13 pm - Monday April 19, 9154

የኢትዮጵያ እድገት መለኪያው የራሱንና የቤተሰቡን ምቾት  ብቻ ያደረገው ደላላው ዘመዴነህ !?! (ካሳ አንበሳው)

ዘመዴነህ ንጋቱ ይባላል፤ በምስራቅ አፍሪካ ኤርነስት ኤንድ ያንግ (Ernst & Young) የተሰኝ አማካሪ ድርጅት ማኔጂንግ ፓርትነር ነው፤ በትውልድ ኢትዮጵያዊ ቢሆንም ዜግነቱ አሜሪካዊ ነው:: ጁሊ የምትባል ጣሊያናዊት አግብቶ ቦሌ አካባቢ ይኖራል፤ የዛሬ 20 ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ያመጣው የባለቤቱ ጉትጎታ እንደሆነ ለተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲናገር ተደምጧል:፤ ከዛ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ የመስራትም ሆነ የመኖር እቅድ እና ፍላጎት አልነበረውም::
ዘመዴነህ የኩርማን መሬት ወይም የመኖሪያ ቤት ደላላ እንዳይመስልህ፤ ድፍን ኢትዮጵያን እየሸነሸነ የሚሸጥ አለም-አቀፍ ደላላ ነው፤ ከያንዳንዱ የመሬት ወረራ እና የተፈጥሮ-ሀብት ብዝበዛ ጀርባ ዘመዴነህ ንጋቱ አለ፤ ህወሓት እና የህወሓት ግብረ አበሮች ገንዘብ የሚያሸሹበትን መንገድ የጠረገው ዘመዴነህ ነው፤ በደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም በጋምቤላ ክልል ለተጧጧፍው የመሬት ንጥቂያ (land grab) ዋናው ተዋናይ ዘመዴነህ ነው፤ በአንድ ወቅት ኦባንግ ሜቶ ለኤርነስት ኤንድ ያንግ ዋና ድሬክተር ይህን ሰው ሃይ በሉልን የሚል ደብዳቤ መጻፉን አስታውሳለው፤ የህንዱን ካሩቱሪን እና የዳንጎቴን  ጨምሮ ሌሎች በአበባ እርሻ የተሰማሩትን <<ባለሃብቶች>> ወደ ኢትዮጵያ ያመጣቸው ዘመዴነህ እንደሆነ መረጃዎች ያሳያሉ፤ የዜጎች መፍናቀል፣ የአካባቢ ብክለት፣ የጉልበት ብዝበዛ ወ.ዘ.ተ. ለዘመዴነህ ቁብ አይሰጡትም፤ እርሻህን ከጀርባህ ለውጪ ባለሃብት አስማምቶ በአናትህ ላይ ከሸጠ በኋላ አንተን አፍር ጎልጓይ እና አረም አራሚ ያደርግሃል፤ ከዛም ሥራ ፈጠርኩልህ ይልሃል፤ እርሻህን ዘመዴነህ ካየብህ መጨረሻህ መንገድ ዳር መውደቅ ነው::
ዘመዴነህ ስራዮ በአውሮፓ እና አሜሪካ እየዞሩ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ማግባባት ነው ይበል እንጂ ዋናው ተልዕኮው ሌላ ነው፤ ይህም ለመንግስት ድጋፍ (lobby) በማሰባሰብ መንግስት በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ተቀባይነትን እንዲኖረው ማድረግ ነው:: ይህን ለመረዳት በአንድ ወቅት ከፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጠኛ ካትሪና ማንሶን (Katrina Manson) ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅን መመልከቱ በቂ ነው፤ ሰውየው የመንግስት ቃል አቀባይ እንጂ ገለልተኛ የኢንቨስትመንት አማካሪ አይመስልም::  ተግባሩ የኤርነስት ኤንድ ያንግን የስነ-ምግባር ደንብን፥ በተለየም ነጻና ገለልተኝነት (objectivity and independence) የሚሉትን የሚጻረር ነው፤ ዘመዴነህ ለውጭ ባለሃብቶች ስለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚሰጠውን