>
5:16 pm - Friday May 24, 9748

ዴርቶጋዳ ደራሲ፤ ይስማዕከ ወርቁ፤ [ቅኝት፤ መስፍን ማሞ ተሰማ - ሲድኒ አውስትራሊያ]

ዴርቶጋዳ

ደራሲ፤ ይስማዕከ ወርቁ

 ቅኝት፤ መስፍን ማሞ ተሰማ

ማስታወሻ

አንባቢ ሆይ! ዴርቶጋዳን ጨምሮ አስራ ሶስት መፃህፍትን ያበረከተው ተዓምረኛውና ምጡቁ ወጣት ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ በደረሰበት አስከፊ አደጋ መናገር አይችልም። የሁለት ህፃናት አባት የሆነው የሥነ ፅሁፍ ጠቢብ ገና የሰላሳ አንድ ዓመት ወጣት ነው። ይስማዕከ ደራሲ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ቅርስ ነው። ይህ ቅርስ ስለ ኢትዮጵያና ቅርሷ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ሁሉ በጊዜ ሊደርስለትና በቅርስነቱ ሊታደገው በረከቶቹ ግድ ይሉናል። ይስማዕከን ኢትዮጵያም ልታክመውና ልታድነው የእናትነት ግዴታም አለባት። ይስማዕከን ማዳን የዚህን ወጣት ትውልድ ራዕይም ማዳን ነው!! እነሆ ወጣቱ ብላቴና የሥነ ጥበብ ፈርጥ የሚገኝበትን ዕውነታ ከቅኝቱ መጨረሻ የሚገኙትን ቪዲዮዎች ጊዜ ወስደው ይመለከቷቸውና የበኩልዎን ይወስኑም ዘንድ በታላቅ ትህትና እጠይቃለሁ።

ይስማዕከ  ሆይ በርታ፤ ዕምነት ተስፋና ፍቅር ያድኑሃል!!

   _______________________________________

{ይህ ቅኝት በሰኔ 2002 ዓ/ም (ጁን 2010) ተፃፈ}

መነሻ፤

                                                                                                                                ዴርቶጋዳን  በማንበቤ ሠላም አጥቼ ሰነበትኩ። ነፍሴም በከፍተኛ ማዕበል ስትናወጥ ከረመች። ውስጠቴን የዘለቀ ጥልቅ ሀዘን ደግሞም ደስታ ደግሞም ብሩህ ራዕይ ተፈራረቁብኝ።  ማዕበሉ ፀጥ ሲል ነፍሴም መልህቋን ስትጥልለብዙ ማዕልትና ሌሊት በጥሞና  አሰላሰልኩ። ከነፍሴ ጋር ተማከርኩ። እርግጥ ነው የዴርቶጋዳ ምሥጢረ  ምሥጢራት ሁሉ  ገና  አልተገለጡልኝም ይሆናል። ነፍሴ ግን መተንፈስ  ፈለገች፤ ከጭንቀቷ መገላገል፤ ስለዴርቶጋዳ  መናገር። እና ብዕሬን አነሳሁ። እነሆ ዴርቶጋዳን ከአንባቢያን ጋር መጋራት ፈለግሁ። ስለምን ደካማዋ ነፍሴ ታፍና ትሙት?! እንግዲህ  አንባቢም ይህንን ፅሁፍ አስጀምሮ ያስጨርሰው ዘንድ ትዕግስቱ ይሁን! እነሆ ዴርቶጋዳ

እኛም አለንዳን ብራውን!

ዳን ብራውንን ስሙን ያልሰማ ወይም ከመፃህፍቱ ያልተቋደሰ ይኖር ይሆን? ብራውንየዳቪንቺ ኮድደራሲ ነው። ይህ ቅኝት በተፃፈበት ሰሞን ካሳተመው ሎስት ሲምበልጋር አምስት መፃህፍትን አቅርቦልናል። ብራውን የደራሲ ሮበርት ሉድለም ደቀ መዝሙር ነው። ሉድለም በአርባ አመቱ ወደ ድርሰት ዓለም ከገባ በሁዋላ በህይወት በኖረባቸው ዘመኑ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ውስብስብ፤ እጅግ ፈጣን የድርጊት ታሪክና የደም ዝውውወርን የማቆም ሃይል ያላቸው የሚመስሉ ልብ አንጠልጣይ የስለላና የሴራ መፃህፍትን አበርክቶልናል።

ደቀመዝሙሩን ከመምህሩ (ብራውንን ከሉድለም) የሚለየው ጉልህ የድርሰት ባህሪ አለው። አንባቢ የብራውንን መፃህፍት አንብቦ ሲጨርስ ነፍሱ እፎይታን አታገኝም። ሠላም አይኖራትም፤ ዕውቀት ትጠማለችና። ይህ የብራውን ልዩ የድርሰት ችሎታው ነው። ይህ የዳን ብራውን የድርሰት አደራረስ ልቤን ምርኮኛው አድርጎት ኖሯል።

ለምሳሌ በብራውን መፃህፍት ሳቢያ –  በቫቲካን ቁልፍልፍ ኮሪደሮችና በከርሰ ምድሩም የምሥጢር ጓዳ ጉድጓዶች፤ በፓሪስ ጥልፍልፍ መንገዶችና ሙዚየሞች፤ በስፔን ካቴድራሎችና በስዊስ የባንክ ጎተራዎች፤ በኒውዮርክ ጉራንጉሮችና በዋሽንግተን ድብቅ ዋሻዎች….የሊዮናርዶ ዳቪንቺን ሥዕላዊ ምሥጢራት፤ የኒውተንን ድብቅ ቀመር፤ የገጣሚያንን ስውር ቅኔ፤ የመንግሥታት መሪዎችን ስውር ተልዕኮየባህታውያንን፤ የቴምፕለሮችን፤ የማሶናውያንን ምሥጢራዊ ድርጅቶችና ዓላማዎችቻቸውንብራውንን ተከትዬ ሳሳድድና አብሬያቸው ስሳደድ ኖሬያለሁ።ከእንግዲህስ ነፃነቴን አውጃለሁ አቶ ዳን ብራውን!

ፀሐይ በጠዋት ማልዳ አዲስ ቀን መውጣቱን ለአዳም ዘር ለማብሰር አድማስን ታካ ከወደ ምሥራቅ አምራና ደምቃ ፍንትው እንደምትል፤ እንዲሁ ደግሞ ከወደ ምሥራቅ አፍሪቃ ከምድረ ኢትዮጵያ  በዓለም የሥነ ፅሁፍ ማማ ላይ የወጣ ዴርቶጋዳ ርችቱን ተኩሷል። ተኳሹም ብላቴና ይስማዕከ ወርቁ ይባላል።

ዴርቶጋዳበሴራው ውቅረት የረቀቀ፤ በቋንቋው ውበት የመጠቀ፤ በገፀ ባህሪያቱ የገዘፈ፤ በምናብ ህዋን የዳሰሰ፤ ተስፋና ራዕይ ያነገበ፤ ትላንት ዛሬንና ነገን ያቆራኘ፤ የዚህ ወጣት ትውልድ ታላቅ የሥነ ፅሁፍና የፈጠራ ስራ ውጤት ነው፤ የብላቴናው ይስማዕከ ወርቁ በረከት።

እነሆ በፓሪስ ኤፍል ታወር ላይ ቆሜ፤ በኒው ዮርክ ስታቹ ኦፍ ሊበርቲ ሠገነት ላይ ወጥቼ፤ በሲድኒ ሀርበር ብሪጅ ላይ ተንጎራድጄ፤ አዲስአባ በምኒልክ አደባባይ ነጋሪት ጎስሜዴርቶጋዳን  ለዓለም አውጃለሁእኛም አለን ዳን ብራውን!!

