>

ቦሌ አየር መንገድን ወደ ሚኒሊክ አደዋ አየር መንገድ (ሚሊዮን አየለች)

በቅርቡ የባህርዳርን ‹‹ግንቦት 20›› አየር መንገድን ወደ ጀግናው ‹‹በላይ ዘለቀ›› አየር መንገድ እንዲቀየር እየተደረገ ያለው የማህበራዊ ሚዲያ እንቅስቃሴ ይበል የሚያሰኝና ሊገፋበት የሚገባ ተግባር ጭምር መሆኑን ላሰምርበት እወዳለሁ አንባ ገነን መንግስት ዋነኛ መለኪያው ህዝቡ ያላመነበትን ከህዝቡ ጋር ሳይወያይ የራሱን ስሙን ባልተቀበሉት ህዝብ ላይ መጫን ነው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት ግንቦት 20 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የዚህ ትምህርት ቤት ምስረታ ከዚህ መንግስት ጋር የተያያዘ አውድ ይኑረው አይኑረው ብዙ መረጃው ባይኖረኝም ምናልባትም ስሙ ተቀይሮ ሊሆንም እንደሚችል መገመት አይከብድም ብዙ አንባ ገነኖች ስማቸውን በየቦታው እንዲነሳ ይፈልጋሉ፡፡
የኢህአዲግ ማእከላዊ ኮሚቴ ሰሞኑን ተሰብስቦ የወሰነው ውሳኔ በአብዛኛው የሀገሪቷ የጀርባ አጥንት ሆነው ሰፊውን ህዝብ ከፍም ዝቅም እያለ የሚያስተዳድሩት ትልልቅ የሀገሪቷን ንብረቶች ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ መወሰኑ በብዙሀኑ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት አላገኘም እርግጥ አንባገነናዊ ገዢ ኃይል የህዝብ ይሁንታና ተቀባይነት ጉዳዩ ሆኖ አያውቅም በአብዛኛው ወደ ግል ይዞታ ለመተላለፍ የታሰቡት ውሀ፤ማብራት፤ስልክ እና ግዙፉ አየር መንገዳችን ነው እነዚህ ትልልቅ የሀገራችን ህዝብ በትንሽ ምጣኔ ሀብት የሚጠቀምባቸው የህዝቡ የኑሮ መተከዣ የሆኑት ተቋማት ወደ ግል ይዞታነት ሲያስተላለፉት ምን ሊከሰት እንደሚችል መገመት አያቅትም የሀገሪቷ ህዝብ ምጣኔ ሀብቱን ሳያሳድግና የመክፈል አቅሙን ሳያጎለብት ወደ ግል ይዞታነት ማስተላለፍ ሰፊውን ህዝብ ከጥቅም ውጪ ማድረግና በሀገሩ ሀብት ባይተዋር እንዲሆን በር መክፈት ነው ለዚህ ፅሁፌ ግን ዋነኛ ሀሳብ እንዲሆነኝ የፈለኩት እንደነዚህ አይነት ውሳኔዎች ሀገሪቷ አለኝ የምትለውን  በዓለም ላይ ትርፋማነቱ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ የሚሄደው እና መዳረሻ ከተሞችን ከነበረበት በብዙ እጥፍ እያደረሰ ያለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአንድ ፓርቲ ቀጭን ትእዛዝ ከመንግስት ጋር ለግል ባለ ሀብቶች በSHAR ለገበያ ማቅረቡን ስንሰማ ከዓመት አመት ትርፋማ የሆነን ድርጅት ለገበያ ያቀረበ ከዓለማችን የመጀመሪያዎቹ ያደርገናል እርግጥ ይሄ አገዛዝ ብዙ ከዓለም ሀገራት የመጀመሪያዎቹ ሊያደርጉት የሚችሉትን አሳፋሪ ኩነቶችን ፈፅሟል የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት ንዶ በራሱ እጅ ፅሁፍ ለተባበሩት መንግስታት