>
8:34 am - Sunday January 29, 2023

በኢህአዴግ ውስጥ ያለው የሃይል አሰላለፍ!!! (ፋሲል የኔአለም)

ዶ/ር አብይ ጠ/ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ ወዲህ በሁሉም ወገን ያለው ግራ መጋባት እንደቀጠለ ነው። በተቃውሞው ጎራ ትልቅ የመረጃ ክፍተት ያለ ይመስለኛል። ትንታኔዎች ይበዛሉ ነገር ግን ትንታኔዎች በጠንካራ መረጃዎች ካልተደገፉ፣ መረጃዎችም እንዲሁ በትንታኔ ካልዳበሩ ሁለቱም ዋጋ የላቸውም። ብዙዎቻችን የመተንተኛ መሳሪያዎችን እናውቃቸዋለን፣ ችግራችን የሚተነተነውን ተጨባጭ መረጃ ማግኘቱ ላይ ነው። አሁን በተቃውሞው ጎራ የሚታየው ግራ መጋባት ከመረጃ እጥረት የሚነሳ ይመስለኛል። በገዢው ፓርቲ በኩል ያሉ ሰዎች ደግሞ መረጃው አላቸው ነገር ግን ትንታኔ ላይ ችግር አለባቸው። ችግራቸው የመተንተኛ መሳሪያዎችን ሳያውቁ ቀርተው ሳይሆን፣  ትንታኔውን ከራስ ጥቅም በተላቀቀ መንገድ ለመተንተን አለመቻለው ነው። ለማንኛውም በእኔ በኩል አንዳንድ የሰማሁዋቸውን መረጃዎች ማካፈሉ ለተንታኞችም ለአጠቃላይ ትግሉም ይጠቅም  ይሆናል በሚል እምነት የተወሰኑትን ብቻ እንዲህ ጽፌያቸዋለሁ፦
1ኛ ኢህአዴግ ከሁለት መከፈሉ ግልጽ ነው። በአንድ በኩል በቀድሞው አካሄድ መጓዝ የሚፈልጉ በሌላ በኩል ደግሞ በአዲስ አስተሳሰብ መመራት የሚፈልጉ( በአብዛኛው ወጣቶችን ያቀፉ) ቡድኖች  አሉ። በኢህአዴጎች መካከል ያለው ጦርነት እስከ ነሃሴው የድርጅቱ  ስብሰባ ድረስ ይቀጥላል። ከዚያ በሁዋላ ምን እንደሚፈጠር አይታወቅም፤ ለውጥ ፈላጊው ያሸንፋል ወይም ይሸነፋል። ለውጥ ፈላጊዎችን ከደገፍናቸው የማሸነፍ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል።
2ኛ ዶ/ር አብይንም ሆነ  የኦህዴድና የብአዴን አመራሮችን በጅምላ የህወሃት ተላላኪ አድርጎ መፈረጁ ትክክል አይደለም። አብይን ነጥሎ የለውጡ ብቸኛ “ስትራቴጂስት” አድርጎ መሳሉም እንዲሁ ትክክል አይደለም።
3 ለውጥ ፈላጊው ቡድን በዋናነት የሚመራው በለማና በደመቀ  ነው። ገዱም ዋናው የለውጡ ደጋፊ ሆኖ ከአቶ ደመቀ ጋር በጥምረት የሚሰራ ነው። እስካሁን የለውጡ አቀንቃኞች ለውጡ ጥገናዊ እንዲሆን የመፈለግ አዝማሚያ አይታይባቸውም። ታሪክ የመቀየር ፍላጎት እንዳላቸው ይነገራል።
