ይህ ወቅት ወሳኝ ነው። ለህወሀትና ለኢትዮጵያ ህዝብ የሞት ሽረት ጊዜ ነው። ከሁለት አንዱ አሸናፊ መሆናቸው አይቀርም። ህወህት ከተሳካለት የምንወዳት ሀገራችን በዩጎዝላቪያ የተያዘውን ሪከርድ በመስበር ወደትንንሽ ሀገራት ተሰነጣጥቃ፡ በደምና ዕልቂት የታጀበ አስከፊ ታሪክ አስመዝግባ፡ የማይበርድ ዘላለማዊ ቀውስ ለቀጠናው አሳቅፋ፡ እሷም ተበታትና ልጆቿም ተላልቀው የሚቋጭበት አደገኛ ውጤት ይሆናል። የኢትዮጵያ ህዝብ ካሸነፈ ግን የዘመናት ተውሳክ ተወግዶ፡ ጥላቻ በፍቅር ተሸንፎ፡ የተባበረችና አንድነቷ የጸናች ሀገር ምስራቅ አፍሪካ ላይ ከፍ ብላ የምትታይበት ይሆናል። ፍልሚያው በሁለት ጎራዎች መሀል ነው። በህወሀትና በኢትዮጵያ ህዝብ። እንግዲህ ግብግቡ ተጀምሯል።
”እኛን አባልተው ሊበሉን ያሰቡ የቀን ጅቦች አሉ ። እድል አንስጣቸው ፤ ተባብረን እንታገላቸው”። የሚል መሪ ቤተመንግስት ገብቷል። እስከአሁን ያልተዋጠልን ልንኖር እንችላለን። መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አይችሉም በሚል አቋም ላይ ሆነን አካሄዳቸውን በጥርጣሬ የምንመለከት እንዳለን ይሰማኛል። ከጨቋኝ ስርዓት የወጣ መሪ እንዴት አዳኝ ይሆናል በሚል እድል ለመስጠት ያልፈለግን ጥቂቶች እንዳልሆንን እሙን ነው። የእሳቸው ነገር ጣዕም ያልሰጠን፡ ልባችን አልከፈት ያለብን፡ ከዚህ ሁሉ በኋላም፡ የጥርጣሬውን መንገድ መከተል የመረጥን እንዳለን ይታወቃል። ግን አሁን ላይ ምን ምርጫ አለን?
ኢትዮጵያ አደጋ ላይ ናት። ምናልባትም ወደ ዘመነ መሳፍንት ሊወስዳት ከሚችል አስከፊ የታሪክ አጋጣሚ ጋር ልትላተም ትችል ይሆናል። እንደሀገር የመቀጠሏ ነገር አደጋ ውስጥ ገብቷል። ከሀዋሳ የሚፈሰው ደም የሚነግረን ብዙ ነው። በጉጂ መሬት እየወደቀ ያለው ወገን የነገን አስከፊ ወቅት የሚያሳየን ነው። ጂማ ላይ ዳር ዳር የሚለው ግጭት በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በአጭሩ ወሳኝ የታሪክ ጊዜ ላይ ቆመናል። ወይ እንጠፋለን። አልያም ከእሳቱ አምልጠን አንዲት ኢትዮጵያን ይዘን እንወጣለን። እዚህ ዘመን ላይ ሆነን ምርጫችን ምንድን ነው? ተስፋችንስ?
የቀን ጅቦች ተሰልፈዋል። የደም ግብር እየጠበቁ ነው። እስከአሁን የፈሰሰው አላረካቸውም። አሁንም ካራ ስለው እየጠበቁን ነው። በሀዋሳ ሊገባ ሲል የተያዘው የጦር መሳሪያ በጅቦቹ በሚስጢር የተላከ የጥፋት ገጸበረከት ነበር። ወልቂጤ ላይም በተመሳሳይ ጅቦቹ በድብቅ ሊያስገቡት የነበረው ጠመንጃና ጥይት በሀገር ወዳድ ሰዎች ጥረት ተይዟል። በሌሎች አከባቢዎች ምን እየተደረገ እንዳለ አናውቅም። ህወሀቶች አርፈው የሚቀመጡ እንዳልሆኑ ግን እናውቃለን:: በየአከባቢው ለኢትዮጵያውያን መተላለቅ የተዘጋጀ የዕልቂት ድግስ እንደሚኖር አይጠፋንም። ከወዲሁ ምልክቶችን በሚገባ እያየን ነው። ጅቦቹ ተነስተዋል። ህወሀቶች የቀመሱት ደም አስክሯቸዋል። በሰፊው ተመኝተዋል። ቋምጠዋል። ተያይዞ ለመጥፋት ከምንጊዜውም በላይ ተዘጋጅተዋል። እኛስ?
ከቤተመንግስት የገቡት መሪ ጥሪ አቅርበዋል። ” ለጅቦቹ እድል አንስጣቸው” እያሉ ነው። ምን ምርጫ አለን? እውነት ለመናገር አሁን ላይ በፍቅር እናሸንፍ የሚል ጥሪ ከቤተመንግስት የሚያሰማ ሰውን ከመደገፍ ውጭ ለጊዜው ምን ምርጫ አለን? ለዚህ ጥሪ ጆሮን መንፈግ ያዋጣልን? አመጣጣቸው ቢያጠራጥረን፡ አካሄዳቸው ባይጥመን፡ ሀገር ለማዳን ላደረጉት ጥሪ ግን እንዴት አንተባበራቸውም? ሌላው ይደርሳል። አሁን ትንፋሽ የሚያሳጣ፡ ልብ የሚያቆም፡ አደጋ ውስጥ ነን። እዚህ አደጋ ላይ ሆነን ”ኢትዮጵያን እናድን” የሚል መሪ ተነስቶ ድጋፍን መንፈግ ከቶ እንዴት ይቻላል?
የምርጫ ጉዳይ አይደለም። የህልውና ነው። ዶ/ር አብይን በዚህን ወቅት መደገፍ ኢትዮጵያን ማዳን ነው። ለጊዜው ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ ቅንጦት ነው።