>
5:13 pm - Sunday April 19, 5581

ባንድ መንግሥት ግዛቶች ውስጥ የብሔራዊ እና አካባቢያዊ ቋንቋ አተገባበር (ከይኄይስ እውነቱ)

 

እንደ ኢትዮጵያ አያሌ ጎሣዎች በሚኖሩባት እና በርካታ አካባቢያዊና ቀበሌያዊ ቋንቋዎች በሚነገርባት አገር ብሔራዊ ወይም አገር አቀፍ የሥራ ቋንቋ የአንድ አገርን ሕዝብ አንድነት ወይም ውህደት ከሚያጠናክሩ አያሌ መሣሪያዎች አንዱ ነው፡፡ ለዚህ አስተያየት ዓላማ ብሔራዊ ቋንቋ በረጅም ጊዜ የታሪክ ሂደት በአብሮነት በሚፈጠር ትሥሥር የአንድ አገር ሕዝብ እውቅና ሰጥቶት አብዛኛው ሕዝብ ለጋራ መግባቢያነት የሚጠቀምበት መንግሥታዊ እና በማኅበራዊ ግንኙነትም በስፋት ሥራ ላይ የዋለ ይፋ ልሳን ነው፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የወያኔ ትግሬ አገዛዝ በፈጠራቸው አገራዊ ምስቅልቅሎች ምክንያት ኦሮሞ ወገኖቻችን በሚኖሩበት አካባቢ የአማርኛ ቋንቋ በመደበኛ ትምህርት ውስጥ ተካትቶ እንዲሰጥ፤ የኦሮምኛ ቋንቋ ከባዕዱ ላቲን ይልቅ በግእዝ ቢሰጥ ስላለው ጠቀሜታ እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች ውስጥ አብዛኛው ነዋሪ የሚናገረውን ልሳን የማያውቁ በቊጥር አናሳም ይሁኑ በርካታ ነዋሪዎች የሚግባቡበት ብሔራዊ ቋንቋ ወይም በጋራ ያግባባናል ብለው የመረጡት ቋንቋ በተጨማሪነት በሥራ ቋንቋነት እውቅና ተሰጥቶት ሥራ ላይ እንዲውል ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ኢትዮጵያውያን እየጠየቁ ይገኛሉ፡፡ ጥያቄው ተገቢና አስፈላጊ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መፍትሄው የሚገኘው በጥገናዊ ወይስ በመሠረታዊ ለውጥ፤ በችሮታ ወይስ በመብትነት የሚለው ደግሞ ሌላ ጉዳይ ይመስለኛል፡፡ ይህን ርእሰ ጉዳይ ጨምሮ ስለ ብሔራዊ ቋንቋ ሙያዊና ሳይንሳዊ ትንታኔውን ከዋኖቻችን አንዱ ለሆኑትና እጅግ ለማከብራቸው ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ እተወዋለኹ፡፡

ቋንቋን/ጎሣን መሠረት ባደረገው የወያኔ ትግሬ የውሸት ፌዴራሊዝም መነሻነት ወያኔ 9 ግልጽ ወህኒ ቤቶች አቁሞ ኢትዮጵያን የትርምስምስ እና የኹከት አገር ካደረጋት እነሆ 27 የግፍና የሰቈቃ ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ለዚህ መሠረት የሆነው ወያኔ ትግሬ መክሥተ ደደቢትን መሠረት አድርጎ በግሉ የቀረፀው  የይስሙላ ‹‹ሕገ መንግሥት›› መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ስለ ወያኔ የይስሙላ ‹‹ሕገ መንግሥት›› በተለያዩ ጊዜያት ለአገራችን ይበጃል ያልኩትን አሳብ ሳካፍል ቆይቼአለሁ፡፡ www.ethiomedia.com/1000codes/fake-constitution.pdf; www.satenaw.com/amharic/archives/54863) ‹የአፈጻጸም ችግር› እያሉ የሚያፌዙት አብዛኞቹ በመለስተኛ ጥገና የወያኔን ጨካኝና አፋኝ አገዛዝ ለማስቀጠል የሚሹ ኃይሎች ይመስሉኛል፡፡ በእኔ እምነት ሙሉ ለሙሉ ሊወገዱ ከሚገባቸው ወያኔ ሠራሽ አደገኛ ነቀርሳዎች አንዱ ይህ ወያኔ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከፋፍሎ ለመበታተን በመሣሪያነት የተጠቀመበት ‹‹ሕገ መንግሥት›› ተብሎ ሊጠራ የማይገባው ብዙ ሊቃውንት ‹ሕገ አራዊት› ብለው የጠሩት በማር የተለወሰ ነገር ግን መርዘኛ ወረቀት ነው፡፡