ማሔር ሻላል ሐሽ ባዝ

በታላቁ መፅሐፍ ላይ ኢትዮጵያ ስሟ ተደጋግሞ ተነስቷል። ከሁሉም በላይ ግን ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ አያሌ የዓለም ማህበረሰብንም አመራማሪውኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ዘርግታለች የሚለው ነው።

ይህ ከተፃፈ ምዕተ ዓመታት ተቆጥረዋል። ዛሬም ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪዋ እንደዘረጋች ናት። ፀሎቷንና ልመናዋን አላቋረጠችም።አንኳኩ ይከፈትላችዃል፤ እሹ ታገኙማላችሁይላል የጌታ ቃል። ኢትዮጵያ እስከዛሬ ባላቋረጠችው ፀሎቷ የምትሻውን አላገኘችም። በሩም አልተከፈተላትም።

ለመሆኑ ስለምን ይሆን ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪዋ ዘርግታ የምትፀልየው? ፀሎቷስ ስለነማን ነው? ፈጣሪዋስ የሚሰማት መቼ ይሆን?…እንጠይቃለን እኛ።

እነሆ አንድዬ ፀሎቷን መስማቱንና የዛሉት ክንዶቿም ይጠነክሩ፤ የጠወለገው ገላዋም ይፋፋ፤ ግርማ ሞገሷም ይመለስ ዘንድ፤ ራዕይ አስይዞ መልዕክተኛውን ልኮላታልዴርቶጋዳን።

እንደ መልዕክተኛው ጳውሎስም፤ ራዕይ የታየው ብላቴናው መልዕክተኛ ይስማዕከ ሲፅፍም፤ ከላይኛው ደራሲ ዘንድ የተላከ ታላቅ መልዐክ በሬን በርግዶ ገብቶ ከእንቅልፌ አባነነኝ።ከወርቃማ ክንፉ ላይ አንድ ላባ ነቅሎ ብዕር ቀርፆ ሰጠኝ። በታላቅ ሰሌዳ ላይምማሔር ሻላል ሐሽ ባዝብለህ ፃፍ አለኝ።…” ይላል።  ምን ማለት ይሆን? ይህ የስላሴ ቋንቋ ነውን? ራዕይ የታያቸው ብቻ የሚገለጥላቸው?

በላይኛው መልዐክ ቋንቋ ማሔር ሻላል ሐሽ ባዝ ማለትም ምርኮ ፈጠነ ብዝበዛ ቸኮለ ማለት ነው ይለናልምሥጢሩን የፈታልን ይስማዕከ።

ተማራኪው ማን ነው? ተበዝባዡስ? ብዝበዛውስ መፍጠኑ ስለምንድን ነው? – እንላለን እኛ ደግሞ፤ ምሥጢራዊው ቋንቋ ይበልጥ በአእምሯችን እየተወሳሰበ።

ኦርያ ኢትዮጵያማሔር ሻላል ሐሽ ባዝ ይላል ደራሲው ደግሞበውድቅት ሌሊት የተነገረውን መልዕክት ሲያስተላልፍልን። ምን ማለት ነው? እንጠይቃለን እኛ ደግሞ።ኦርያ!…ማሔል ሻላል ሐሽ ባዝማለትም የኢትዮጵያ ተባዮች ከላይዋ ላይ ተነሱምርኮ ፈጥኗልብዝበዛ ቸኩሏልማለት መሆኑን ተርጉሞልናል ደራሲው።

ያንተ ያለህ! እንላለን እኛ፤ መልዕክቱ እንደ ድንገተኛ ነጎድጓዳዊ መብረቅ በህሊኛችን ውስጠ ውስጥ ብርሃኑ ሲያስገመግም እየታየን።ዓይን አላቸው አያዩም፤ ጆሮ አላቸው አይሰሙምየሚለው የመለኮት ቃል ከነጎድጓዳዊው ብርሃን ጋር በአእምሯችን እያስተጋባ።

ዕውነት ነው እንላለን፤ የጋረደን ጉም እየተገለጠልን፤ ዕውነታው እየታየን። ኢትዮጵያ በተባዮች ተወራለች። ኢትዮጵያ ተማርካለች። እጆቿንም ወደ ፈጣሪ እንደዘረጋች ያለችው ዛሬም መማረኳን ስታሳየው ነው፤ አቅም ማጣቷን፤ ከምርኮዋ ነፃ የሚያወጣት አለማግኘቷን።

ኦርያ ኢትዮጵያ!”

ዕርግጥ ነው አይተናል። ዕውነት ነው ሰምተናል። ብዝበዛው ፈጥኗል። የኢትዮጵያን ሆድዕቃ ቦትርፈው አንጀቷን የሚዘለዝሉ ጅቦች በዝተዋል። እነሆ እንደ መስቀል ቅርጫም እየተቀራመቷት ናቸውና። ለዘመናት አይተን እንዳላየሰምተንም እንዳልሰማ ኖረናል። ሀጢያታችን በዝቷል። ወንጀላችንም በርክቷል። እንደ ጲላጦስ እጆቻችንን ታጥበንበኢትዮጵያ ምርኮ የለንበትም፤ ብዝበዛውንም አናውቅምለማለት አንችልም። የፍርድ ቀን ቀርቧልና!

ማሔር ሻላል ሐሽ ባዝእግዚአብሄርም ታላቅ ሰሌዳ ወስደህ  ምርኮ ፈጠነ ብዝበዛ ቸኮለ ብለህ በሰው ፊደል ፃፍበት። የታመኑትን ሰዎች ካህኑን ኦርዮንና የበራኪዩን ልጅ ዘካርያስን ምስክሮች አድርግልኝ አለኝይላል የኢሳያስ መፅሀፍ። ይህ እንግዲህ የናሳው ሳይንቲስት ኢንጂነር ሻጊዝ እጅጉ በዴርቶጋዳ ላይ ለትንሳኤ ኢትዮጵያ ያዘጋጀው / ሚራዥ በቀይ ድንጋይ ላይ ተቀርፆ  የደረሰው መልዕክት መፅሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም ነው።

