>

የክፉዎች ሴራ ይከሽፋል!  (ታዬ ደንድዓ )

ባለፈዉ ዓመት ኢሉ አባቦር ላይ በኦሮሞ እና በአማራ መሀከል ግጭት ተቀስቅሶ ነበር። ያ ግጭት ግብ ነበረዉ። ግቡ በሁለቱ ታላላቅ የኢትዮጵያ ብሔሮች መሀከል የነበረዉን ምናባዊ መጠራጠር ይበልጥ በማጠናከር በኢትዮጵያ ህዝብ ሰቆቃ እና ባርነት መበልፀግ ነዉ። ግን ህልም ሆኖ ቀርቷል። ግጭቱ ኦሮማራን ወልዶ የሴራኞችን ጉልበት እንዳልነበረ አድርጓል። ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ጥሩ ተስፋ ማየት እንደ ጀመረ ለማሳየት ምስክር መጥራት አያስፈልግም።
ዛሬም ሴራኞች አልተኙም። የተሸነፉበትን ስልታዊ ቦታ ስለሚያዉቁ በአሮሞ እና በአማራ መሀከል ጥርጣሬ ለመፍጠር የሞት ሽረት ትግል ላይ ናቸዉ። በራሳቸዉ ባጀት መድበዉ ትንሽ ችግር ከፈጠሩ በኀላ ነገሩን ከሚገባዉ በላይ በሚዲያ  ያራግባሉ። ኦሮሞ አማራን አፈናቀለ እያሉ የአዞ እምባ እያነቡ “ኦሮማራ ፈርሷል!” እያሉ ይጮሀሉ። ግን ከንቱ ልፋት ነዉ። ኦሮማራ ፈፅሞ አይፈርስም። ሌሎች ብሔሮችን ጨምሮ በማቀፍ የኢትዮጵያን አንድነት ብቻ ሳይሆን የምስራቅ አፍሪካን አንድነት በማይነቃነቅ መሠረት ላይ የገነባል!
ነገሮች ግልፅ መሆን አለባቸዉ። በኦሮሚያ ክልል ማንንም የማፈናቀል ፖሊሲ የለም። አላማችን ሁሉንም ብሔሮች አቅፈን በፍቅር እና በትብብር ለዘመናት የተንሰራፋዉን ሰቆቃ ከክልላችን እና ከሀገራችን ጫንቃ ላይ ማዉረድ ነዉ። በትብብር የከበደንን ሸክም ለብቻችን እንደማንወጣዉ ጠንቅቄን እናዉቃለን። ከተባበርን ደግሞ የትኛዉንም ተራራ መናድ እንደምንችል በተጨባጭ አይተናል። ስለዚህ ኦሮሚያ እንደ ክልልም ሆነ እነደ ህዝብ ሁሉንም በእኩልነት ይዞ ሀገርን ማሸገር እንጂ ወንድሞቻችንን የማግለል ህልም የለዉም። ነገር ግን ሜዳ ሁሉ ወለል አይደለም። እዝያም እዝህም ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ። ግጭት በስጋ ወንድሞች መሀከልም ይከሰታል። ችግሩ ግጭቶችን የሚናይበት መነፅር ነዉ። ቶሎሣ እና ገመቹ ወይም ኩራባቸዉ እና ወርቁ ቢገዳደሉ ነገሩ ምንም ነዉ። ነገር ግን ገመቹ እና ኩራባቸዉ ትንሽ ቢጋጩ ጉዳዪ ይከራል። ይህ እጅግ አደገኛ ነዉ። በዝህ ላይ የጠላት ሴራ አለ።
ይህን ችግር ለመፍታት መስራት ያስፈልጋል። የመጀመሪያዉ ስራ  መነፅሩን ማስተካከል ነዉ። የግለሰቦች ጉዳይ እንደ ጠቅላላ ህዝብ መታየት የለበትም። ሚዲያዎቻችን በዝህ ጉዳይ ላይ ስልጡን መሆን አለባቸዉ።
 ሁለተኛዉ የራስን ፖሊሲ ግልፅ ማድረግ ነዉ። ክልላችን በኦሮሚያ የሚኖሩ ብሔር-ብሔረሰቦችን ከኦሮሞ ለይቶ አይመለከትም። ይህን የሚያደረገዉ ከምንም በላይ ለኦሮሞ ህዝብ ዘላቂ ጥቅም በማሰብ ነዉ። በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ኦሮሞዎች በነፃነት ተከብረዉ ይኖሩ ዘንድ በኦሮሚያ የሚኖሩ ብሔሮች መከበር አለባቸዉ። ከላከበሩ መከበር እንደማይኖር ይታወቃል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ወንድሞቹን አቅፎ በፍቅር አብሮ መኖር የኦሮሞ ህዝብ መሠረታዊ ባህል ነዉ። ስለዝህ በክልላችን በሚኖር የትኛዉም ብሔር ላይ ጥቃት የሚፈፅም ግለሰብ ወይም ቡድን የኦሮሞ ህዝብ ቀንደኛ ጠላት ነዉ። ይህ የክልሉ እና ክልሉን የሚመራዉ ድርጅት ግልፅ አቋም ነዉ።
ግን ነገሮች መልክ መያዝ አለባቸዉ። የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። አማራ ክልል የሚኖር ኦሮሞ የክልሉን ህግና ደንብ ማክበር አለበት። ህግ ከጣሰ ተጠያቂ ነዉ። ጥፋቱን በብሔር ካባ መሸፈን የለበትም። ለሱ ብቻ የሚወጣ ልዪ ህግ የለም። የአማራ ክልል ግዴታ ባለዉ ህግ ሁሉንም እኩል ማስተናገድ ብቻ ነዉ። በአዳማ ወይም በአምቦ የሚኖር አማራም እንደዚሁ ነዉ። የኦሮሚያን ህግ እና ደንብ አክብሮ መኖር አለበት። ካላከበረ ይጠየቃል። በዝህ ላይ ድርድር የለም። የእኩልነት እንጂ የተለየ መብት አንሰጥም። ለእኛም እንድሰጠን አንፈልግም። ግልፅ መነጋገር ያስፈልጋል።
ፍቅር እና እዉነት ያሸንፋል!
የክፉዎች ሴራ ይከሽፋል!
Filed in: Amharic