በሕግ አቀራረፅ እና አደረጃጀት መርህ ሕዝብና መንግሥት በቃል ኪዳን የሚፈጣጠሙበት የበላይ ሕግ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም የበታች ሕጎች ሲዘጋጁ ሁሉም ክፍሎች በመርህ፣ በፍልስምና፣ በዓላማ፣ በመንፈስ ወዘተ. እርስ በርስ የተሰናሰሉና ወጥነት ያላቸው ሆነው ነው፡፡ በመሆኑም በሚዘጋጀው ሕግ የአሳብ ነቀርሳ ካለ በሽታው በመላ ክፍሎቹ መሠራጨቱ አይቀሬ ነው፡፡

አገዛዞች በመሠረታዊ ባሕርያቸው በሕግ ስለማያምኑና ከሕግም በላይ ስለሆኑ የሚያወጧቸው ‹‹ሕጎች›› ከይስሙላ ‹ሕገ መንግሥታቸው› ጀምሮ ሕገ ወጥና በዜጎች ላይ የተጫኑ የግፍ ቀምበሮቸ ናቸው፡፡ ስለሆነም እነዚህን ‹ሕጎች› ለመቀበልም ሆነ ለማክበር ቢያንስ የሞራል ግዴታ የለብንም፡፡ ወያኔ/ሕወሓት በውሸት ፌዴራላዊ ሥርዓት ስም ላቆማቸው 9 የግጭት አጥሮች ያስቀመጣቸው ሎሌዎች እንዲያስፈጽሙት ጽፎ የሰደደላቸው ሰነድም በየትኛውም መመዘኛ ‹የአካባቢ ሕግጋተ መንግሥት› አይደሉም፡፡  ስለሆነም እነዚህ በደቡብ አፍሪቃው የጥቂት ነጮች አገዛዝ በተከላቸው 10 የባንቱስታን ግዛቶች (Bantustan or Homelands) አምሳል የተቀረፀውን ‹ክልል› የተባለ የእሾኽ አጥር መቀበል አገዛዙን ከመቀበል ተነጥሎ አይታይም፡፡ በእሾኽ ወይም በሚዋጋ ሽቦ የተሠሩትን አጥሮች አፍርሰን ትክክለኛ አስተዳደራዊ ግዛቶችን/ክፍላተ ሃገራትን ማዋቀር ካልቻልን በቋንቋ ሆነ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች የምንሻውን መፍትሄ ማግኘት የሚቻል አይመስለኝም፡፡

ኢትዮጵያ አገራችን ከገባችበት ዐዘቅተ ዐዘቅታት ለመውጣት መፍትሔው ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያዳርስ ሥር ነቀል ለውጥ ነው ብለን የምናምን ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሥር ነቀል ለውጥ ከሚያስፈልጋቸው አገራዊ ጉዳዮች አንዱ ወያኔ የተከለብን ደንቃራ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› አንዱና ዋነኛው ነው፡፡

