>

ቁጣ፣ ክፍፍልና ትርምስ ... ኢሕአዴግ፣ ሕወሓት፣የትግራይ ህዝብ፣ ዓረና ትግራይ፣ አይጋ ፎረም እና ሌሎች የሕወሓት ሚዲያዎች (ከድር እንድርያስ)

 
#ኢሕአዴግ 
♦ የሕወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ #የኢሕአዴግን ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሰላለፈውን ውሳኔ፣ ያወጣውን መግለጫ እና ለኤርትራ መንግስትና ህዝብ ያቀረበውን የሰላም እና የጋራ ተጠቃሚነት ጥሪ #ለመሻር ወይም #ለማሻሻል በመቀሌ ተሰባስበዋል።
ሕወሓት 
♦ በሕወሓት ውስጥ ያላው ክፍፍል እየከረረ ነው። አሁን ያለው ሕወሓት የሌቦች እና የባልቴቶች ጥርቅም ነው። የትግራይ ህዝብ ተከድቷል። የአድዋ የቤተሰብ ዳይናስቲ ይወገዱ፣ ለፍርድም ይቅረቡ የሚሉ የሕወሓት ካድሬዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ሌላ #አንጃ ሊፈጠርም ይችላል። የመለስ ራዕይ ደጋፊዎች እና በቅርብ በተሐድሶ ከስልጣን የተባረሩት አመራሮችም እጃቸውን አስገብተዋል።
#የትግራይ ህዝብ
♦ የትግራይ ህዝብ ከኤርትራ ጋር ሰላም ይቅደም፣ ኤርትራውያን በደም የተሳሰርን አንድ ህዝብ ነን በሚሉ የኣግኣዚያን እንቅስቃሴ አባላት እና ሉዐላዊነታችን ይቅደም መሬታችን ለሻዕቢያ አንሰጥም፣ የአልጀርሱን ውሳኔ ፈፅሞ አንቀበልም በሚሉ የትግራይ ተወላጆች መካከል ያላው ልዩነት እየሰፋ ነው። ዛሬ በትግራይ በርካታ ስብሰባዎች በመካሄድ ላይ ናቸው።
#ዓረና ትግራይ
♦ ሕወሓት እና ዓረና ትግራይ ፍጥጫ ላይ ናቸው። የዓረና ትግራይ አመራሮች ሰሞኑን ስብሰባ ላይ ናቸው። በመግለጫቸው እንደጠቆሙት በመላ ትግራይ ታላላቅ ስብሰባዎችን እና ሰልፎችን ለመጥራት በዝግጅት ላይ ናቸው።
#አይጋ ፎረም
♦ አይጋ ፎረምን ጨምሮ ሌሎች የሕወሓት ሚዲያዎችም የትግራይ ህዝብ ከኢሮብ ህዝብ ጎን በመቆም የሕወሓት/ኢሕአዴግን ውሳኔ እንዲቃወም ጥሪ አቅርበዋል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስትን አቋም አክርረው በመቃወም ላይ የሚገኙት የሕወሓት ካድሬዎች ናቸው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መነሳት፣ የአልጀርሱ ስምምነት መቀበል፣ የእስረኞቹ መፈታት፣ የሚዲያዎች ሚዛናዊነት ማጣት፣ የኦሕዴድ እና ብአዴን አካሄድ፣ የዶ/ር አብይ ያልተጠበቁ እርምጃዎች ጥቂቶቹ ናቸው።
——————————————-
ከኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫና ጥሪ…
የኢትዮ-ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በጥልቀት በመገምገም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር የሚከተለዉን ጥሪ አስተላልፏል።
በኢትዮጵያ ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየውን አለመግባባት እንዲያቃና በሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰለም እንዲፈጠር ከኢህአዴግ የቀረበ ጥሪ!
