>
5:21 pm - Thursday July 21, 2270

ግልጽ ደብዳቤ ለተከበሩ ጠ/ ሚኒስትር (የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ)

 ግልጽ ደብዳቤ ለተከበሩ ጠ/ ሚኒስትር
ጉዳዮ፣  ለህዝበ ሙስሊሙ ጥያቄዎች መልስ የመስጠት ተነሳሽነትዎን ይመለከታል!??!
የኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ
በሰኔ 8/2010 በዒድ አልፈጥር በዓል እለት በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ መስጠትዎ ይታወቃል። በመግለጫዎ ወቅታዊ የአገራችንን ፓለቲካዊ ትኩሳቶችን እልባት ለመስጠት እንደሚሰሩ እና በተለይም የህዝበ ሙስሊሙን ማንኛውንም ጥያቄዎች ለመመለስ ዝግጁ መሆንዎን መግለፅዎ በህዝበ ሙስሊሙ ውስጥ አዲስ ተስፋ የፈጠረ አጋጣሚ ሆኗል።
     እኛ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላለፋት አመታት መንግስት ከሁሉም ሃይማኖቶች በእኩል ርቀት ነፃ እና ፍትሀዊ በሆነ አግባብ  መቆም ሲገባው በሙስሊሙ ተቋማት እና የእምነት ጉዳዮች ውስጥ በግልፅ ጣልቃ በመግባቱ የተነሳ የመነጩ  የመብት ጥሰቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመቃወም እና ለመታገል አደባባይ ከወጣን ስድስት አመታት ተቆጠሩ። በሙሉ የሀገራዊ ሃላፊነት ስሜት እና ኢትዮጵያ ሀገራችን የሁሉም እምነቶች እና የሃይማኖቶች መብቶች የተከበሩባት ሆና ማየትን በማለም  ያደረግነው ሰላማዊ ትግል እነሆ ለመሰል ትግሎች በር ከፍቶ የለውጥ ቀንዲል መሆን ቢችልም ህዝበ ሙስሊሙን ግን ያለ ስሙ ስም ያለ ግብሩም የከፋ ስቃይ እና መከራ እንዲደርስበት አድርጎል።
           እነዚያ አመታት አልፈው በሀገሪቱ ፈጣን የሆኑ የፓለቲካ ለውጦች ቢስተናገዱም ያነሳነው ጥያቄ መልስ ሊያገኝ እንደሚችል የሚጠቁም የአመለካከትም ሆነ የተግባር ፍንጭ ማየት ሳንችል እስካለፈው የረመዳን ፍች በዓል ድረስ ቆይተናል።
   ክቡር ጠ/ ሚኒስትር፣
   መንግስትዎ እና ያዋቀሩት ካቢኔ በዓይነቱ የተለየ እና ለሀገራችን ታሪክና ለህዝባችን ክብር የሚመጥን ምክንያታዊ ፓለቲካ ማራመድ በመጀመራችሁ መንግስትዎ ሰፊ ተቀባይነትን ማግኘት ችሏል።የዚህ ቅቡልነት ምንጩን ጠለቅ ብለን ስንፈትሸው በዋናነት የምናገኘው ለህዝቦች ማንነት፣ሀገራዊ ድርሻ እና ሃላፊነት በሚመጥን መልኩ ከላይ ከአመራሩ የታየው የአመለካከት ለውጥ ሆኖ እናገኘዋለን።
ክቡር ጠ/ሚኒስቴር፣
   ከላይ በተጠቀሰው መግለጫዎ የህዝበ ሙስሊሙን ማንኛውንም ጥያቄ ለመፍታት ያለዎን ዝግጁነት መግለፅዎን በሁለት መሠረታዊ  ምክኒያቶች በመልካምነት ተቀብለነዋል። በመጀመሪያ ለአመታት በፅናት እንደ ህዝብ ዋጋ ስንከፍልለት የኖርነው ጥያቄ ደጋግመን እንደምንለው ያልተመለሰ ጥያቄ መሆኑን ዕውቅና መቸሩ ነው። የጥያቂያችን አለመመለስ ሳያንስ  ጥያቂያችን ተቀልብሶ የሚዲያ ፕሮፖጋንዳ እና የሃይል እርምጃ ሰለባ ተደርገን ከመቆየታችን አንፃር ላልተመለሰው ጥያቂያችን እልባት ለመስጠት የመጀመሪያው እርከን የሆነውን “ህዝብ ያልተመለሰለት ጥያቄ አለው” ብሎ የሚነሳን መሪ ዕውቅና ስንሰጥ ችግሩን በሚገባ የተረዳ መሪ ለመፍትሄውም ቁርጠኛ እንደሚሆን ስለምናምን ነው።