አዎንአለ ሚራዥ ቀዩን ድንጋይ እንደያዘ፤ ምርኮ ፈጥኗል ብዝበዛም ቸኩሏል። ሀገሪቱ በቅጥረኞችና በአድርባዮች እየተበዘበዘች ነው። ህዝቦቿ የበይ ተመልካች ሆነዋል። ተስፋ በቆረጠ ትውልድ ተሞልታለች። ወጣቶቿ እንጀራ ፍለጋ በባዕዳን ሀገር ሲሰደዱ በጋንጃቸው እየታረዱ ነው። ሴት ልጆቿ የአረብ ገረዶች እየሆኑ ነው። ማምለጫ ያጡትም በጥቁር አልማዛቸው ላይ ተኝተው እየለመኑ ነው። አዎ ጥቂቶች እየበዘበዙ ነው። ኢትዮጵያን የተሰበረ መንፈስ ወጥሯታል። ምርኮ ፈጥኗል ብዝበዛም ቸኩሏል።

ያንተ ያለህ! እንላለን እኛ ይህንን ስናነብ  ከሚያስጨንቅ ህልም ውስጥ ድንገት እንደ ባነንን ሁሉ። ምርኮው መፍጠኑ ብዝበዛውም መቻኮሉ ስለምን ይሆን? እንላለን በአንክሮ። ምን ይሻላል? ምን ይበጃል? አርባ ማዕልት አርባ ሌሊት ብንፆም ብንፀልይና ብንሰግድ ፈጣሪያችን ይታረቀን ይሆን? – እንጠይቃለን እኛ።

የለም! ይለናል ዴርቶጋዳ። ፆም ፀሎት ለነፍሳችሁ ነው፤ ለሥጋችሁ። እና ምን ይሻለናል? እንጠይቃለን ደግመን።

አንድ ነገር ያስፈልጋል። ለለውጥ ራስን መስጠት። አሁንምኢትዮጵያ አንድ አብዮት ያስፈልጋታል። ልጆቿን የማይበላ አብዮት! ራሱን የማይውጥ አብዮት! ሳይንቲፊክ ሪቮሉሽን። በሳይንስና ቴክኒዮሎጂ የታገዘ አብዮት።ለውጥን የሚጠላ  ኢትዮጵያዊ የለም። ለውጡ ሆዳቸውን ከሚያጎልባቸው ጥቂቶች በቀር። ችግሩ ግን የለውጡ አካል መሆን የሚፈልግ የለም። በሌሎች ሞትና ደም ለመጠርቃትና ኑሯቸውን ለማደላደል የሚመኙ ብዙዎች ናቸው። – ከዓለማችን ዝነኛ ሳይንቲስቶች አንዱ ሻጊዝ እጁጉ ነው የሚመልስልንበዴርቶጋዳ።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ግራ በመጋባት እንጠይቃለን። ከሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ሰቆቃው ጴጥሮስ ምሥጢራዊ ሥነ ግጥም ውስጥ መልሱን ታገኙታላችሁይለናል ዴርቶጋዳ።

1961 / አባ ዲዲሞስ የተባሉ ሰው ለባለ ራዕዩ ወጣት ገጣሚ ፀጋዬ ገብረ መድህን በአቁማዳቸው ውስጥ ከያዙት ብራና አርባ ስምንት ቃላትን አውጥተው አንድ መቶ አምስት (105) ስንኞች ባሉትሰቆቃው ጴጥሮስሥነ ግጥሙ ውስጥ ወጣቱ ባለቅኔ እንዲዘራቸው ያደርጉታል። አርባ ስምንቱን የአባ ዲዲሞስ ምሥጢራዊ ቃላት ጨምሮሰቆቃው ጴጥሮስአራት መቶ ዘጠና ሰባት (497) ቃላት አሉት። እነሆ እኒህ አርባ ስምንት ቃላት ታላቅ ምሥጢር ያለውንና በቁጥሮች የተነቀሰውን ፊደል ቅርፅ የተሰራውን ዴርቶጋዳየተሰኘውን መስቀል እንቆቅልሽ የሚፈቱ ቁልፎች ናቸውይለናል ይስማዕከ ወርቁ። ታምር አያልቅም፤ በዴርቶጋዳ! ለመሆኑ አባ ዲዲሞስ ማን ናቸው? እንጠይቃለን እኛ።

አባ ዲዲሞስ የአባ ፊንሀስና የአባ ዠንበሩ ጓደኛ የነበሩየማፊያው የአባ ዲዎላ አባትበሳይንቲስት ሻጊዝ እና በዶ/ ሚራዥ ጀርባ ላይ የሚገኙትን የመስቀል ንቅሳቶች የሳሉአቡነ ጵጥሮስ ሀውልት ላይ ሽንታቸውን እያንፎለፎሉ አቡኑን ሲሳደቡከወጣቱ ባለቅኔ ፀጋዬ ጋር ግብግብ የገጠሙ ናቸው፤ አባ ዲዲሞስ ማለት።

ስለምንድን ነው አባ ዲዲሞስ አቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ላይ መሽናታቸው? የከረመ ብስጭት አለባቸውአባ ዲዲሞስ። አቡነ ጴጥሮስ አልሰማ ብሎኝ ነው የሞተውይላሉ አባ ዲዲሞስ።ክፉ ነገርን ማለፊያ ጥበብ አልነገርኩህም ነበር?…አንተ ድንጋይ!…ክፉ ቀንን በጥበብ ከማለፍ በላይ ጥበብ የለምይህንንም ነግሬህ ነበር። ይህቺ ደም መላስ የለመደች ሀገር የምትለወጥ መስሎሃል! …ስንት ጀግኖች ሞቱላትአልተለወጠችም። ጴጥሮስ አልነገርኩህምአንተ ብትኖር ኖሮ ይሄኔ  አቡነ ዲዲሞስ እባል ነበር። የዚህች አገር እጣ ፈንታ በእጃችን ይወድቅ ነበር። እንለውጣት ነበር። ግን ሞትክጵጵስና ሳትሾመኝ ሞትክይህን እያሉ ነበር አባ ዲዲሞስ  አቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ላይ ሽንታቸውን ያንፎለፎሉት1961 /ም።

ይህንን ስናነብ አእምሯችን ይወጠራል። አቡነ ጴጥሮስና አባ ዲዲሞስ ይተዋወቁ ነበርን? ምሥጢርም ነበራቸው ማለት ነው? ኢትዮጵያን የመለወጥ ምሥጢር? ለመሆኑ  አቡኑና አባው ኢትዮጵያን የመለወጥ ራዕያቸው ምን ነበር? ሃይማኖትና ፖለቲካ፤ ጉድ ነው! እንላለን በመሃይም አንደበታችን፤ እንቆቅልሹ ሲበዛብን።

ይኸው እኒህኛው ጳጳስ የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም አበምኔት እንኳ ያድርጉኝ ብላቸው ከለከሉኝ። አባ ዠንበሩን ሾሙት። አንተ ብትኖር ግን ወንበዴዎች  ጳጳስ  ሆነው  አይሾሙም ነበር። እኔና አንተ የምናውቀው የዚህች ሀገር ምሥጢር በወንበዴዎች እጅ አይገባም ነበር።ለምን ስልጣን ሳትሰጠኝ ሞትክ? ለዚህች ሀገር ታላቅ ስራ ልንሰራ ተስማምተን ከዳኸኝ አንተ ድንጋይ…”  ማርያም ድንግላዊት ሆይ! እባክሽ አማልጂን! እንላለን ስድስት ጊዜ አማትበን በአባ ዲዲሞስ ንግግር ተጨንቀን።

