>

የተፈናቀሉትን ወደነበሩበት መመለስ አስፈላጊና አስቸኳይ ነው - ግን ግማሽ መፍትሔ ነው!!! (መስፍን ነጋሽ)

የአገሩ፣ የምድሩ ባለቤቶች ዜጎች ሳይሆኑ ምናባዊዎቹ “ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች” እስከሆኑ ድረስ፣ ማፈናቀሉና ማሳደዱ ዛሬ በአማራው ላይ ነገ ደግሞ በተረኛው ላይ ይቀጥላል። 27 ዓመት፣ “የዚህ አካባቢ መሬት የአንድ የተመረጠ ብሔር ብቻ ነው” ስትል ከከረምክ፣ “ከምርጡ” ብሔር ውጭ ያሉ ሰዎች በማንኛውም ጊዜ፣ በማንኛውም ምክንያት ሲባረሩ ራስህን ገላጋይና አስተዛዛኝ አድርገህ ማቅረብ አትችልም። ችግሩን የጥቂት መጥፎ ሰዎች ችግር አስመስሎ ማቅረብም ማድበስበስ ነው።
እገሌ የሚባል ወረዳ ላይ የሚኖሩ ሰዎች ከመሬቱ ጋራ ያላቸው ግንኙነት ከዜግነታቸውና ከንብረት ባለቤትነት ብቻ የሚመነጭ እስካልሆነ ድረስ ከምርጡ ብሔረሰብ ያልወጡ “መጤዎችን” ማባረር ስህተት የሚሆነው በሁለተኛ ደረጃ ምክንያቶች ብቻ ነው። እነዚህ ምክንያቶች ለምሳሌ ሰዎቹ ሲባረሩ በተገቢው አካሄድ ካልሆነ፣ አካላዊ ጥቃት ከተፈጸመባቸው ወዘተ ናቸው። ውጭ አገር የሥራ ፈቃድ ተሰጥቶት ከሚሠራና ሲያስፈልግ ፈቃዱ ተሰርዞ ወደመጣበት እንዲሄድ ከሚጠየቅ ሰው ብዙም የተለየ መብት የላቸውም ማለት ነው። ይህን ዝሆን እዚህ ጎልተን፣ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ጨ ተዘዋውሮ ስለመስራት ያወራል የሚለውን ጨዋታ ለቀልድ አዋቂዎች እንተወው።
ሁልጊዜም ተባራሪ ከሌላ “ክልል” መጥቷል የሚባል እና በብሔሩ ከአባራሪው የተለየ የሚሆነው በአጋጣሚ ወይም በወረዳ አስተዳዳሪዎች ስሕተት/ክፋት አይደለም።
“ወንድሞቻችን ስለሆኑ መባረራቸው አግባብ አይደለም” የሚለው ማስተዛዘኛ ሰብአዊና ተገቢ ቢሆንም የችግሩን ምንጭ ሳይጋፈጡ ለማለፍ የሚመዘዝ ማጭበርበሪያም ሆኖ ሲያገለግል እታዘባለሁ። የዜጎች መብት መመስረት ያለበት ከማንኛችንም ወንድማዊ ስሜት ወይም አዘኔታ ሳይሆን ከዜግነትና የእኩል ባለቤትነት መብት ብቻ ነው።
Filed in: Amharic