>

እንደ ሕገ መንግሥቱ ባድመም ጾረናም የትግራይ ክልል ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ (ውብሸት ሙላት)

ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዓላዊ አገር ድንበር የላትም!

እንደ ሕገ መንግሥቱ ባድመም ጾረናም የትግራይ ክልል ጉዳይ ብቻ ነው፡፡

(ውብሸት ሙላት)
የፌደራሉ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ ሁለት ላይ እንደተገለጸው  የአገሪቱ የግዛት ወሰን (ድንበር) የክልሎቹ ወሰን ነው፡፡ ሕገ-መንግሥቱ ሲረቀቅ ይሄም አንቀጽ በዚህ መልኩ መደንገግ እንደሌለበት፣ኢትዮጵያም እንደሌሎች ሉዓላዊ አገራት ሁሉ፣ የራሷ የሆነ ዳር ድንበርና አዋሳኞች ሊኖሯት እንደሚገባ ክርክር እንደነበር ከተለያዩ ሰነዶች መረዳት ይቻላል፡፡
 የኢትዮጵያ ድንበር ሳይቀር የሚወሰነው በክልሎች ሕግጋተ መንግሥት ነው እንደማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ክልሎች አዋሳኞቻቸውን ብሎም ድንበራቸውን የደነገጉ ቢሆንም የደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሕገ መንግሥት ግን የክልሉ ወሰን የዞኖቹ እና የወረዳዎቹ ነው በማለት ደንግጓል፡፡
ይሁን እንጂ እንኳንስ ወረዳ እና ዞን ይቅርና ከልሎችም ከሌሎች ሉዓላዊ አገራት ጋር ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን መዋዋል ስለማይችሉ ይህ ዓይነቱ በክልል፣በዞን እና በወረዳ የኢትዮጵያን የግዛት ወሰን በተለይም  ከሌሎች ሉዓላዊ አገራት ጋር የምትዋሰንባቸውን ድንበሮች መለየት ለአፈጻጸምም አስቸጋሪ ነው፡፡
ክልሎቹ ከሉዓላዊ አገራት እና ከሌሎች ክልሎች ጋር ይዋሰናሉ፡፡ ከሌሎች አገራት ጋር በሚዋሰኑበት ጊዜ ጉዳዩ ዓለማ አቀፍ ሲሆን፣ ከሌላ ክልል ጋር በሚዋሰኑበት ድንበር ምክንያት የሚነሱት ጉዳዮች ደግሞ የፌደራል ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በተቃራኒው፣ ድንበርን በተመለከተ ጥቅልል አድርጎ የክልል ማድረግ ተጠየቃዊ አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ፌደሬሽን ግዛቷ (territory)  የክልሎቹ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ነገር ግን፣ የግዛት ወሰኗ ደግሞ በጥቅሉ የክልሎቹ ሳይሆን ክልሎቹ ከሌሎች ሉዓላዊ አገራት ጋር ያላቸው ድንበር (border or boundary) ነው፡፡ ስለሆነም፣ ክልሎቹ ከሌሎች አገራት ጋር የሚዋሰኑበትን የድንበር አከላለል እና ተያያዥ ጉዳዮች በፌደራሉ መንግሥት ሥልጣን ሥር እስካልሆኑ ድረስ ሁኔታዎቹን የበለጠ ውስብስብ ያደርጋቸዋል፡፡
የፌደራሉ ሕገ መንግሥቱ ላይም ይሁን የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ላይ እንደተገለጸው ከሆነ የባድመም ይሁን በጾረናና ሌሎች የትግራይ ክልል ከኤርትራ ጋር የሚዋሰኑባቸው አካባቢዎችን የሚመለከተው ክልሉንና ኤርትራን ብቻ ነው እንደማለት ነው፡፡ ወለፈንድ (absurd) የድንበር ሕግ!!!!
እንደዚህ ዓይነቶቹ የሕገመንግሥት አንቀጾች ካልተሻሻሉ ወደፊት በርካታ ውስብስ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል፡፡ ሊያስከትል የሚችላቸውን መዘዞች ለጊዜው እንተወው፡፡ ቢያንስ ግን ለአገራዊ ግንባታ ደንቀራ ነው፡፡ መሻሻል ይገባዋል፡፡
Filed in: Amharic