ጵጵስናውንም ወንበዴዎች ተሹመውበታል እንዴ? እግዚኦ!! ይህ ሁሉ ሲሆን  ኢትዮጵያውያን የት ነበርን?  ለመሆኑ አባ ዲዲሞስና  አቡነ ጴጥሮስ ይጋሩት የነበረው የዚህች ሀገር ምሥጢርስ ምንድን ነበር? እንጠይቃለን ራሳችንን ደጋግመን።

ታዲያ አባ ዲዲሞስ ሀውልቱ ላይ መሽናታቸውና አቡነ ጴጥሮስን መሳደባቸው ሆን ብለው ነበር፤ ወጣቱን ባለቅኔና ገጣሚ ፀጋዬ  ገብረመድህንን  አበሳጭተው ለማጥመድ።

ድንጋይ አይደለምይላቸዋል ወጣቱ ገጣሚ በደም ፍላት፤ አባ ዲዲሞስ ላይ አፍጥጦ። ድንጋይ ነው ይሉታል እሳቸውም መልስው እያፈጠጡበት። ይቃመሳሉ በቡጢዲዲሞስና ፀጋዬ።ያን ሌሊት ፀጋዬ ቤቱ ሲገባ  “ሰቆቃው ጴጥሮስ ይፅፋል። ያንኑ ሌሊት አባ ዲዲሞስም ፀጋዬ ቤት ዘው ብለው ይገባሉ። እናም ያንኑ ሌሊት አቁማዳቸውን ፈትተው ከብራናቸው ላይ አርባ ስምንት ቃላት ለወጣቱ  ገጣሚ ሰጥተውት  ሰቆቃው ጴጥሮስውስጥ አራምባና ቆቦ አድርጎ እንዲዘራቸው አዘዙት። የቃላቱን ምሥጢር ፀጋዬ አያውቅም። አውቆም  ከነበረ  አልነገረንም። ግንዝም እንበልብሎ ፅፏል፤አብረን ዝም እንበል ሌላ ቅኔ፤ ሌላ ቁልፍ፤ ሌላ ምሥጢር ይሆን? አናውቅም።ከእንግዲህእሳት ወይ አበባየሥነ ግጥም መድብል መሆኑ አከተመ፤ የምሥጢራት ጎተራ እንጂ! እድሜ ለዴርቶጋዳ፤ እድሜ ለብላቴናው ይስማዕከ!

እሳት ወይ አበባ የሚለው የፀጋዬ  የሥነ ግጥም መድብል ለህትመትብርሃንና ሰላምሲገባ አባ ዲዲሞስአክሳፎስየሚል ርዕስ ያለው የመፅሀፍ ረቂቅ ይዘው ገብተው ነበር – “ሰቆቃው ጴጥሮስበመድብሉ  ውስጥ መካተቱንና  አርባ ስምንቱም ምሥጢራዊ ቃላት በግጥሙ ውስጥ ተሰራጭተው መኖራቸውን ለማረጋገጥ። አባ ዲዲሞስአክሳፎስ አላሳተሙም። ለመሆኑአክሳፎስምን ማለት ይሆን? ማለታችን ግን አልቀረም። ማን ያውቃል? አንድ ቀንአክሳፎስታትሞ ምሥጢሩንም እናውቅ ይሆናል። እስከዛው ግን  ዴርቶጋዳምሥጢር እንመራመር

አባ ዠንበሩ ራዕይ ናቸው

 አባ ዠንበሩ፤ አባ ዲዲሞስ፤ አባ ፊንሐስ። ሶስት አባዎች፤ የዴርቶጋዳ ምሥጢር መዘውሮች። ሶስት አርበኞች። በፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዘመን የነፃነት ፋኖዎች። በምሥጢራት የተሞሉ አባዎች፤  አርበኞች።  ከነፃነት  በዃላስ?…

“…ዋሻውን መቆፈር ስንጀምር (አባ ዠንበሩ፤ አባ ዲዲሞስ፤ አባ ፊንሐስ) አላማችን ለራሳችን መደበቂያነት ለመጠቀም ነበር። በዃላ የሀገሪቱ ውድ ሀብቶችና የብራና መፃህፎች ከጥፋት መከላከያ ሆኖ አገለገለ። እኔም በዚህ ወቅት በገዳሙ ውስጥ በማነባቸው መፃህፍት እየተቀየርኩ መጣሁ። ራዕዬን ከግለሰብነት ወደ ሀገራዊነት ቀየርኩት…” አባ ዠንበሩ ናቸው ለዶ/ ሚራዥ የሚነግሩት።

አባ ዠንበሩ የዴርቶጋዳ ራዕይ ናቸው፤ እርሾ። የጣና ገዳማት ጥንተ ጥንታዊ መፃህፍት ናቸው አባ ዠንበሩን ዳግም የፈጠሯቸውራዕይ የሰጧቸው። እንቀጥል የአባ ዠንበሩን ትረካ፤

“…ይህንን ዋሻ ወደ ትልቅ ህቡዕ የምርምርና መንግሥታት ሲለዋወጡ የማይለዋወጥ ለሀገሪቱ ፅኑ መሰረት የሚሆን ምሥጢራዊ ድርጅት የማድረግ ራዕይ በውስጤ ተጠነሰሰኢትዮጵያን ለኢትዮጵያውያን ማድረግ የሚቻለው ትክክለኛው የቴክኒዮሎጂ ዕውቀትና ትክክለኛው የቴክኒዮሎጂ መሳሪያ በራሷ ልጆች እጅ ሲገባ መሆኑን ተረዳሁ።ይህንን ራዕይ የተጋራኝ ሰው አለቃ አያሌው ብቻ ነበር። አያሌውአባ ዲዲሞስ ይባል ነበር። አባ ዲዲሞስ ብዙ ለውጦች ለማምጣት ሥልጣን ይፈልግ ነበር።ከአቡነ ጴጥሮስ ጋር ቅርርቦሽ ነበረው።አቡነ ጴጥሮስ በባንዶች የጣሊያን አሽከሮች በጥይት ተደብድበው ሞቱ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ባህሪው ተለወጠብኝ።…”  ይላሉ አባ ዠንበሩ ለዶ/ ሚራዥ ሲያስረዱ። አባ ፊንሐስስ?… “…አባ ፊንሐስ ስለ ሀገር ማሰብ አይፈልግም። ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ያንገሸግሸው ነበርይላሉ አባ ዠንበሩ። አስገራሚ ታሪክሶስት አባዎችሶስት መንገዶች።

አባ ዲዲሞስ፤ አርበኛ፤ ፈላስፋ፤ ንቅሳት (ንድፍ) ነዳፊ፤ ለውጥ አላሚ፤ ሥልጣን ፈላጊ።

አባ ፊንሐስ፤ ከራስ በላይ ንፋስ ያሉ፤ የኢትዮጵያን እንባ መጥረግ እማይፈልጉ፤ ከዋሻው ውስጥ ከሚገኙት ቅርሶች የንጉሥ  ዘውድ ሰርቀው የሸጡ፤ ወንጀለኛ አባ።