እገነጠላለው ያለችው ሀገር እንኳ ሳትቀድመው ኤርትራ እንድትገነጠል ድጋፍ የሰጠ የመጀመሪያው አሳፋሪ ድርጊት፤ የባህር በር ሀገሪቷ በሚያስፈልጋት ወቅት አሰብን የሚያህል የባህር ወደብ የግመል መጠጫ ነው ብሎ ለጅቡቲ በቀን ባለ ብዙ ሚሊየን ከፋይ እንድትሆን ያደረገ ሌላ ከዓለም የመጀመሪያው ጅል ገዢ፤ በጦርነት ያሸነፈውን ሀገር በጠረፄዛ ውይይት ያለ ይግባኝ በመሸነፈው ወደር ያልተገኘለት አሳፋሪ መንግስት ይሄነን ሁሉ ያደረገ ቀጥሎ ሌሎች አሳፋሪ ድርጊቶችን ለመፈፀም እንደሚነሳ መገመት የግድ ጠንቋይ መሆን አልያም ትንቢት ተናጋሪ መሆን አይጠበቅብንም እያየነው ያለነው ይሄንን ስለሆነ፡፡ አየር መንገዱ ለውጪ አልያም የሀገርን ሀብት ሙልጭ አድርገው ለበሉት ባለ ሀብቶች ሸጠ ማለት ቀድመው የሚከውኑት ቢዝነሳቸውን ሊያስተዋውቁበት የሚችልን  ለኢትዮጵያ አይከን የሆነውን አርማና ስም ማስወገድ ነው ይሄ ደግሞ አንድ ሀገሪቷ ትተዋወቅበታለች የአለም ሀገራት ሀገሪቷን  ከነታሪኳ ሊያውቁት ይገባል ብለን ያሰብነውን አየር መንገድ ከነ አካቲው ለህዝቡ እንግዳ ለሀገሩ ባዳ እንዲሆን መፍቀድም ነው፡፡ ይሄ አይነቱ አሳፋሪ ድርጊት አሁን ላይ ያሉት የኢህአዲግ ገዢዎች ሁለት ጊዜ ብቻ ሳይሆን አስር ጊዜ ሊያስቡበት ይገባል፡፡
ከዛሬ አመት በፊት የቦሌን አየር መንገድ በተመለከት ሀገሪቷ የምትመካበበት ግዙፉ የአፍሪቃ ከተማ ላይ ያለ አየር መንገድ ሀገሪቷንም ታሪኳንም በሚያስጠራ መልኩ ስመ ስያሜውን ሊያገኝ ይገባል የሚል አንድ ሀሳብ አንስቺ ነበር በዚህ ፅሁፍ ይህንኑ ለመድገም እፈልጋለሁ
የሚኒሊክ ስም ሲነሳ ዛር እንደያዘው የሚያንቀጠቅጠው  የሚጥል በሽታ እንዳለበት እየተነሳ የሚፈርጥ እንዳለ በሚገባ እረዳለሁ ለሚጥለውም ዛር ለያዘውም መድሀኒቱ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለ ከሱ አቅምሰነው ከበሽታው ነፃ እንዲወጣ እናደርገዋለን ለእነዚህ ሰዎች ዋነኛ መድሀኒታቸው በተረት ተረት የታሪክ አተላ ውስጥ ተደብቀው በየጊዜው የሚኒሊክ ስም በተጠራ ቁጥር አብሾ እንዳለበት ዘለው ዘለው የሚያጓሩ ከትክክለኛው ታሪክ ተቋዳሽ ሆነው ለህሊናቸውም ለአእምሮአቸውም በሽታ እረፍት ቢሰጡት እመኛለሁ፡፡
የብዙ ሀገራት ታላላቅ የህዝብ መዳረሻቸው የተገነባው ሀገሪቷን በገነቡት ለሀገራቸው የጀርባ አጥንት ናቸው ብለው እንደ ውዳሴ ማርያም ለህዝቦቻቸው ብሎም ለአለም ሀገራት በሚሰብኳው ታላላቅ ጀግኖቻቸው ነው መንገዳቸው፤መዳረሻ ከተማቸው፤አንዳንድ የህዝብ መሰብሰቢያ ቦታቸው ሳይቀር ለሀገራቸው ከትንንሽ አስተዋፅኦ እስከ ትልልቅ ለሀገራቸው ሲሉ ደም እስከ ገበሩላቸው በታላላቅ ጀግኖቻቸው ስም ይሰይሙላቸዋል ትውልዱም ለሀገር ለህዝብ የሚከፈለው መሰዋትነት ውሎ አድሮ ታላቅ ክብር እንደሚያስገኝ የወደፊታቸውን በማመን ለሀገራቸው ሲሉ የሚኖሩ ህፃናትን መፍጠር ይችሉበታል፡፡ እንዲሁ የአየር ማረፊያቸውም   መንገደኞች ወደዚህ ሀገርና ከተማ ሲሄድ የሀገሪቷን ታሪክ ለማወቅ ከሀገሪቷ አየር መንገድ ይነሳሉ የሀገሪቷ አየር መንገድ በራሱ የሀገሪቷን ታሪክ የያዘ በራሱ ታሪክና ቤተ መፃሕፍት ነው፡፡