ላንድ መንግሥት ዓምድ የሆነው የፍትሕ አስተዳደር አፈር ድሜ በበላበት፣ ዜጎች በማንነታቸው በጅምላ በሚገደሉበት፤ እንደ መጤ/ባይተዋር አገራችሁ አይደለም እየተባሉ ከየክፍላተ ሃገራቱ እትብታቸውን ቀብረው÷ ወልደው ከብደው ሃብት ንብረት አፍርተው ከኖሩበት ቀያቸው በግድያ÷ በድብደባና በግፍ በሚፈናቀሉበት፤ ካንድ መንደር ተሰባስበው የመጡ ተራ ማጅራት መቺዎችና በሎሌነት ያደሩላቸው ግብረ አበሮቻቸው የአገሪቱን አንጡራ ሃብትና ንብረት ያለምንም ጠያቂ በሚዘርፉበት፤ በጉልበት የያዙትን የፖለቲካ ሥልጣንና በዚሁ ያገኙትን ጥቅም ለማስጠበቅ የግላቸውን ሠራዊት፣ ደኅንነት፣ መረጃና ወህኒ ቤት ባደራጁበት፤ መንግሥታዊና የሃይማኖት ተቋማትን በሙሉ የግል ገንዘባቸው ባደረጉበት ወዘተ. ወዘተ. ወዘተ. (መዘርዘሩም ያማል)  የአገዛዝ ዘመን ‹ሕገ መንግሥት› አለ ብሎ መናገር እጅጉን ያሳፍራል፡፡ የሕግ የበላይነት ሳይሆን የሰዎች አገዛዝ የሠለጠነበት ለማለትም አልመች አለኝ፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ጉዶች አገርና ሕዝብ ጠልተው÷ ከባዕድ ጠላትም ከፍተው÷ ከኅሊናቸው ተፋትው÷ ባጠቃላይ ከሰብአዊነት ባሕርይ ተራቁተው ያሉ ‹አውሬዎች› በመሆናቸው የሰዎች አገዛዝ የሚለውም አልመጥናቸው ቢለኝ ነው፡፡ ከአገዛዞችም ‹አገር ወዳዶች›÷‹ቸር› አምባገነኖች/ፈላጭ ቆራጮች አሉና፡፡

ሰው መሆን ከዚያም ወረድ ሲል ኢትዮጵያዊ ዜግነት የብሔራዊ ማንነት መገለጫ የመብትና ነፃነት መጎናጸፊያ እንዲሁም ግዴታና ኃላፊነትን ለመቀበል መሠረት ቢሆን፤ የሕግ የበላይነት (በሕግ መተዳደርና ማስተዳደር እንዲሁም በሕግ ፊት እኩል መታየት፣ ከሕግ አግባብ ውጭ ማንኛውም ዜጋ መብቱንና ነፃነቱን አለማጣት ወዘተ.) ቢኖር፤ የሕግ መሠረት ያላቸው ዘላቂ የዲሞክራሲ ተቋማት ቢኖሩን፤ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ተቋማት ተገቢውን ቦታና ክብር ቢሰጣቸውና የአገዛዝ መሣሪያዎች ባይሆኑ፤ የማኅበረሰብ (civic) ተቋማት በነፃነት ተደራጅተውና ተጠናክረው የሚጠበቅባቸውን ግዴታዎች በመወጣት ተራው የማኅበረሰብ አባል ጋር ቢደርሱለት፤ የፖለቲካ ማኅበራት በጎሣ ሳይሆን ለሕዝብና አገር በሚበጅ ሃሳብ ዙሪያ ተሰባስበው በነፃነት በመደራጀትና በመንቀሳቀስ የሕዝብን ንቃተ ፖለቲካ ከፍ ቢያደርጉ፤ ባጠቃላይ መርህን መሠረት ያደረገ እና የሕብረተሰባችንን መሠረታዊ የጋራ እሴቶች ያገናዘበ ፍልስምና ላይ የተደራጀና የተዘረጋ ሥርዓት ቢኖረን ኖሮ ወዘተ. በሰዎች ፈቃድና ምኞት ያውም በዘፈቀደ በሚመራ በተለይም ሰብአዊ ባሕርያቸውን ባጡ ወፈፌዎች አገር ምስቅልቅሏ ባልወጣ ነበር፡፡