አባ ዠንበሩስ? አባ ዠንበሩማ ራዕይ ናቸው ብለናል፤ የኢትዮጵያ ራዕይ

እንቀጥል

“…በዚህ ዋሻ ውስጥ ብዙ ለውጦች ታይተዋልይህም የሆነው እንደ ኢንጂነር ሻጊዝ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች በገንዘብም በእውቀትም አብረውን መስራት ከጀመሩ በሁዋላ ነው።…” ይላሉ አበ ዠንበሩ ለዶ/ ሚራዥ ሲያብራሩ። አባ ዠንበሩ ምንድን ነው እሚነግሩን? ኢንጂነር ሻጊዝ እጅጉ፤ የናሳው ምርጥ ሳይንቲስት ከአባ ዠንበሩ ጋር? እንጠይቃለን በታላቅ መደመም፤ የዴርቶጋዳ  ተአምር  መቼም  በዋዛ  አያልቅም።

ከእኔ የሚጠበቀው ምንድን ነው?” / ሚራዥ ነበር አባ ዠንበሩን የጠየቃቸው።

ሁለት ነገር ይጠበቅብሃል። አንዱ ቀሪ ህይወትህን በዚህ ድርጅት ውስጥ በማገልገል ሀገርህን ከጥፋት ማዳን ነው። በዚህ ሰዓት ዓለም ዐቀፍ ማፍያዎች ከማይጠረቁት የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር በመሻረክ  ሀገርህን  እየበዘበዙዋት  ነው።

ማሔር ሻላል ሐሽ ባዝምርኮ ፈጠነ ብዝበዛ ቸኮለ። ኢትዮጵያ ተስፋ በቆረጡ ወጣቶችና ህዝቦች ተሞልታለች። የብዙ ኢትዮጵያውያን መንፈስ ተሰብሯል። የድህነቱ ምንጭ ምን እንደሆነ  ሁላችን  እናውቀው ይሆናል። እሱን ለመድፈን ግን አንድ ልብ የለንም። መንፈሳችን  ተሰብሯል። ስለዚህም  በአሰቃቂ  ሁኔታ  እየተበዘበዝን ነው። ራሳችንን ለብዝበዛ  ያጋለጥነው  እኛው ራሳችን  ነን።  የጋራ  ራዕይ  ሊኖረን  ይገባል።

አባ ዠንበሩ የሚነግሩት ለማን ነው? እንላለን። እያንዳንዱ ቃል በህሊናችን እየተሰነቀረ የሀገራችንን እውን ሰቆቃ ለዳተኛው ልባችን እየነገረ ማንነታችንን ሲፈትነን እየታወቀን። አዎ ዕውነት ነው፤ መንፈሳችን ተሰብሯል፤ በዘመናችን የህወሃት ፕሮፓጋንዳና ተግባር ማንነታችን ተሽመድምዷል፤ ወኔያችን ተሰልቧል፤ መሰረታችን ተናግቷልምን ይሻላል? እንመለስ ወደ አባ ዠንበሩ፤

 

“… ሌላው ከእኔ የሚጠበቀው ነገር ምንድን ነው?” ጠየቃቸው / ሚራዥ።

የሰጠመውን መርከብ የምናወጣበትን ቁልፍ ስጠኝ

ምን?”

ቅርፅ የተሰራውን ግማደ መስቀል መልስልኝ።

እሱ መስቀል ቁልፍ ነበር እንዴ?”

ሰአሊነነ ቅድስት! ጉድ መጣ!! አባ ዠንበሩ ሰጠመ ያሉት መርከብ ምንድን ነው? እንላለን ልባችን እንደ ማዕበል እየተነሳና እየፈረጠ። ማንስ ለምን አሰጠመው? መቼስ ነበር የሰጠመው? በውስጡስ ምን ይዟል? መርከቡና አባዎቹስ ግንኙነታቸው ምን ይሆን? ግማደ መስቀሉስ እንደምን የሰጠመው መርከብ መክፈቻ ቁልፍ ሊሆን ይችላል? ለዶ/ ሚራዥስ ቁልፉን ማን ሰጠው? እግዚኦ! እንላላን የጥያቄዎች አይነትና ብዛት በአእምሯችን ሲተራመስብንእናም ምሥጢራቱ ላይ ለመድረስ፤ ውስብስቡን ለመፍታት፤ ዴርቶጋዳን ገፅ በገፅ እያጣፋን እንነጉዳለን

ሣይንቲስት ሻጊዝ እጅጉ ህያው ነው

ከዴርቶጋዳ ረቂቅና አስገራሚ ገፀ ባህሪያት አንዱ ሣይንቲስት ኢንጂነር / ሻጊዝ እጅጉ ነው።  ይህ ሰው አሜሪካንን የህዋው ልዕለ ሃያል ካደረጓት ሳይንቲስቶች አንዱ ነው። ሻጊዝ የኢትዮጵያ ልጅ ነው።እነሆ ሳይንቲስቱ ፊቱን ወደ እናት ሀገሩ መልሷልይለናል ዴርቶጋዳ። መላ እውቀቱን፤ ንብረቱንና እሱነቱን ለሀገሩ መስጠት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋልሳይንቲስቱ ፊቱን ወደ ድሃ ሀገሩ መመለሱ ደግሞ የተለያዩ መንግሥታትን ከፍተኛ ሽብር ውስጥ ጥሏቸዋል። ሻጊዝ ከአሜሪካን መዳፍ እንዳይወጣ የአሜሪካን መንግሥት ለሲ አይ ጥብቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል

ሳይንቲስት ሻጊዝ እጅጉ የዓለማችንን ራዳሮች ሳተላይቶችና የመገናኛ አውታሮች በፈለገው ጊዜ መዝጋት የሚችል አእምሮ ያለው ነው።እና ይህ ሰው ድሃ ሀገሩን ለማንሳት በመነሳቱ አሜሪካንና እስራኤል ተረብሸዋል። በአረብ ሀገራት የስለላ መዋቅራት ታፍኖ ሊወሰድ ይችላል ስለሚሉም ርምጃ መውሰድ አለባቸው። የእስራኤሉ ሞሳድ በእጁ ሊያስገባው መረቡን ዘርግቷል። የሩሲያው ቢም የሻጊዝን ማንነት የሚያውቅ በመሆኑ እንቅስቃሴውን እየተከታተለ ከነህይወቱ አፍኖ ሊወስደው መሰናዶውን አጠናቋል። ከሁሉም በላይ የሚገርመው ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት የስለላ ድርጅት ወኪሎች የሳይንቲስቱን ህይወት የሚቀጥፉበትን አመቺ ጊዜና ሰአት እየተጠባበቁ መሆናቸው ነው። ”…ይህ ሰው እንኳንስ ጭንቅላቱና ሊቅነቱ አስከሬኑ እንኳን ኢትዮጵያን አይረግጣትም” – ሲሉ ዝተዋል፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የላካቸው ገዳይ ሰላዮች። ለምን? ማለታችን ግድ ነው ይህንን ሲነግረን ዴርቶጋዳ።

