
አሁን የማየው ነገር ግን ፍፁም የተለየ ነው፡፡ በቂም-በቀል አስተምህሮት የዛገው አዕምሮዬ በዶ/ር አብይ ይቅር-ባይነት እና አክብሮት ግራ ተጋብቷል፡፡ በእርግጥ መሆን ያለበት እንደሆነ፣ ሊደረግ የሚገባው ነገር እንደተደረገ አውቃለሁ! እንደው የለመድኩት ቂምና ጥላቻ፥ እልህና በቀል መቅረቱን ማመን አቃተኝ፡፡ የማየው ነገር ብርቅ ሆነብኝ፡፡ ይሄ ነገር በህልሜ እንዳይሆን እባካችሁ ቀስቅሱኝ? ስሞትላችሁ “እውነት ነው” በሉኝ? “የቂም-በቀል ፖለቲካ አልፏል!” በሉኝ? “የይቅርታና አብሮነት ዘመን ተጀምሯል”፣ “የዱክማኖች ፖለቲካ ላይመለስ ሄዷል በሉኝ?”… እባካችሁ አትፍረዱብኝ፣ ቂም-በቀል ስማር ነው ያደኩት፡፡ ልቦናዬ በጥላቻ ቆስሎ ፍቅርን መሸከም አቅቶታል! ልቤ በቂም-በቀል ደንዝዞ ይቅርታን መገንዘብ ተስኖታል!! ዘር-ማንዘሬን ቆጥሮ የሚጠላኝ፥ የሚበቀለኝ በቀለኛ መንግስት አልፏል በሉኝ፡፡ አደራ…አደራ… ነገ ጠዋት ይሄ ሁሉ “ህልም ነው” እንዳትሉኝ፡፡ ተስፋዬን አንዳታጨልሙብኝ፣ ምኞቴን አታጣጥሉብኝ… ያ… ዘረኛ፥ ቂመኛ፥ በቀለኛ፥… ስርዓት ላይመለስ ሄዷል በሉኝ፡፡