>

በ2012ቱ ምርጫ በየክልሎቹ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የሚያሳይ አጭር ዳሰሳ!!! (ኤርሚያስ ቶኩማ)

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከእለት ወደእለት አዳዲስ ነገሮችን እያሳየን ይገኛል፤ ከጥቂት ወራቶች በፊት የነበሩ አሣዛኝ ክስተቶች ጠፍቶ ህዝቡ ነገን በተስፋ መመልከት ጀምሯል፤ ኦህዴድ የሐገሪቱን ፖለቲካ ወደተለየ መንገድ መርቶታል ነገሮች በዚህ የሚቀጥሉ ከሆነ የ2012ቱ ምርጫ በሐገሪቱ የመጀመሪያው ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይሆናል ብዬ አስባለሁ። እንደሀሳቤ ሆኖ ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ከሆነ ህወሃትና ብአዴን በተፎካካሪዎቻቸው ተሸንፈው ሥልጣን ሊለቁ ይችላሉ። ለማንኛውም በየክልሎቹ ምን ሊፈጠር እንደሚችል የሚሰማኝን ላስቀምጥ።
==> በኦሮሚያ ክልል በሚደረገው ምርጫ የእነለማ መገርሳው ኦህዴድ ከኦፌኮ ከባድ ፈተና ሊያጋጥመው ቢችልም ሊያሸንፍ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም።  በኦህዴድ ውስጥ የሚገኙት የሥራ ሰው የሆኑት አመራሮቹ የህዝቡን ልብ ለማግኘት ብዙም ስለማይቸገሩ እስከ 2017 ክልላቸውን የማስተዳደር እድል ያገኛሉ ብዬ አስባለሁ። ኦህዴድ ከጎሳ ድርጅትነት አልፎ ወደሀገራዊ ድርጅትነት ቢያድግ ከክልሉ አልፎ በመላው ኢትዮጵያ መመረጥ ይችላል።
==> በአማራ ክልል ብአዴን እንደየህወሃት ተላላኪ ስለሚታይ ህዝቡ በብአዴን እምነት ይኖረዋል ብዬ አላስብም። በወጣቶች የተገነባው አዲሱ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ ስሙን ጠብቆ ህዝቡን ማሳመን ከቻለ ከብአዴን ይልቅ በምርጫ አሸንፎ ክልሉን የማስተዳደር እድል ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ።
==> የባድመ ጉዳይ እልባት ካላገኘ በትግራይ ክልል በሚደረግ ምርጫ ከሕወኃት የማይሻለው አረና የማሸነፍ እድል ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ።
==> ደቡብ ክልል አወቃቀሩ በራሱ ችግር ስላለበት በአንድነት ሊሰበስባቸው የሚችል የብሔር ድርጅት ስለማይኖር ሐገራዊ የፖለቲካ ድርጅቶች ድምጽ የማግኘት እድል ቢኖራቸውም ደኢህዴን በካድሬዎቹ አማካኝነት በሚሰራቸው ስራዎች አሸናፊ ሊሆን ይችላል።
==> አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ መስተዳድሮች ላይ እንዲሁም በከፊል ወሎ ላይ ማሸነፍ የሚችሉት ያለጥርጥር ህብረ ብሔራዊ ድርጅቶች ይሆናሉ። በተቀሩት ክልሎች ብዙም ለውጥ ይኖራል ብዬ አላስብም።
መጭውን ጊዜ እና የምርጫ ሁኔታ ሰብሰብ አድርጌ
በአጭሩ ስመለከተው:- 
– ኦሮምያ በተራማጁ መሪ መረራ እና በቀለ ገርባ እንዲሁም በተለይ በትላልቅ ከተሞችና ከተሜዎች አካባቢ በህብረብሄራዊ ድርጅቶ እንደ ጉድ ትናጣለች – ደቡብ ላይ ጠንካራ ህብረ ብሄራዊ ድርጅት ብቅ ካለ ዱክማኖቹን ነባር ድርጅቶች ግልብጥብጣቸው ነው እሚወጣው
–  ትግራይ ላይ አረና በርትቶ ከሰራ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ ውጤት ይመዘገባል
– ማሃል አገር ሸዋ የተበላ እቁብ በለው።
– አፋር ሱማሌ የቤንሻንጉልና ጋምቤላ ከህብረብሄር ይልቅ ተቀባይነት ያለው አዲስ ብሄራዊ ድርጅት ብቅ ካለ አበቃለት  ።
– አማራ ትልልቅ ስም ስብእና እና ከፍተኛ ከበሬታና የህዝብ ታማኝነት በተጨባጭ ያስመሰከሩ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን የማይደራደሩ ሃይሎችን ያቀፈ ህብረ ብሄራዊ ድርጅት ብአዴንን በዜሮ ያስወጣዋል።
እንግዲህ የምርጫው ውጤት እንደዚህ የሚሆን ከሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች ሀገሪቱን ተከፋፍለው በመያዝ ምን አይነት መንግሥት ሊፈጠር እንደሚችል መገመት ነው። ለማንኛውም የሚመጣውን መጠበቅ ነው እኔ ግን አሁን ባለው ሁኔታ  ዶክተር አቢይ እስከ2022 የሀገሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆን ዘንድ ምኞቴ ነው።
Filed in: Amharic