በዘረኝነት ላይ የተገነባውና ዘረኝነት የተጠናወተው የህወሃት/ኢህአዴግ አገዛዝ በኢትዮጵያዊነት የማያምን በመሆኑ ሀገሪቱን በማፈራረስ ላይ ይገኛል፤ ኢትዮጵያ በጥፋት ዘመን ውስጥ ትገኛለች፤ ከዚህ ጥፋት የሚያወጣትየኖህ መርከብያስፈልጋታል። ሳይንቲስት ሻጊዝ እጅጉ ሀገሩን ከፍፁማዊ ጥፋት ለማዳንየኖህ መርከብ ከሚገነቡላት አንዱ ነው። እና ህወሃትየኖህ መርከብከመታነፁና ከማለቁ በፊት አናፂውን ሳይንቲስት ሻጊዝን እና ባልደረቦቹን ማጥፋት አለበትኢንጂነር ሳይንቲስት ሻጊዝ እጅጉ ተከቧል፤ በማንኛውም ሰዓት ከከባቢዎች በአንዱ ህይወቱ ልትጠፋ ትችላለችሻጊዝ እጅጉ ግን ራዕይ አለው፤ ለሀገሩ ብርሃን የሚፈነጥቅ ከድህነትና ከአምባገነኖች የሚያላቅቅ ራዕይ አለውመንገደኛ ነው ሻጊዝ፤ ሩቅ አላሚሩቅ ተጓዥእንቀንጭብ ከዴርቶጋዳ፤

“…ኢትዮጵያ መጪው ትውልድ ከፍሎ የማይጨርሰው ብድር ተበድራለች። እያንዳንዱ ወጣት እያንዳንዱ ታዳጊ የሚወርሰው ሌላ ነገር የለም።የገንዘብ ዕዳ፤ የሞራል ዕዳ፤ የደም ዕዳ ኢትዮጵያውያን ነዳጃቸው ላይ ቆመው እየለመኑ ነው። ኢትዮጵያውያን ዩራኒየማቸው ላይ ቆመው ነዳጅ አጥሯቸዋል።የኢትዮጵያ ጥቋቁር አልማዞች ጥቁር አልማዛቸው ላይ ቆመው እየተመፀወቱ ነውወንድሜ ሚራዥእኔና አንተስ እስከመቼ ዝም እንላለን?..እስከመቼ ድረስ ዳር እንቆማለን?” ሳይንቲስት ሻጊዝ እጅጉ ለዶ/ ሚራዥ የተናገረው ያገጠጠ ሀቅ ሰውነታችንን እንደ ኤሌክትሪክ ንዝረት ሲወረው ይሰማናል። ጥያቄው ለኛም መሆኑ ይከሰትልናልና።

ሻጊዝ የሚናገረው የእያንዳንዳችንን ዐይነ ውሃ እየተመለከተ እንደሆነ ሁሉ ይሰማንናሀገራችን ኢትዮጵያ በዘመነ ህወሃት ምዝበራዋና ፍዳዋ፤ ሰቆቃዋና የደም ዕዳዋ ገዝፎ በጣዕር ድምፅ ስትጠራንና ዓይኖቿ የመከራ ዘመን ልጆቿን መድህንንት ለማግኘት ሲንከራተቱ ይታየንናበእስከዛሬውየምንቸገረኝምግባራችን ሀፍረቱ ያሸማቅቀናል። ስለምን እኛ ልንወጣው የሚገባንን ዕዳ ለመጪው ትውልድ ለልጆቻችን እናስተላልፍላቸዋለን? ስለምን ያለዕዳቸው ዕዳ እንሰጣቸዋለን? ዝምታችን የሚያበቃውስ መች ይሆን? እስከመቼ በዚህ እንዘልቃለን?…እንላለን ለራሳችን፤ ህሊናችን ሲወቅረን እየታወቀን

እንመለስ ወደ ዴርቶጋዳ ትረካ፤

እስከመቼ!” አለ ሚራዥ ውስጡ ተቃጥሎ። እኔ በበኩሌ ከአሁኗ ደቂቃ ጀምሮ ማንኛውንም ተግባር ለመፈፀም ዝግጁ ነኝ። ግን ምን ማድረግ እችላለሁ? የችግሩ ሰንሰለት ተቆርጦ የማያልቅ ነው። የሰው ሀይልና በቂ ገንዘብ ያስፈልጋል።ይህ የሚራዥ ጭንቀት ቀልባችንን ይስበዋል። ዕውነቱን ነው ሚራዥ እንላለን ምን ማድረግ እንችላለን?”እናስተጋባለን እኛም የሚራዥን ጥያቄ።

ዕውነት አይደለም ይላል ሳይንቲስት ሻጊዝለሚራዥም ለኛም። በቂ ገንዘብ ብቻ አይደለም የሚፈልገው። ብዙ ህዝብም አይደለም የሚፈልገው። ልብ ለልብ ከተገናኘንና አብረን ከሰራን እንኳንስ አንዲት ሀገር ዓለምን መለወጥ የሚያስችል ዕውቀትና አቅም አለን…” ዕቅጩን ይነግረናል ሻጊዝ፤ ለዶ/ ሚራዥ ብቻ ሳይሆን በቀጥታ ለኛ የሚመልስልን እስኪመስለን

“…ይልቅ እኔም አንተም ሞት ሳይቀድመን ወገኖቻችንን ከሞት የምንታደግበት ወቅት ላይ ነን።ኢትዮጵያ ተስፋ  በቆረጡ  ወጣቶች ተሞልታለች። ራዕይ ያጡ ህዝቦች ጎተራ ሆናለች። ራዕይ የሌለው ህዝብ ደግሞ ይጠፋል። የተስፋው መስኮት መከፈት አለበት። ኢትዮጵያን ሌላ ሰው መጥቶ አይለውጥልህም። አንተን ለመለወጥ ሌላ ሰው አይመጣም። ይህን ሀቅ እወቅ። ኢትዮጵያ ውስጥ ብትን የሚሉት ቻይናዎችና አረቦች ሁሉ ለአንተ ብልፅግና ግድ የላቸውም። ሀገርህን ከቅጥረኞችና ከወሮበሎች የምታድንበት ጊዜው አሁን ነው።

አንድ ጥያቄ እንድጠይቅህ ፍቀድልኝአለው ሚራዥ

ጠይቀኝ…”

ወደ ጦር ሜዳ እየላከኝ ነው?”