በእርግጥ በኛም ሀገር በአንድ አንድ ክልሎች በጀግኖች ኢትዮጵያውያን የተሰየሙ ጥቂት አየር መንገዶች እንዳሉን ይታወቃል የመቀሌው አሉላ አባ ነጋ አየር መንገድን እና አፄ ቲዎድሮስ አየር መንገድን እንደ ምሳሌ ማንሳት እንችላለን እነዙኽ ጀግኖች ለኢትዮጵያ ታሪክ የጀርባ አጥንት የጀርባ አጥንት መሆናቸው አይጠረጠርም በነገራችን ላይ ራስ አሉላ የኤርትራ ተወላጅ መሆናቸው ልብ ይለዋል በመቀሌ ላይ መገንባቱ ኤርትራ የሁለት አንባ ገነን ሰዎች ስምምነት ይለያት እንጂ ህዝብ ለህዝብ ባለው ግንኙነት ደረጃ እንዳልታመነበት የሚያሳይ ነው ምን አልባት አንድ ቀን በጣይቱ ስም አስመራ ላይ የአየር መንገድ እንገነባ ይሆናል ሰው ሀሳቡን ይኖራል አይደል የሚባለው ሀሳብ መንፈስ ነው በትውልዶች ሰንሰለት የሚጓዝ በቅርብ ባይሆን እንኳ ትውልዱ የሁለቱን አንድነት መርምሮ ሲደርስበት አንድ መሆናቸው የማይካድ ነው፡፡
የቦሌ አየር መንገድ ስያሜ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያስተሳረው የታሪክ አውድ ፈልጌ ፈልጌ አጣሁለት ይሄንን የሚያክል ግዙፍ አየር መንገድ በአፍሪቃም በዓለምም ተመስጋኝ የሆነ በቀን ብዙ ሺ መንገደኞችን እያደረሰ የሚመልስ የኢትዮጵያ እንብርት ላይ የተገነባ አየር መንገድ እስካሁን የኢትዮጵያን ግዙፍ ታሪክ ለምን አልተሸከመም ?
ሚኒሊክ አሁን ላለችው ኢትዮጵያ ዋልታ ፤መሰሶ፤ማገር መሆናቸው የማይካድ ነው በእርግጥ አፄ ሚኒሊክ አሁን ላለው የኢትዮጵያ ትውልድ ሁለት መልክ ያላቸው ገራሚ ንጉስ መሆናቸው ነው በአንደኛው ወገን አፄ ሚኒሊክን ጨካኝ አረመኔ አድርገው ሲስሏው ሌላኛው ወገን ደግሞ( እዚህ ወገን ውስጥ እኔም አለሁ) የኢትዮጵያ አንድነት አለት የዋህ የነፃታችን እስትንፋስ አድርገን እንስላቸዋለን ፡፡
እናም እንዲህ በሆኑት ኢትዮጵያዊ ታላቅ ንጉስ መላው ኢትዮጵያን በጀግንነታቸውና በአስተዳደር ብቃታቸው ሁሉንም በእኩል በማስተዳደር የእናትነት ክብር ደርበውላቸዋል ለመላው እንደ ሲምቦል እንዲታዩ ሆነዋል፡፡
አፂ ሚኒሊክ በአድዋ አውደ ወረጊያ ባሳዩት ጀግንነት መላው ኢትዮጵያዊ የነጭን የባርነት ቀንበር እንዳያጠልቅ በእራሱ እርሻ ላይ በራ መሬት ላይ ከናፍሮቹ ከጆሮዎቹ ጋር ታስረው የግፍን ቀንበር እንዳይገፉት አድርገዋል
ሚኒሊክ ተነስቶ ባያነሳ ጋሻ 
ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ
እንዲል ታዲያ ይሄንን የሚያክል ግዙፍ ታሪክ የተሸከመን ንጉስ እና ግዙፍ ታሪክ የተሸከመን ቦታ መላው ዓለም በሚመላለስበት የሀገሪቷ ዋና መዲና ላይ ሙሉ አየር መንገድን ብንሰይምላቸው ምን ይለናል ?
ያኔ ታላቁ አየር መንገዳችን ትልቁን የኢትዮጵያን ታሪክ ተሸክሞ ለኢትጵያውያኖችም ትልቅ አምባሳደር ይሆናል።
Filed in: Amharic