መግለጫ ቅንድብ ይሰቅላል፣ አገጭ ዘጭ ያደርጋል፣ ጉም ያዘግናል:: በቱርክ፥ አሜሪካና ካናዳ ያቀረበውን ማብራሪያ ዩቱዩብ (Youtube) ላይ ስለተጫኑ ማንም ሰው ተመልክቶ የራሱን ትዝብት መውሰድ ይችላል፤ እኔን በግሌ ኢቢሲ ማረኝ አሰኝቶኛል፤ ዘመዴነህ ስለ ኢትዮጵያ እድገትና ለኢንቨስትመንት አመቺነት ገለጻ ሲሰጥ ከሰሙ <ኢትዮጵያ> የምትባል [ሌላ] ሀገር አውሮፓ አህጉር ውስጥ መኖር አለባት ቢሊ አይፈረድብዎትም፤ የዘመዴነህ ኢትዮጵያ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል የሰፈነባት፤ የተማረ የሰው ሃይል ያጥለቀለቃት፤ ጤናው የተጠበቀ አምራች ዜጎች ባለቤት፤ በጣም ርካሽ እና የማይቋረጥ [የኤሌክትሪክ] የሃይል አቅርቦት የታደለች፤ መሰረተ ልማት የተሳለጠባት፤ ሰረቶ የሚያሰራ መንግስት የሚመራት ሀገር ናት::
እንደ ዘመዴነህ ገለጻ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሰላም እና መረጋጋት እነ ዴርማርክን ያስቀናል፤ የባህር በር ጉዳይ ለዘመዴነህ ከቁጥር የሚገባ አይደለም፤ በደረሰበት ሁሉ ኢትዮጵያ የትልልቅ መርከቦች ባለቤት ስለሆነች የባህር በር የላትም ብላችሁ አትጨነቁ ይላቸዋል፡- ባለሃብቶችን፤ መርከብ የባህር በርን እንደሚተካ ለዘመዴነህ ብቻ ነው የተገለጠለት::
እንደ ዘመዴነህ ገለጻ ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ ገንዘብን ባንክ አስቀምጦ ትርፍን በአካፋ የማፈስ ያህል ነው፤ አደጋ የለሽ  (risk-free) ኢንቨስትመንት፤ የዘመዴነህ ኢትዮጵያ ገንዘብ ላለው ኢንቨስተር ይቅርና ተቀጥሮ ለመኖር የሚፍልግ አሜሪካዎና አውሮፓዊ ጭምር የምታማልል ሀገር ናት::
የዘመዴነህ ኢትዮጵያ በእድገቷ እና ለኢንቨስትመንት አመቺነቷ በአለም ላይ አቻ የሌላት ብትመስልም በቅርቡ የአለም ባንክ ግሩፕ (The World Bank Group) ይፋ ያደረገው የ2018 ለንግድ ስራ አመቺነት ደረጃ (Ease of Doing Business Index) ሪፖርት ኢትዮጵያን ከዓለም 161ኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል:: ይህም ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ ሃገራት አማካኝ ደረጃ ያነሰ ነው::
ዘመዴነህ የኢትዮጵያን እድገት የሚለካው እንዴትና በምን ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው:: ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሰጠን ሰውየው ከዘመን መጸሄት ጋር መስከረም 22, 2008 በመኖሪያ ቤቱ ያደረገው ቃለ መጠይቅ ነው::  ዘመዴነህ እንዲህ ይላል
<<…ለምሳሌ ይሄንንም ቤት ልንሠራ ስናስብ ሲገዛ ቦታው የዚያን ጊዜ ምንም የሌለበት ነበር፤ እርሷ (ባለቤቴ) ወደዚህ አካባቢ ትንሽ ቤት ስለነበራት ይሄንን ቦታ እናየው ነበር፤ ከሰፈር ሰፍር መሬት እንድንገዛ እርሷም ትዞር ነበር፤ ከዚያም አንድ ቀን መሬት አግኝቻለሁ በሊዝ መግዛት አለብን አለችኝ፤ ምን ያደርግልናል ስላት ይሄ ወደፊት በጣም ጠቃሚ አካባቢ የሚሆን ነው አለችኝ፤ ተደራድራ መጣች ይሄ ያለንበት አሁን አንድ ሺ ካሬ ነው ያኔ በሁለት ሚሊዮን ገዛነው፤ አይሆንም ብዬ ስል እርሷ ኡኡ አለች፤ የዚያን ጊዜ ታዲያ ለአንድ ወር ያህል ተናድጄ አላናገርኳትም፤ አሁን ዋጋው እየጨመረ ሳየው፣ አሁን ያለውን የቦታውን ግምት ስሰማ ሁሌ በደስታ እስማታለሁ፤ አሁን መሬቱ ስድሳ አምስት ሚሊዮን የሚገመት ሆኗል፤ አሁን ደግሞ ተያያዥ በሆነ ቦታ አንድ ሺ አምስት መቶ ካሬ በሊዝ ወጥቷል…አሁን ይሄም ሲገመት ሰባ አምስት ሚሊዮን ነው፤ በአጠቃላይ አሁን የያዝነው ቦታ የመሬቱ ግምት መቶ አርባ ሚሊዮን ነው፤ እኔ ብሆን እዚህ ሠፈር አሁን መኖር አልችልም፤ #በአንድ_በኩል_ይሄ_የሚያሳየው_የኢትዮጵያንም_ዕድገት_ነው>>
ዘመዴነህ እንደዚህ ነው፤ የግሌ መኖሪያ ቤት ዋጋ ሰለጨመረ ሃገሪቷ አድጋለች ይልሃል፤ የራሱ ኑሮ የኢትዮጵያ ዕድገት መለኪያ ነው፤ ይችን መለኪያ “Zemedeneh Coefficient” እንበላት ይሆን? ይህን መለኪያ ደና አድርጎ ቢያብራራው የኖቤል ሽልማት ሊያስገኝለት ይችል ይሆናል፤ እዚሁ ላይ ግርምት የጫረብኝ ሌላው ጉዳይ <ሃገሪቷ የዛሬ 10 ዓመት መካከለኝ ገቢ ያላቸው ሃገሮችን ትቀላቀላለች> የሚለን ዘመዴነህ የገዛ መሬቱን እና ቤቱን የወደፊት ዋጋ መተንበይ አለመቻሉ ነው:: ይህ በራሱ የሰውየውን እውቀትና ችሎታ እንድንጠረጥር ይጋብዛል::
ለዘመዴነህ የኢትዮጵያ እድገትን የተለየ የሚያደርገው ኢኮኖሚው ለተካታታይ አስር ዓመታት በሁለት አኃዝ ማደጉ ብቻ አይደለም፤ ይልቅስ የተመዘገበው ልማት ሁሉን ያሳተፍ፤ ሁሉን ተጠቃሚ ያደረገ መሆኑ ነው፤ በዜጎች መካከል ያለው የሃብትና የገቢ ልዩነት እምብዛም የማይራራቅና ጤናማ ነው፤ ለዘመዴነህ፤ ይህንን ለዘመን መጽሄቱ ጋዜጠኛ እንዴህ ሲል ያብራራል::
<<….የ10.3% እና10.4% ዕድገት ምን አምጥቷል? የሚለው ደግሞ አስፈላጊ ነው፤  #የኢትዮጵያ_ዕድገት_ሁሉን_ያካተተ_የመሆኑ_ነገር_ነው፤ #ኢትዮጵያ_በዓለም_ውስጥ_እጅግ_ተመራጭ_የሆነ_ጊኒ_ኮፊሺየንት_የገቢ_አለመራራቅ_ሪከርድ_አላት፡፡ #በሀብታምና_በደሃው_መካከል_ያለው_ርቀት_ሚዛናዊ_የሆነበት ነው፤ ይህ ሲሆን ለኢንቨስተሮችም የበለጠ በራስ መተማመን ይሰጣቸዋል፤ ምክንያቱም ቀጣይነት ያለው ዕድገት በመሆኑ ነው፡፡>>
ዘመዴነህ በዚህ አያበቃም፤ የኢትዮ ቴሌኮም ለምን መመስገን እንዳለበት ለዘመን መጽሄቱ ጋዜጠኝ የራሱን ቤት ምሣሌ አድርጎ እንዲህ ሲል አስረዳው;-
<<እዚህ ቤቴ አሁን አራተኛ ትውልድ ሞባይል ቴክኖሎጂ አለ፤ ኢንተርኔቱም እጅግ ፈጣን ነው፤ ድምፁም የጠራ ነው፤ እዚህ እቤቴ ድረስ ፋይበር ኬብል አስገብቻለሁ፤ ስለዚህ የ15 ዓመት ልጄ ማይክ የቤት ሥራ የማይሠራበት ምንም ምክንያት የለውም ማለት ነው፤ ይሄን ማመስገን አለብን፤ በገጠርም ኢትዮ ቴሌኮም ብዙ ሠርቷል፤ መመስገን አለበት>>
የሸራተኑን ስታጋዮኒ ሬስቶራን አዘውትሮ ለሚጠቀመው ዘመዴነህ [በአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ <ስራ አስፍጻሚዎን ይወቁ> (Know your Executives!) በሚለው አምድ እንደገለጸው] የኢትዮጵያ እድገት መለኪያው የራሱና የቤተሰቡ ምቾት ነው:: ባለቤቱ ጁሊ እና ልጁ ማይክ ብቻ አይጉደልባቸው………..
ለማንኛውም በድህረ ወያኔ ኢትዮጵያ ለፍርድ መቅረብ ካለበቻው ሰዎች ውስጥ ዘመዴነህ ግንባር ቀደሙ ነው፤ ይህችን እንድጽፍ የኮረኮረችኝ ኢዮብ ብርሃነ ሰለዚህ  ሰውዬ የከተባት ነገር ነች::
Filed in: Amharic