>

በደም የደለበው ኢፈርትና ሜቴክ ሳይፈርስ በኢትዮጵያ ሰላም ይሰፍናል ማለት ቀልድ ነው!!! (መሳይ መኮንን)

ዶ/ር አብይ ሜቴክን በተመለከተ ሹም ሽር አድርገዋል። ደመቀን አንስተው አምባቸውን ተክተዋል። ወ/ሮ አዜብንና አቶ አስመላሽ ወልደስላሴን በቦርድ አባልነት ሰይመዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሜቴክና በኢፈርት ላይ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ይጠበቁ ነበር። ህወሀት ኢትዮጵያን እንደ ጥገት ላም እያለበ፡ በአጥንቷ እንድትቀር ያደርጋት በእነዚህ ተቋማት አማካኝነት ነው። ዓይን ያወጣ ዘረፋ የሚከናወንባቸው እነዚህ ተቋማት ህወሀትን በኢኮኖሚ ጡንቻው እንዲፈረጥም በማድረግ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ያስከተሉ ለመሆናቸው በርካታ አስረጂ መረጃዎችን በማቅረብ መግለጽ የሚቻል ነው። የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመቀየርና ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት እነዚህ ተቋማት ላይ የሚወሰድ እርምጃ ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል።
የትግራይ መልሶ ማቋቋሚያ ድርጅት ኢፈርት በኢትዮጵያውያን ደም የደለበ ተቋም ነው። የህወሀት መሪዎች ጫካ እያሉ ከኢትዮጵያ ባንኮች እየዘረፉ የመሰረቱት፡ የአራት ኪሎን ቤተመንግስት ከተቆጣጠሩ በኋላ ደግሞ ከንግድ ባንክ በተበላሸ ብድር ስም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በመውሰድ ያፋፉት የግፍ ድርጅት ነው። በሀገሪቱ የሚሰሩት ግዝፍ ፕሮጀክቶችን ያለጨረታ እየወሰደ ከጥራት በታች እየሰራ፡ ከበጀት በላይ እየተከፈለው ሽቅብ ወደሀብቱ ጣሪያ በአጭር ጊዜ ተምዘግዝጎ የወጣ መሆኑ ሀቅ ነው።
አቶ ስብሃት በአሜሪካን ድምጽ አንድ ወቅት ላይ እንደነገሩን ኢፈርት የሀገሪቱን ከሲሶ በላይ ኢኮኖሚ ተሸክሟል። የኦዲት ምርመራ አይቶ የማያውቀው፡ በትግራይ ህዝብ ስም በጥቂት የህወሀት መሪዎች የሚዘውረው ኢፈርት በኢትዮጵያ ኢፍትሃዊ የኢኮኖሚ ውድድር እንዲኖር በማድረግ ብዙዎችን ነባር የሀገሪቱን የኢንዱስትሪ ተቋማት ከጨዋታ ውጪ አድርጎ በብቸኝነት መላ ሀገሪቱን የተቆጣጠረ የአፓርታይድ ድርጅት ነው።
አንድ ዘለላ ቡና በማታመርተው የትግራይ ክልል የሀገሪቱ ትልቁ የቡና ኤክስፖርት የሚያደርገው የጉና ንግድ የዚሁ ኢፈርት አባል ድርጅት መሆኑን ከብዙ በጥቂቱ መጥቀስ ይቻላል። ምርጥ ምርጡ ለኢፈርት ሆኖ አያሌ የሀገሪቱ ትርፋማ ተቋማት በኪሳራ የተዘጉት ለዚሁ የግፍ ተቋም ተብሎ ለመሆኑ በተለያዩ ጥናቶች ተመስክሯል።ኢፈርት እያለ በኢትዮጵያ ፍትህ አይኖርም። በደም የደለበው ኢፈርት ሳይፈርስ በኢትዮጵያ ሰላም ይሰፍናል ማለት ቀልድ ነው።
የኢትዮጵያ መሰረታዊ የብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን(ሜቴክ) ሌላው በኢትዮጵያውያን ደም የተገነባ ተቋም ነው። አቶ መለስ ዘረፋው በህጋዊ መንገድ እንዲከናወንና ለጄነራሎቻቸው ጡረታ መውጪያ እንዲሆን በሚል ያቋቋሙት ሜቴክ ይሉኝታ በሌለው መልኩ ሀገሪቱን ሲግጥ የከረመ ተቋም ነው። ከኢፈርት ጋር በጥምረት በመሆን ትልልቅ ፕሮጀክቶችን እየተረከበ በደካማ ውጤት ሀገሪቱን መጫወቺያ ያደረገው ሜቴክ በቢሊዮን ዶላሮች ኪሳራ መጠየቅና መከሰስ ሲገባው ያለጨረታ ፕሮጀክቶችን እየተሰጠው፡ ያለመያዣ ቢሊዮን ብሮችን በብድር በመውሰድ በአሳፋሪ ታሪኩ እንዲቀጥል ተደርጓል።