4 ለአብይ መመረጥ ትልቁን ሚና የተጫወተው ደመቀ መኮንን ነው፤ ከተወዳዳሪነት በመውጣት ብቻ ሳይሆን በኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ባሳየው ድንቅ መድረክ የመምራት ችሎታው ቀጣዩን መንገድም የሰመረ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል። ድሮ ስለደመቀ የምንሰማውና የዛሬው ደመቀ ፍጹም የተለያዩ መሆናቸውን የብአዴን አባላት የሚመሰክሩት ነው።  ደመቀ በምርጫ ያልተወዳደረው ለአብይ እድሉን ለመስጠት ብቻ ሳይሆን ሌሎች  ምክንያቶችም አሉ። ሃይለማርያምም እንደተነገረለት ስልጣን በፈቃዱ ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረበው በስልጣኑ እንደማይቆይ ስላወቀ ነው፤ በሴራ ፖለቲካ ውስጥ እጅ ከፍንጅ የተያዘበት ስራ ሲሰራ መገኘቱንም ከእሱ ጋር በቅርብ ሲሰሩ የነበሩ ሰዎች የሚመሰክሩት ነው።
5 ለውጡን ለማደናቀፍ  እየሰሩ ያሉት በብአዴን በኩል በረከት፣ አለምነው፣ ዝማም፣ ፍሬህይወት፣ ገነት፣ ከበደ፣ አዲሱና ህላዊ በዋናነት ሲጠቀሱ፣ ህወሃት ከጀርባ ሆኖ ድጋፍ ይሰጣቸዋል። እነዚህ ሰዎች የደመቀንና ገዱን ቡድን ለመምታትና ብአዴንን ለህወሃት ለማስረከብ ከፍተኛ ስራ እየሰሩ ነው። ደግነቱ አብዛኛው ለውጥ ፈላጊው የብአዴን ወጣት አመራር ከእነ ገዱ ጋር መሰለፉን በርካታ አባላቱ የሚገልጹት ሃቅ ነው። ህወሃት ከኦህዴድ በኩል የሚያሰልፈው ተላላለኪ በማጣቱ ችግር ውስጥ ወድቋል፤ ለማ በወሰደው “ቆራጥ” እርምጃ ኦህዴድ ውስጥ ያሉ የህወሃት ተላላኪዎች ተጠራርገው ወጥተዋል። ህወሃት በኦህዴድ በኩል በረከቶችን  ማግኘት አልቻለም። ለማ መገርሳን የገጠመው ፈተና ህወሃትን እንቃወማለን የሚሉ በአብዛኛው በውጭ ያሉ “ የኦሮሞ አክቲቪስቶች” የሚፈጥሩበት ጫና ነው። አሁን በሚያደርጉት ቅስቀሳ ለማን ህዝባዊ ድጋፍ ካሳጡት፣ በህወሃት ሊበላ ይችላል።  ልብ በሉ! እነ ለማና ገዱ ( ደመቀ) ተሸንፈው እነ በረከት ካሸነፉ ( የማሸነፍ እድላቸው ዝቅተኛ ቢሆንም) በዚች አገር ላይ ከፍተኛ ጉዳት ይደርሳል ።
6 አብይ ያለ ለማ እና ገዱ( ደመቀ)  እንዲሁም ያለ ህዝብ ድጋፍ በሚቀጥሉት ወራት ከህወሃት እና ከእነበረከት ጋር የሚኖረውን ጦርነት በአሸናፊነት ለመወጣት አይችልም። የአብይ ቀጣዩ የለውጥ አጀንዳ በመከላከያውና ደህንነቱ ላይ በመሆኑ ፍልሚያው ቀላል አይሆንም።
በአጭሩ፣ የተቃውሞው ጎራ ኢህአዴግን በጅምላ መቃወሙ ትክክል አይመስለኝም። አዲስ አስተሳሰብ እንከተል የሚሉትን ቡድኖች ለይቶ መደገፍ ከስትራቴጂ አንጻር በጣም አዋጪ ነው። እኛ ከምናስበው በላይ በመካከላቸው ከፍተኛ ጦርነት እየተካሄደ ነው። አንገቷ የረዘመ ኢትዮጵያን ማየት የሚፈልጉት ሃይሎች ትግላቸውን በብልጠትና በጥንቃቄ ማካሄድ እንደለባቸው አምናለሁ።
Filed in: Amharic