>

ታላቁ የዓድዋ ድል የማንቂያ ደወል የሆነላቸው የአፍሪካ ልጆች የመሰረቱት O.A.U  አምደጽዮን ሰርጸድንግል

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ “የአፍሪካ ኅብረት – AU”) የተመሰረተው ከዛሬ 55 ዓመታት በፊት (ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም) ነበር፡፡
እ.አ.አ በ1884/85 ከተካሄደው የበርሊን ጉባዔ (Berlin Conference) በኋላ ኃያላኑ የአውሮፓ አገራት የአፍሪካ አገራትን በመቀራመት የቅኝ ግዛት አደረጓቸው፡፡ አውሮፓውያኑ አገራትም በቀጥተኛ አስተዳደር እንዲሁም  በከፋፍሎ መግዛት መርሆች በመታገዝ አፍሪካውያኑን ለባርነት ዳረጓቸው፡፡ የአፍሪካን የተፈጥሮ ሀብት ለኢንዱስትሪዎቻቸው ግብዓት ወደ አገራቸው አጋዙት፡፡
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም አውሮፓዊው ወራሪ የኢጣሊያ ጦር በታላቁ ንጉሰ ነገሥት ዳግማዊ አጤ ምኒልክ በተመራው የኢትዮጵያ ጦር ሲሸነፍ በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ያሉ አፍሪካውያን ስለነፃነት በርትተው ማለም ጀመሩ፡፡ ታላቁ የዓድዋ ድል የማንቂያ ደወል ሆነላቸው፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ አፍሪካውያን በአንድም ይን በሌላ መንገድ ለነፃነታቸው መዋጋት ጀመሩ፡፡ ጋና የጀመረችው የነፃነት ችቦ በሌሎቹም አገራት አበራ፡፡
የአኅጉሩ መሪዎች በዓለም መድረክ ላይ ለበለጠ ተሰሚነትና የትብብርን ግንባር ማሳየት እንደነበረባቸው በመገንዘብና ገና ነጻ ላልወጡትም ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ሉዐላዊነት መታገል ስለነበረባቸው ዓላማቸውን ግብ ለማድረስ የሚያስችል ኅብረት/ማኅበር  ለመመስረት አሰቡ፡፡ ማኅበሩን በመመስረት ሂደት ላይም ኢትዮጵያና ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡት አገራት በሁለት የተለያዩ ጎራዎች ተከፈሉ፡፡
አንደኛው ቡድን ራሱን ‹‹የዘመናዊ ተራማጅ›› ብሎ የሚጠራው ‹‹የካዛብላንካ ቡድን›› ሲሆን የቡድኑ አባላት በፖለቲካና በኢኮኖሚ የተዋሃደች የአፍሪካ ፌደሬሽንን የመመስረት ዓላማና የግራ ዘመም ፖለቲካ አቀንቃኝ በሆኑ መሪዎች የተዋቀረ ነበር፡፡ በዚህ ጎራ የተሰለፉት አገራት ጋና፣ አልጄሪያ፣ ጊኒ🇬🇳፣ ሞሮኮ🇲🇦፣ ግብጽ🇪🇬፣ ማሊ🇲🇱 እና ሊቢያ 🇱🇾ሲሆኑ የቡድኑ መሪም  የወቅቱ የጋናው ፕሬዝደንት ክዋሜ ንክሩማህ ነበሩ፡፡
ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ‹‹የሞንሮቪያ ቡድን›› ሲሆን የአፍሪካ አገራት ያለፖለቲካዊ ውህደት በኢኮኖሚያዊና በሕዝብ ለሕዝብ ትስስሮች ተባብረው መዝለቅ እንዳለባቸው ያምናል፡፡ በዚህ ጎራ የነበሩት አገራት ሴኔጋል🇸🇳️፣ ናይጄሪያ🇳🇬️፣ ላይቤሪያ🇱🇷️ እና ኢትዮጵያ 💚💛🧡 ነበሩ።
🔯🔯🔯
በመጨረሻም በወቅቱ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ታላቅ ጥረትና በንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድጋፍ ሁለቱም ወገኖች አዲስ አበባ ላይ እንዲገናኙ በተደረገው ጥሪ መሠረት ግንቦት 14 ቀን 1955 ዓ.ም የ32 ነጻ አገራት ተወካዮች አዲስ አበባ ላይ ለስብሰባ ተቀመጡ፡፡ ከሦስት ቀናት ውይይት በኋላም፣ ግንቦት 17 ቀን 1955 ዓ.ም አገራቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የስምምነት ውል (OAU Charter) ሲፈርሙ የድርጅቱ ምስረታ እውን ሆነ።
በወቅቱም የአገራቱ መሪዎች ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ፣ ጸሐፌትዕዛዝ ክቡር አቶ አክሊሉ ሀብተወልድና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ከተማ ይፍሩ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ላቅ ያለ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ በርካታ ወገኖች ለቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ‹‹የአፍሪካ አባት›› የሚል ስም ሰጥተዋቸዋል፡፡

ጃንሆይ – የአፍሪካ አባት! 

Filed in: Amharic