>

ፍላጎታችን ባይሆንም እንኳን… የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ልናከብር ይገባል! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በ35ኛው የሰሜን አሜሪካ ፌስቲቫል ላይ እንዲገኙ፤ በኢትዮጵያ ኢምባሲ በኩል በደብዳቤ ቁጥር ዋሽ/09/620/2010 ጥያቄ መቅረቡ ይታወሳል። የፌዴሬሽኑ የቦርድ አባላት ይህንን ደብዳቤ መሰረት በማድረግ ለቀናት ያህል የዘለቀ ስብሰባ አድርገዋል። የቦርድ አባላቱ ለመጨረሻ ግዜ ከአባላቶቻቸው ጋር በመምከር፤ ድምጽ እንዲሰጡ በተወሰነው መሰረት፤ ትላንት ምሽት  ድምጸ ውሳኔ ሰጥተዋል። በውጤቱም የዶ/ር አብይ አህመድን ጥያቄ አክብረው፤ ነገር ግን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚቸገሩ አሳውቀዋል።

ፌዴሬሽኑ ባወጣው መግለጫ ላይ፤ 1ኛ- ጥያቄው የቀረበው ዝግጅቱ ሊጀመር ጥቂት ሳምንታት ሲቀረው በመሆኑ፤

2ኛ- በስቴድየም ውስጥ ሊኖር የሚችለው ጭንቅንቅ ታሳቢ በማድረግ፤

3ኛ- ፌዴሬሽኑ ለህዝቡ ደህንነት የሚገባው የኢንሹራንስ ክፍያ ተፈጽሞ ያለቀ በመሆኑና አሁን እንደአዲስ ሁሉንም ነገር መጀመሩ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል በመግለጫው ላይ አሳውቋል። ሆኖም ፌዴሬሽኑ ለመጀመሪያ ግዜ፤ የኢትዮጵያ መሪ በዝግጅቱ ላይ እንዲገኝ መጠየቁ በራሱ መልካም ጅምር መሆኑንና ወደፊት በጠቅላይ ሚንስትሩ ቢሮ እና በፌዴሬሽኑ መካከል ያለው ግንኙነት እንደሚቀጥል ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን በመግለጫው ላይ አሳውቋል።

አሁን የጨዋታው ኳስ ወደ ዶ/ር አብይ አህመድ እና ወደ ህዝቡ ተመልሷል። ስለዚህ የስፖርት ፌዴሬሽኑን ውሳኔ ኢምባሲው እና ዶ/ር አብይ አህመድ በማክበር ሊቀበሉት ይገባል። ከምንም በላይ ደግሞ ህዝቡ የ31 ቡድን ተወካዮች ያሉበትንና ሃሳባቸውን በነጻነት አንሸራሽረው ድምጸ ውሳኔ የሰጡትን የአብላጫ ቦርድ አባላት ድምጽ ማክበር ይጠበቅበታል። እኛን ጨምሮ ብዙዎች የዶ/ር አብይ አህመድን በዳላሱ ዝግጅት ላይ መገኘት የምንደግፈው የነበረ ቢሆንም፤ የአብላጫ ድምጽ ውሳኔ መከበር ስላለበት፤ ፍላጎታችንን ለራሳችን ዋጥ አድርገን፤ የፌዴሬሽኑን ውሳኔ ግን ልናከብር ይገባናል – መልእክታችን ነው።

የድምጹ አሰጣ ጡም እንዲህ ነበር። የጋዜጠኛ አርአያ ተስፋማሪያምን ጽሁፍ ያንብቡ 

ዶ/ር አብይ ESFNA ላይ እንዳይገኙ ተወሰነ!??!
አርአያ ተስፋማሪያም
በሰሜን አሜርካ የኢትዮጵያ ስፖርት ፌዴሬሽን አመታዊ ውድድር ላይ በሚቀጥለው ወር ለመገኘት..ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ በአሜሪካ -የኢትዮጵያ ኢምባሴ በኩል አቀረቡት የተባለው ጥያቄ በቦርድ አመራሮች ድምፅ እንደተሰጡበት ምንጮች ገለፁ። ዛሬ ምሽት በተጠናቀቀውና 31 የክለብ አመራር ቦርድ አባላት በኢሜል በሰጡት ድምፅ 14 አባላት “ጠ/ሚ/ር ዶ/ር አብይ መገኘት የለባቸውም” በሚል ሲወስኑ፣ 11 አባላት ይገኙ ሲሉ..ቀሪ 6 አባላት ድምፀ ታኣቅቦ ማድረጋቸውን ምንጮች አስታውቀዋል። .ተሰጠ በተባለው ድምፅ የዶ/ር አብይ ጥያቄ ምላሽ እንዳላገኘ ታውቋል።
Filed in: Amharic