                                             *         * *

ይህ የሻጊዝና የሚራዥ ምልልስ አንዳች ልዩ ስሜትን በውስጣችን ሲያቀጣጥል ይሰማናል። ተስፋ ይታየናል። ያም ተስፋ የሚጀምረው ከራሳችን እንደሆን ስንገነዘብም በራስ የመተማመን ስሜታችን ከውስጣችን ሲንር ሲንተገተግ፤ ችቦው ሲለኮስ ይታወቀናል። ዕውነት ነው እንላለን፤ ራዕይ የሌለው ትውልድ ተስፋ የለውም፤ ተስፋ ከሌለው በመንፈስም በምግባርም የጠወለገ ትውልድ ይሆናል፤ የጠወለገ ትውልድ ደግሞ እያዘገመ ይሞታል። እና ጊዜው አሁን ነው እንላለን። ሀገራችን ማጥ ውስጥ የገባችውና እንዲህ ያለው አሳዛኝና አደገኛ ደረጃ ላይ የደረሰችው በኛው ትውልድ ነው። ተስፋ በቆረጠና ራዕይ በራቀው ወጣት ትውልድ ለመሞላቷ አንዱ ምክንያት እኛ በእድሜ የሰነበትነው (1966 / አብዮት ፍንዳታና ማግስት ወስጥ የተሳተፍነው/ባንሳተፍም የኖርነው) ትውልድ አካላት ነን፤ አንድም በዝምታችን አንድም በጥፋት ተባባሪነታችን።

አዎ እውነት ነው! ኢትዮጵያን ሌላ ስው መጥቶ አይለውጥልንም። ኢትዮጵያ በሀራጅ እየተሸጠች ነው፤ ለቻይናው ለህንዱ ለአረቡ። ኢትዮጵያውያን በገዛ ሀገራቸው ባይተዋርና ባርያ፤ በምርታቸው የበይ ተመልካች ሆነዋል። የደደቢቱ ህወሃት ክፉ አገዛዝ የኢትዮጵያን ለም መሬት የሚቸበችብላቸው ባዕዳን ሌት ተቀን የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት የሚጭኑት ወደ ሀገሮቻቸው እንጂ ለኢትዮጵያውያን ዕድገትና ብልፅግና በሚውልበት መንገድና ስምሪት በኢትዮጵያ ምድር አይደለም። ዘርፎ ለዘራፊ በሯን በርግዶ በከፈተው ወንጀለኛና ወሮበላ የህወሃትና ህወሃታውያን አገዛዝ አዝማችነት ዓለም አቀፍ የምዝበራ ቡድናት ኢትዮጵያን በያቅጣጫው እየተቀራመቷት ናቸው። ማን ከእኛ በቀር ሊያድናት ይችላል?…ከእኛስ በቀር ማን ህይወቱን ገብሮ  ኢትዮጵያን ሊታደጋት ይችላል?

እንቀጥል ቅኝታችንን፤

የሻጊዝ ራዕይ ወዴት ያመራ ይሆን? የሚራዥስ ተልዕኮ?…ዴርቶጋዳ ሴራውና ታሪኩ እንደ ሸረሪት ድር እየተወሳሰበና እየሰፋ፤ ከድርጊት ወደ ድርጊት ከምሥጢር ወደ ላቀ ምሥጢር ሲወነጨፍ፤ ልባችንም አብሮ እየተወነጨፈ ይነጉዳል

እንቀንጭብ  ከትርክቱ  ሂደት፤

እነሆ በጃንዋሪ 13 2006 ከኦስቲን ቴክሳስ ታላቅ የሀዘን ዜና በዓለማችን ህዋ ላይ ተናኘ፤ የሳይንቲስት ሻጊዝ እጅጉ ሞት።

ሳይንቲስቱ ፊቱን ወደ ድሃ ሀገሩ በመለሰና ሀገሩን ከጥፋት ለመታደግ የፖለቲካ መዋቅር ባቆመ በሁለት ዓመት ውስጥ፤ ኢትዮጵያዊው የህዋ ሳይንቲስት ሻጊዝ እጅጉ በተወለደ 58 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷልአሉን አሜሪካኖቹ። እልል አለ የህወሃት/አህአዴግ  አገዛዝ፤ እፎይ ብሎ ተነፈሰ፤ ሻጊዝን አድነው እንዲያጠፉለት የላካቸው ነፍሰ ገዳዮች በእጃቸው የሳይንቲስቱን እስትንፋስ እንዳቆሙለት ሁሉ እየተሰማው። ይህ  እውነት ነው፤ ሻጊዝ ሞቷል።ግና ሳይንቲስት ሻጊዝ እጅጉ ዕውን የሞተው ተፈጥሯዊ ሞት ነውን?! ዴርቶጋዳ ስለሻጊዝ ሞትና ከሞት ወዲያ ባለው ህያው ህይወቱ ቀልባችንን ሰድሮ፤ ሀዘናችንን አስውጦውስብስቡን ታሪክ እያፍታታያልተገለጠልንን እየገላለጠልን ትረካው ይንቆረቆራልምሥጢሩም ይበራያል

                                        *       * *

ሳይንቲስት ኢንጂነር / ሻጊዝ እጅጉ አልሞተም፤ በዴርቶጋዳ፤ በዴር 33 በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ከርሰ ምድር፤ በምድረ ኢትዮጵያ፤ ዘላለማዊ ህያውነትን ተቀዳጅቷል። እንዴት? ለእኒህና ለሌሎችም የዴርቶጋዳ ምሥጢራትዴርቶጋዳን ማንበብ ብቻ ይሆናል መፍትሄው። ቁንፅል ስዕላዊ  ቅኝታችን  ግና ይቀጥላል፤  

አባ ዠንበሩ በሳይንቲስት ሻጊዝ እጅጉ ውስጥ ህያው ሆነዋል። ለኢትዮጵያ ክብር፤ ልዕልና እና ብልፅግና ህልም የነበራቸው። ነፃነቷን፤ ታሪኳንና ቅርሷን ጠብቀው ያቆዩን አባቶቻችን  ተምሳሌ ናቸው አባ ዠንበሩ። እና ሳይንቲስት ሻጊዝ የአባ ዠንበሩን ህልም ዕውን አደረገና ሞተ።አባ ዠንበሩም ሞቱ፤ ህልማቸውና ራዕያቸው ግን አልሞተም።

አዎ ሳይንቲስት ሻጊዝ ሞቷል፤ ዓርማው ግን አልወደቀም። በዶ/ ሚራዥ፤ በሞሳዷ ሲራጳ፤ በአሜሪካ አየር ሀይል ውስጥ ዝነኛ አብራሪ በነበረው ጌራ፤ በቁጥር ሁለት የዴርቶጋዳ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶችና ምሁራን፤ በዴር 33 ራዕዩ ዛሬም አለ። እኒህ ሁሉና በዚህ ቅኝት ያላነሳናቸው  የዴርቶጋዳ ገፀ ባህርያት  በታሪኩ ውስጥ ባላቸው ሚና እና ሰብዕና ዕውቀትና ተልዕኮ አንባቢን በስሜት ማዕበል እያናጡ፤ በታሪኩ መርከብ እያንሳፈፉ፤ ከምዕራፍ  ምዕራፍ  እሚያስፈነጠሩ ናቸው

ዴር 33 በሳይንቲስት ሻጊዝ የተነደፈች በዴርቶጋዳ ጥበበኞች ህልውና ያገኘች፤ እንደ መኪና በየብስ እንደ አሞራ በሰማይ የምትበር የተራቀቀች የዴርቶጋዳ ውጤት ናት። ዴር 33 የዴርቶጋዳ አባላት ራዕይ ተምሳሌ ናት። ዴር 33 የሳይንስ ልቦለድ ናት አትበሉ። ሻጊዝ እጅጉ ዛሬ ዓለም የሚገለገልበትን ኤስ (አቅጣጫ አመልካች) አልፈለሰፈምን? ታዲያ ዴር 33 እንደምን የሳይንስ ልቦለድ ብቻ ልትሆን ትችላለች? ዴር 33 ራዕያችን ናት፤ የአባ ዠንበሩ ራዕይ፤ የሻጊዝ ራይዕ፤ የኢትዮጵያ ወጣት ትውልድ ራዕይ