    ተነሳሽነትዎን በበጎ የወሰድንበት ሁለተኛው ምክኒያት ችግሩን ከስሩ የመፍታት አቅም እንዳለዎ በማመን እና በመግለጫዎም ይህንኑ በመጠቆምዎ ነው። በሁለት ወራት የስልጣን ላይ ቆይታዎ እዛም  እዚህም  ለሚነሱ ጥያቄዎች እሣት የማጥፋት ስራ ሳይሆን እንደ መንግስት ለህዝብ ጥያቄ ሊኖር የሚገባውን አመለካከት ስር ነቀል በሆነ መልኩ በመቀየርዎ ችግሮቹ በአፈፃፀም ደረጃ በቀላሉ የሚፈቱበት አየር እየተፈጠረ መሆኑ ግልፅ ነው። ህዝበ ሙስሊሙ ላነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ያልቻለው የመሪ ድርጅቱ (መጅሊስ) መዋቅር ውስብስብ ሆኖ ሣይሆን መንግስት በጉዳዩ ለይ የያዘው አሉታዊ አቋም በመኖሩ ነበር።
      በመሆኑም መንግስትዎ ማንኛውንም ችግር በመወያየት ለመፍታት ዝግጁ መሆኑን በሚዲያ ማሳወቁ ቀጣዩ ሂደት አተገባበር እንደሚሆን ይታመናል።የአሁኑን መግለጫ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ጊዚያዊ የፓለቲካ ግለት ማብረጃ  ሳይሆን ወደ መሬት ወርዶ የሚተገበር  እንደሚሆን እናምናለን።በዚህም ም ክንያት አተገባበሩ ለጥያቄዎቹ መሠረታዊነት፣ህዝቡ ካደረገው ሰላማዊ ትግል እና መንግስትም ለህዝብ ፍትሃዊ ጥያቄዎች ከሚሰጠው ዋጋና ክብደት አንፃር ተመጣጣኝ በሆነ ሂደት እና ጥልቀት እንዲከናወን እንፈልጋለን፣አጥብቀንም እንጠይቃለን።ችግሮቹ በሙሉ የመንግስትን ትኩረት በሚያመላክትና የባለመብቶቹን ስነልቦና ሊያረካ በሚችል መልኩ ይፈቱ ዘንድ የበኩላችንን ለማበርከት በህዝበ ሙስሊሙ ተወክሎ ሲንቀሳቀስ እንደነበረ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ዝግጁነታችንን ስንገልፅ የጥያቄዎቹ መመለስ እና የሚመለሱበት መንገድ መሰረታዊ በሆነ መልኩ የተሣሠሩ እንደሆኑ በማስታወስ  ጭምር ነው። ይህንን  የምንለው  ለችግሩ የሚሰጠው መፍትሄ ዘለቄታዊነቱ አስተማማኝ የሚሆነው የጉዳዩ ባለቤትን  እና  ግንባር ቀደም ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ በሚደረግ ቀጥተኛ ውይይት  ሲካሄድ በመሆኑ ነው።
        በመጨረሻም በሀገራችን ላይ አንዣቦ ከነበረው አስፈሪ አደጋ በተወሰነ ደረጃ  እያገገምን ባለንበት በዚህ ወቅት የለውጥ ሂደቱን የሚያደናቅፋ ክስተቶች እዚህም እዚያ እየተስተዋሉ በመሆኑ ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ለመንግስትዎ ሁለንተናዊ ድጋፋን እንደሚቀጥል ልናረጋግጥ እንወዳለን።
ለህዝቦች ጥያቄ መልስ የመስጠት ሂደት ውስጥ እንድንገባ ላደረገን አላህ ምስጋና እያቀረብን  እየተወሰዱ ላሉ ፖለቲካዊ እርምጃዎች አክብሮታችንን ለመግለፅ እንሻለን ። መንግስታዊ ብልሹ አስተሳሰብና አሰራር የፈጠሯቸውን ችግሮች በመንግስታዊ እና ህዝባዊ ወገንተኝነት ለመፍታት በሚደረገው ጥረት በራሳችንም ሆነ ከሌሎች የሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን ለስኬታማነቱ የበኩላችንን እንደምንወጣ እየገለፅን ለሃገራችን እና  ለክቡር ጠቅላይ  ሚኒሰትራችን መልካሙን ሁሉ እንመኛለን።
ሃገራችን ኢትዮጵያን አላህ የሰላም፣ የፍትህ፣ የነፃነትና የብልፅግና ሃገር ያድርግልን! አሚን
Filed in: Amharic