77ቢሊየን ብር ወስዶ አንድም የስኳር ፋብሪካ ሳይገነባ ሌላ ተጨማሪ ገንዘብ ያለሀፍረት የሚጠይቀው ሜቴክ፡ በሀገሪቱ ፓርላማ ጉዳዩ ቀርቦ ”ጄነራሎቹ መስዋዕትነት የከፈሉ በመሆናቸው አትንኳቸው” የሚል ዓይነት አስተያየት በእነአባይ ነፍሶ ተሰጥቶ በዝምታ የታለፈ ተቋም፡ ነው። ሜቴክ መፍረስ አለበት። በዘረፋ የተዘፈቁ ጄነራሎቹ በህግ መጠየቅ አለባቸው። ይህ ባልሆነበት በኢትዮጵያ ለውጥ የሚታሰብ አይሆንም። እነሜቴክ ጫፋቸውን የሚነካ ሳይኖር ኢትዮጵያውያን የሚናፍቁትን ለውጥ ማምጣት አይቻልም።
ዶ/ር አብይ የምር ለውጥ ማምጣት ከፈለጉ በእነዚህ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። በዘር መስመር የተገነቡትን ኢፈርትንና ሜቴክን በህጋዊ መንገድ እንዲወረሱ ተደርጎ ከእንደገና በአዲስ መዋቅር ተጠያቂ በሆነ ኢትዮጵያዊ አመራር እንዲተዳደሩ ማድረግ በትንሹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚጠበቅ ውሳኔ ነበር። በዘረፋው የተጠመቁትን በህግ እንዲጠየቁ ማድረግም የለውጡ አንዱ አካል በሆነ ነበር።
እንደምንሰማው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢፈርትንና ሜቴክን ጫፋቸውንም የሚነኩ አይደሉም። ዳር ዳሩን ከማከክ ውጪ ምንም ለውጥ እንደማያመጡ የዛሬው ሹመትና ሽረታቸው ምስክር ሆኗል። እነዚህን የደም ተቋማት ከማፍረስ ይልቅ ሰዎቹን አባብሎ በነበሩበት እንዲቀጥሉ ማድረግን የመረጡ መስለዋል። ሰሞኑን የትግራይ ተወላጆችን ሰብስበው የሚከሰስ እንደማይኖርም ቃል ገብተዋል። የሆነ የያዛቸው ነገር እንዳለ መረዳት ይቻላል። ምናልባት ሰዎቹን በዝግታና በሂደት ከአጠገባቸው ለማጥፋት በሚል ለጊዜው ስር ነቀል እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥበው ሊሆን ይችላል። ከግምት ውጪ የምናውቀው ነገር የለም። እነዚህን ተቋማት አሁን በያዙበት መልኩ እንዲቀጥሉ መፍቀድ ግን አደገኛ አካሄድ ነው።
 እንደደቡብ አፍሪካው አፓርታይድ ስርዓት ህወሀቶች የኢኮኖሚ የበላይነቱን ይዘው እስከወዲያኛው እንዲቀጥሉ መንገዶች የተከፈቱላቸው ይመስላል። ህወሀት ከፖለቲካ መድረኩ ዞር እንዲል ቢደረግ እንኳን በኢኮኖሚው ጡንቻው እንደፈረጠመ የሚዘልቅ ከሆነ ለኢትዮጵያውያን ለውጥ አይሆንም። አደገኛው አካሄድም ይሄው ነው።
ህወሀት በነበረው መልኩ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ይለኝም። በሌላ ቅርጽና መልክ ሊመጣ የሚችልበት እድል ሊኖረው ይችላል። ህወሀት ከኢትዮጵያ ገጽ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ ያለበት ዘረኛና ወንጀለኛ ስብስብ መሆኑን ከተማመንን በየትኛውም ፎርም ዳግም ልናየው መፍቀድ አይኖርብንም። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አያያዝ ህወሀትን የማባባል እንዳይሆን እሰጋለሁ። እነአባይ ነፍሶን በየቦርዱ ውስጥ ስናያቸው፡ ሌሎች የህወሀትና የህወሀት ጠበቃ የሆኑ ባለስልጣናት በተለያዩ ሹመቶች ዳግም ብቅ ማለታቸው አንድ ጥያቄ እንዳነሳ እገደዳለሁ። ”እውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህወሀት ተጽዕኖ መላቀቅ አልቻሉምን?”
Filed in: Amharic