>

"በግፍ የታሰሩ ወንድሞቻችን መፈታት የጥያቄያችን አካል እንጂ የመጨርሻ ግባችን አይደለም!!!" (ኡስታዝ አቡበከር አህመድ)

ለአመታት በግፍ እስር ስትሰቃዩ የነበራችሁ ወንድሞቻችን  በኢድ ቀናችን ከእስር ተፈታችሁ ከናፈቃችሁ ቤተሰባችሁ እና ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ጋር በመቀላቀላችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ማለትን እወዳለሁ
በእስር በነበራችሁበት ወቅት ያሳለፋችሁትን መራራ እና ከባድ ስቃይ በሂደቱ ያለፍን ወንድሞች በደንብ እንረዳዋለን፡፡ የከፈላችሁትን መስዋትነት  አላህ ይቀበላችሁ
 የኢትዬጲያ ሙስሊም ማህበረሰብ የእምነት ነፃነቱ እንዲከበር ላለፉት አመታት ያደረገው ሰላማዊ ትግል ዛሬ ላይ ሃገራችን እየተመለከተችው ላለው የለውጥ ንፋስ ቀዳሚው አስተዋፅኦ ያበረከተ ነው፡፡
በዚህ ሂደት ውስጥ ብዙዎች ለእስር ተዳርገዋል፣አካላቸውን እና ህይወታቸውን አጥተዋል፣ለአስከፊ የስደት አለም ተዳርገዋል፡፡ የሙስሊሙ የመብት ጥያቄ በሂደቱ በግፍ የታሰሩትን በማስፈታት ላይ የተገደበ ሳይሆን በሃገሪቱ ባጠቃላይ እንደ ዜጋ ልናገኛቸው የሚገቡ መብቶቻችን እስኪከበሩ የሚቀጥል ነው፡፡
መንግስት ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚል እስረኞችን ለመፍታት ከወሰነበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በግፍ እስር ላይ የነበሩ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ሲፈታ የቆየ ሲሆን በሙስሊሙ ሰላማዊ የመብት ትግል ጋር በተያያዘ ለግፍ እስር የተዳረጉ ወንድሞችን በመፍታቱ ረገድ ውስንነት በመመልከታችን ብሄራዊ መግባባቱ ሙስሊሙን የማያካትት ነው ወይ የሚል ጥያቄ አጭሮብን ነበር፡፡
በዛሬው እለት በአህመድ እድሪስ የክስ መዝገብ ተከሰተው የነበሩት የደሴ ወጣቶች እና በአማን አሰፋ መዝገብ የግፍ ብይን ተላልፎባቸው የነበሩ  ቀሪ ወንድሞች  በቀጣይ ቀናት ከእስር እንዲፈቱ መደረጉ  ውሳኔው የዘገየ ቢሆንም የሚበረታታ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡
አሁንም ቢሆን በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ብቻ ሳይሆን በክልል እስር ቤቶችም የእምነት ነፃነት በመጠየቃቸው በግፍ እስር ላይ የሚገኙ በርካታ ወንድሞቻችን እንዲሁም ለሃገራችን ፍትህ እና ነፃነት በመታገላችው በግፍ እስር ላይ የሚገኙ የህሊና እስረኞች በሙሉ መንግስት ሊፈታቸው እንደሚገባ ማሳብሰብ እንወዳለን፡፡
የእምነት ነፃነት በመጠየቃቸው ለእስር የተዳረጉ ወንድሞቻችን ከእስር ተፈቱ ማለት ሙስሊሙ ማህበረሰብ ያነሳቸው በርካታ የፍትህ የነፃነት እና የእኩልነት ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል ማለት አይደለም፡፡
መንግስት የነበሩበትን ድክመቶች አምኖ ተቀብሎ በአዲስ አስተሳሰብ ለለውጥ እንሰራለን እያለ ባለበት በዚህ ወቅት የሙስሊሙ ማህበረሰብንም የእምነት ነፃነት ጥያቄዎች ምላሽ ሊሰጥባቸው ይገባል፡፡
ሙስሊሙ ካነሳቸው መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመጅሊሱ አመራሮች በህዝበ ሙስሊሙ በሚመረጡ ህዝብን በቀናነት የሚያገለግሉ አመራሮች እንዲተኩ የሚጠይቅ ነው፡፡ አሁን ላይ ያሉት የኢትዬጲያ እስልምና ጉዳዬች ጠቅላይ ምክር ቤት አመራሮች የሰፊውን ህዝበ ሙስሊም ውክልና የሌላቸው ከመሆኑም ባሻገር የሙስሊሙን አንጡራ ሃብት ለሃጅ ጉዞ ከፍተኛ ገንዘብ በመጠየቅ ሙስሊሙን እየበዘበዙ ይገኛል፡፡ ይህ በግልፅ እየተፈፀመ የሚገኝን ዘረፋ እና ብልሹ አሰራር እንዲቆም መንግስት የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ ምላሽ በመስጠት ችግሩን ሊቀርፍ ይገባል፡፡
ሙስሊሙ ያነሳቸው ጥያቄዎች በአዲሱ አመራር ምላሽ እንዲሰጥባቸው ሙስሊሙ ከዚህ ቀደም ለአመታት ሲያደርገው የቆየውን ሰላማዊ ትግል አሁንም አጠናክሮ ከመቀጠል ውጪ አማራጭ እንደሌለው መረዳት ይገባል፡፡
ሃገራችን ወደነበረችበት ሰላም እና እድገት ለመመለስ የሃገሪቷ ግማሽ የሆነውን ሙስሊም ማህበረሰብ ችላ በማለት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት ፈፅሞ እንደማይቻል ለአዲሱ አመራር ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡
በያያዘ:-
Filed in: Amharic