>

የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን የለውጥ እርምጃዎች ለመደገፍ የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች የተሰጠ መግለጫ

ቅዳሜ፣ ሰኔ 16/2010 በአዲስ አበባ አብዮት አደባባይ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን የለውጥ እርምጃዎች ለመደገፍ የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች የተሰጠ መግለጫ!

ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት 27 አመታት በጥቂቶች የጭቆና አገዛዝ ስር ወድቃ ዜጎቿ ለሞት፣ ለእስር፣ ለአካል ጉዳት፣ ለቶርቸር፣ ለስደት፣ የሀገራችን ሀብት እና ማዕድናት ተዘርፎ ለጥቂቶች የተንደላቀቀ ኑሮ እና ምቾት እየዋለ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ። በአጠቃላይ የሀገራችን ህዝቦች በገዛ ሀገራቸዉ ተንቀዉ እና ተዋርደዉ ለመከራ ኑሮ የተዳረጉበት፣ የሀገራችን ወጣቶች በሀገራቸዉ ተስፋ አጥተዉ ለስደት የተዳረጉበትና በየበረሃዉ በዉሃ ጥም እና በረሀብ እየረገፉ፣ በባህር የዓሳ እራት እየሆኑ እንደሆነ ይታወቃል።

የሀገራችን ህዝቦች በተለይም ወጣቱ አንድም ቀን ለዚህ ለዉርደት ለዳረጋቸዉ የጥቂቶች የጭቆና አገዛዝ ተንበርክከዉ አያዉቁም። በኦሮሚያ የቄሮ፣ በአማራ የፋኖ፣በጉራጌ ዘርማ በሌሎች የሀገራችን አከባቢዎችም ወጣቶች በተደራጀ እና በተበታተነ መልኩ ገዢዎችን እየተፋለሙ ዉድ ህይወታችዉን እና አካላቸዉን ገብረዋል። ትኩስ የወጣትነት ዕድሜያችዉንም በማዕከላዊ፣ በቃሊቲ፣ በቂሊንጦ፣ በከርቸሌ እና ሌሎች ማጎሪያ ካምፖች ዉስጥ ለማሳለፍ ተገደዋል።

በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ወጣቶች መስዋዕትነት እና የደም ፅዋ ሞልቶ መፍሰስ ጀምራል። በሀገራችን ወጣቶች ትግል የህዝብ ልጆች የሆኑ፣ ህዝብ ህዝብ የሚሸቱ፣ የህዝቡ ስቃይ የሚያማቸዉ አመራሮች ወደ ፊት በመዉጣት ትላልቅ እርምጃዎችን መዉሰድ ጅምረዋል። በዶ/ር አቢይ አህመድ የሚመራዉ አዲሱ መንግስት በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን ነፃ አዉጥቷል። በተለያዩ ሀገራት ተሰድዉ በእስር የሚሰቃዩ ኢትዮጵያዉያንን አስፈትተትዋል። ሲደረጉ የነብሩ ዝርፊያዎችን በማስቆም ላይ ይገኛል። አይነኬ የማይመስሉ የገዢዉ መደብ ደም መጣጭ ፈርኦኖች ከስልጣን በማሰናበት ተስፋ የሚሰጥ የለዉጥ እንቅስቃሴ ጀምራል። በዚህ ሂደትም ሀገራችን ከተስፋ ማጣት ጨለማ ወደ ተስፋ ጭላንጭል ብርሃን ማማተር ጀምራለች።

ይህ የለዉጥ ሂደት ከጥቅም እና ከስልጣን ከበላይነት ያንሸራተታችዉ የገዢ መደቦች ሌቦች በሀገራች እየታየ ያለዉን የለዉጥ እንቅስቃሴ በመቀልበስ የበላይነታችዉን በድጋሜ ለማግኝት አሻጥሮችን የተንኮል ሴራዎችን በጎንጎን ላይ ይገኛሉ። በዚህም ብሄሮችን ማጋጨት እና ከቀያቸዉ በማፈናቀል፥ ኦኮኖሚዉ ዉስጥ ያላችዉን የበላይነት በመጠቀም ሰዉ ሰራሽ ዕጥረትና ችግር በመልፍጠር ዜጎች በኑሮ ዉድነት እንዲጠበሱ በማድረግ ላይ ይገኛሉ። በተለያዩ አካባቢዎችም የህግ የበላይነት እንዳይሰፍን በማድረግ፥ የማስፈራሪያ የድርጅት መግለጫዎችን በማዉጣት እና የተቃዉሞ ሰልፎችን በመጥራት የዶ/ር አቢይ አህመድ መንግስትን በሃይል ለመጣል በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ።

ስለሆነም የእነዚህን ደም መጣጭ ገዢ መደቦችን አሻጥር በመቃወም እና ለዶ/ር አቢይ አህመድ መንግስት ያለንን ድጋፍ እና አጋርነት ለመግለፅ ቅዳሜ ሰኔ 16/2010 ከጠዋቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ታላቅ ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፍ ተጠርቷል። ስለሆነም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በድጋፍ ሰልፉ ላይ በመገኘት ለዶ/ር አቢይ አህመድ መንግስት ያለዉን ድጋፍ እና አጋርነት እንዲገልፅ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

በመስዋዕትነታችን ያገኘነዉን የለዉጥ ተስፋ በሌቦች አይጨልምም!!
የህዝቦች አንድነት በፍቅር እንጂ በመፈራራት አይገነባም!!
ሌቦች ተመልሰዉ ወደ ስልጣን መምጣት በመቃብራችን ላይ ብቻ ይሆናል!!
ከዶ/ር አቢይ አህመድ የለዉጥ አመራር ጋር ወደፊት!!
የሌቦችን የተንኮል ሴራ እና አሻጥር እናጋልጣለን፥ ለመብታችንም እንፋለማለን!!
በሀገራችን እየታየ ያለዉ የለዉጥ ተስፋ በማንም ሊቀለበስ አይችልም!!
ህገ ወጥነት እና ግጭት ማስፋፋት የሌቦች ሴራ መሆኑን ነቅተናል!!
ሰላማችንን በመጠበቅ እና በፍቅራችንን በማጠናከር በአንድነት ወደ ፊት እንራመዳለን!!

Filed in: Amharic