ይልቅስ ለዚህች ልዩ የዚህ ትውልድ ራዕይ 33 ቁጥር ለምን መታወቂያዋ ሆነ? አዎ! ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ከዘመናት የዲያቢሎስ ባርነት ነፃ ሊያወጣ ከሀጢያቱም ሊያነፃው ራሱን አሳልፎ በመስቀል ተቸንክሮ የሞተው 33 ዓመቱ ነበር።እና የዴር 33 ተምሳሌነት ይህ ወጣት ትውልድ የሀገሩ መድህን፤ የሀገሩ ትንሳኤ፤ የሀገሩ ራዕይ ሆኖ ሀገሩን ይታደጋት ወገኑኑም ከናዚስት ህወሃት ባርነት ነፃ ያወጣ ዘንዳአመልካች ትሆን? ማለታችን ግን አልቀረም።

ልጅ በአባቱ  ሀጢያት አይኖርም

አባ ፊንሐስ ወንጀለኛ ናቸው። አባ ፊንሐስ ከሀገራቸው ብሶትና ሰቆቃ ይልቅ ግላዊ ህይወታቸው የሚደላደልበትንና የሚከብሩበትን ህልም ሲያልሙ  – ለዚህም ደፋ ቀና ሲሉ የኖሩ አባት ናቸው። አባ ፊንሐስ መንፈሳዊ አባትነታቸው ለአለማዊ ህይወታቸው ካባ ሆኖ የሸፈነላቸው አባት ናቸው።እንዲህ ያሉ አባ ፊንሐሶች በየትውልዱ ሁሉ ተፈጥረዋል፤ ነበሩም። ዛሬም ናዚስት ህወሃትን አገልጋዮች ብዙ አባ ፊንሐሶች ሞልተዋልየዴርቶጋዳው አባ ፊንሐስ ለኒህ ሁሉ ተምሳሌያዊ ገፀ ባህሪ ናቸው።

አባ ዲዲሞስ ሩቅ ተጓዥ ራዕይ የነበራቸው አባት ነበሩ። አባ ዲዲሞስ አዋቂ ናቸው፤ የተማሩ። የአባ ዲዲሞስ ራዕይና ዕውቀት ግና በሥልጣን አባዜ ተሸበበ፤ ታወረ። አቡነ ጵጥሮስን የተቃወሙትም ለዚሁ ነበርሥልጣንን በእሳቸው በኩል ማግኘት ከመቻላቸው በፊት ስለሞቱ። እና አባ ዲዲሞስ ዕውቀታቸውንና ሩቅ ተጓዥ ራዕያቸውን ለሥልጣን አባዜ የሸጡ አባቶቻችን ሁሉ ተምሳሌ ናቸው። በየትውልዱ ብዙ አባ ዲዲሞሶች ተፈጥረው አልፈዋል፤ ዛሬም በዚህ ትውልድ ውስጥ የናዚስት ህወሃት አገልጋይ የሆኑ አያሌ አባ ዲዲሞስ ምሁራንም ተናኝተው ይገኛሉ

የሞሳዷ ሲጳራ የአባ ፊንሐስ ልጅ ናት። ሲጳራ ግን በአባቷ ወንጀል አልኖረችም። ጌራ እና ሞረዳ የአባ ዠንበሩን ራዕይ አንግበዋል። ሚራዥ በአባቱ ፈለግ ተተክቷል።  ሁሉም የሳይንቲስት ሻጊዝን አርማ አንስተዋል። ነገ ሌላ ቀን ነው፤ ነገ በኢትዮጵያ አዲስ ቀን ይወጣል

እኒህ ምርጥ ወጣቶች በዴርቶጋዳ የምናገኛቸው የዚህ ትውልድ ተምሳሌት ናቸው። እኒህ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ገንቢ ወጣቶች በአባቶቻቸው ሀጢያት አይኖሩም። በአባቶቻቸው ራዕይ እንጂ!! ኢትዮጵያን ዛሬ ናዚስት ህወሃትና በ አምሳሉ የፈጠራቸው ህወሃታውያን  ከከተቷት  መቀመቅ የሚያወጣትም ይህ ወጣት ትውልድ ነው። ይነሳል ክንዱን አጠንክሮ፤ በኢትዮጵያዊነቱ ተባብሮ! ያውለበልባል አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራውን ከፍ አርጎ! ይዘምራል በህብረ ድምፅ፤ ከአድማስ አድማስ ያስተጋባልይላል ኦርያ ኢትዮጵያ!…ማሔር ሻላል ሐሽ ባዝ!!

መሸበቢያ

ክብር የእግዚአብሄር ነው። ምሥጋናም በእግዚአብሄር ይሰምራል። አስጀምሮ ላስጨረሰኝ ዴርቶጋዳለብላቴናው ይስማዕከ ወርቁክብር ምሥጋናዬ በላይኛው ፈጣሪ ስም ባለህበት ይድረስህ። በነገይቷ ኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል በወጣቱ ትውልድ ራዕይ ተስፋ ሰጥተኸናልናፀሎታችን እውን ይሆን ዘንድ እንማልዳለን።

እነሆ ተስፋችንን በዴርቶጋዳ ከውስጣችን እንደቀሰቀስከው፤ የላይኛው መልዕክተኛ መልዐክም በውድቅት ሌሊት፤ በድቅድቅ ጨለማ ከተኛህበት መጥቶ ደግሞ ደጋግሞ ይቀስቅስህ። ከራስጌህም ቆሞ መለኮታዊ ብርሃኑን ያብራልህ። ከክንፉም ላባ ነቅሎ፤ እንደ ብዕርም ቀርፆ  በእጅህ ያስጨብጥህ። መለኮታዊ የኢትዮጵያ ትንሳዔ መልዕክቱም በመላዕክት ልሳን ይገለጥልህ። በብራናህም ትከትበው ዘንዳተስፋ ላጣው ለተስፋይቱ  ምድር ህዝብ ተስፋ ትናኝም ተስፋም ታዳርስ ዘንዳ ደግመህ ደጋግመህ ፃፍ። ዛሬም ነገም ለዘለዓለሙአሜን!

 

ሰኔ 2010 ዓ/ም (ጁን 2018)

ሲድኒ አውስትራሊያ

mmtessema@gmail.com

ደራሲ ይስማዕከ ወርቁ የሚገኝበትን ሁኔታ የሚያሳዩ ዋቢ ቪዲዮዎች

https://www.youtube.com/watch?v=Hlt17elS844

https://www.youtube.com/watch?v=hMcPk9c0Ajo&t=92s

https://www.youtube.com/watch?v=Wl3KhASzpB0&feature=youtu.be

Filed in: Amharic