ዛሬ እነዚህ መሠረታዊ የአገር ንጣፎች ስለሌሉን በቋንቋ በተሸነሸኑት የኢትዮጵያ ግዛቶች የሚኖሩ ዜጎች አንዱ ነባር ሌላው ‹መጤ› ተብሎ ከሕይወት/ኑሮ ዋስትናው ጀምሮ በሚኖርበት አካባቢ ቢያንስ በብሔራዊ ቋንቋ ለመስተናገድ የገዢዎችን/የግለሰቦችን መልካም ፈቃድ መሻቱ የወረድንበትን መጨረሻ የሌለው ዐዘቅት አንዱ ማሳያ ይመስለኛል፡፡ አንድ ማኅበረሰብ በመረጠው/አፍ በፈታበት ቋንቋ መጠቀሙ፣ ቋንቋውንም ማዳበር/ማበልጸጉ መሠረታዊ መብትና አስፈላጊም ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት ባለበት አገር በዚህ ረገድ የመንግሥት ድርሻ መፍቀድና መከልከል ሳይሆን የብዙኃኑን ብቻ ሳይሆን የአናሳውንም ነዋሪ መብት ማስጠበቅ ነው፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ እንደሁኔታው ብሔራዊ ቋንቋን ወይም በቊጥር አነስተኛ የሆኑትና ብዙኃኑ የሚጠቀምበትን ቋንቋ የማያውቁት ወገኖች በመረጡት ቋንቋ ቢያንስ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ኹሉ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል፡፡ አብሮነት ያለውን እምቅ ኃይል ከማሰብ ጋር ቅንነቱ ከተጨመረበት አንዱ የሌላውን ቋንቋ በመደበኛም ሆነ ኢ-መደበኛ መልኩ በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ አካትቶ (በረጅም ጊዜ ሂደት) ወደ ጋራ መግባቢያ ቋንቋ መድረስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡

በዲሞክራሲያው ሥርዓት ዜጎች የአገራቸው ባለቤቶች ሲሆኑ፣ መብትና ነፃነታቸው ሲከበር፣ እውቀት÷ ጥናትና ምርምር ተገቢ ቦታቸውን ሲያገኙ፤ በዚህ ክፍለ ሃገር ይህ ቋንቋ በተጨማሪነት የሥራ ቋንቋ እንዲሆንልን በማለት የግለሰብ ባለሥልጣናትን መልካም ፈቃድ መጠየቅ አያስፈልግም/ተገቢም አይደለም፡፡ በመለማመጥና ማንም በችሮታ የሚሰጠውም ጉዳይ አይደለም፡፡ ሕግንና የተዘረጋውን ሥርዓት መሠረት አድርጎ የሚፈጸም የመብት ጥያቄ እንጂ፡፡ ጥገናው ጊዜያዊ መፍትሄ ቢመስልም ያለውን ‹ሥርዓት› ለማስቀጠል ያለመ ከሆነ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ስለሆነም ለጥገናው ሳይሆን ለዘላቂው መሠረታዊ ለውጥ እንሥራ፡፡ በርግጥ ሁሉ ነገር በሕግ ላይፈታ ይችላል፡፡ ለዘመናት ሲንከባለል መጥቶ እንደ ተራራ የተከመረው ውስብስብ የኢትዮጵያ ችግር እስከ ታችኛው የአስተዳደር ዕርከን ወርዶ ሕዝብን ባሰተፈ መልኩ መወያያትን፣ መደማመጥንና በፈቃድ ላይ የተመሠረተ መግባባትን ይጠይቃል፡፡ እውነተኛ የፌዴራላዊ ሥርዓት ካሉት ተግዳሮቶች አንዱ ብዝኀ ጎሣ ባለበት አገር አካባቢያዊ ብዝኀነትን እና የብሔራዊ አንድነትን ሚዛን ጠብቆ የማስጓዙ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም የተጠና ሕገ መንግሥታዊና የፖሊሲ ርምጃዎችን ይጠይቃል፡፡

Filed in: Amharic