ለኢትዮጵያችን እድገትና ለሕዝቦች ተጠቃሚነት ሰላም ከምንም በላይ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሰረት ነው፡፡ ከግለሰብ የወደፊት የማደግና መለወጥ ህልም ጀምሮ እስከ ሀገር ድረስ ሰላም ከደፈረሰ የቱንም አይነት የልማትና የዲሞክራሲ አላማዎችን ማሳካት አይቻልም፡፡
በኢትዮጵያና በኤርትራ መሃከል ከ1990 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተውን ጦርነት በአፍሪካ ከተከሰቱ የድንበር ጦርነቶች ሁሉ ደም አፋሳሹ ሲሆን፣ ከሁለቱም ወገን በርካታ ሺህ የሰው ሕይወት ሊጠፋ ችሏል፡፡ ጦርነቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከኤርትራና ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢ የመኖሪያ ቀዬ አፈናቅሏል፡፡ በሁለቱ ሀገራት መሃከል የተደረገው ጦርነት በሁለቱም ሃገራት ያሉ ቤተሰቦችን አፍርሷል፣ በድንበር አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ሁሌም ያለመረጋጋትና የስጋት ስነ-ልቦና ሰለባ አድርጓቸዋል፡፡
በድንበር አካባቢ በንግድ የሚተዳደሩ ሰዎች ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፡፡ በድምሩ ላለፉት 20 አመታት በሁለቱም ሀገራት ህዝቦች ላይ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ፈጥሯል፡፡ በመሆኑም የሁለቱ ሀገራት የወደፊት ግንኙነት ምን ሊሆን ይችላል? የሚለው ጥያቄ የአብዛኛው ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንዲሁም የዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ከጦርነቱ በኋላ በአፍሪካ አንድነት ድርጅትና በተባበሩት መንግስታት አደራዳሪነት የአልጀርሱ ስምምነት ቢደረግም ላለፉት 20 ዓመታት በሁለቱ ወንድማማች ሀገሮች መካከል ጦርነትም ሆነ ሰላም የሌለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት ወደነበረበት ለመመለስ ላለፉት ሃያ አመታት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ውጤት አላመጡም፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ጊዜ በሁለቱ ሀገራት መካከል የዕውነት ሰላም ለማስፈን ከቀድሞው የተለየ አቋምና አካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱም መንግሥታት ለህዝባቸው ምርጫና ፍላጎት ቦታ የማይሰጡ ሊሆኑ አይችሉም፡፡
እኔ እበልጥ፣ እኔ እበልጥ የሚል ፉክክር ለሁለቱም ህዝቦች የሚፈይደው ነገር አይኖርም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለአፍሪካ ቀንድ ሀገሮችና አካባቢ የፖለቲካ ቀውስ መብረድና መረጋጋት ዘላቂው መፍትሔ የኢትዮጵያና የኤርትራ ጤናማ ግንኙነት መመሥረት ነው፡፡ይህን ባለማድረጋችን በርካታ ለሁለቱ እህትማማች ሀገሮችም ሆነ ለአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ትልቅ ፋይዳ ያላቸዉ እድሎች አምልጠዉናል፡፡ የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ቀድሞም ቢሆን ወዳጅ ነን፡፡ በደም፣ በባህል፣ በቋንቋና በረጅም ጊዜ የጋራ ታሪክ የተሳሰርን ሕዝቦች ነን፡፡
በመሆኑም በጥቅም ብቻ ሳይሆን በደም ለተሳሰሩት የሁለቱ ሀገር ሕዝቦች የጋራ ጥቅም ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት የአልጀርሱን ስምምነት እና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ሙሉ ለሙሉ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ የወሰነና ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን ለመግለፅ ይፈልጋል፡፡
ይህንኑ በጋራ ተጠቃሚነትና እኩልነት ላይ የተመሰረተውን የሀገራችን ፖሊሲም አጠናክረን እንደምንቀጥል በዚሁ አጋጣሚ በድጋሚ ለማረጋገጥ እንወዳለን፡፡
የኤርትራ መንግስትም ተመሳሳይ አቋም በመውሰድ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ የሰላም ጥሪያችንን ተቀብሎ በሁለቱም ወንድማማች ህዝቦች መካከል ከዚህ በፊት የነበረውን አብሮነትና ሰላም ወደነበረበት ለመመለስና በቀጣይም ዘላቂነቱን ለመጠበቅ ለተግባራዊነቱ ያለማመንታት በቁርጠኝነት እንዲሰራ እንጠይቃለን፡፡
የኢህአዴግ ም/ቤት ጽ/ቤት 
ግንቦት 28/2010 ዓ.ም 
አዲስ አበባ፤
Filed in: Amharic