>

"..በቀጣዩ ሳምንት ስልጣኔን እለቃለሁ...." (ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስ)

ዘመድኩን በቀለ
የቀድሞዋ ተወዳጇ ጋዜጣ  የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በነበረው በተወዳጁ ጋዜጠኛ መስፍን ነጋሽ እና በጋዜጠኛ አርጋው አሽኔ አዘጋጅነት የሚቀርበው የዋዜማ ሬድዮ ከውስጥ የመረጃ ምንጮቼ አገኘሁት ያለውን የፓትሪያርክ አባ ማትያስን የስልጣን መልቀቅ ጥያቄ በሚከተለው መልኩ ዘግቦታል ።
የኦርቶዶክስ ቤተ-ክህነት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ እየተማከሩ ነው ።
ዋዜማ ራዲዮ ~ ብዙ ውጣ ውረዶችና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት የሚፈታተናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክህነት ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ለቅርብ ስዎቻቸው በመጪው ሳምንት “ስልጣኔን እለቃለሁ” ማለታቸውን የዋዜማ ምንጮች ነግረውናል።
ባለፉት አራት ቀናት ሲካሄድ በነበረውና ትናንት ሐሙስ በተጠናቀቀው 36ኛው የሰበካ መንፈሳዊ ጉባዔ ላይ ከሌሎች ጳጳሳትና ከቤተክህነት አስተዳደር ጋር በአደባባይ እስጥ አገባ ውስጥ ያሳለፉት አቡነ ማትያስ በጉባዔው ጣልቃ ስልጣናቸውን ለመልቀቅ እንደሚፈልጉ ለቅርብ ሰዎቻቸው ተናግረዋል።
በቤተክህነቱ አካባቢ ስልጣናቸውን የሚገዳደሩና የማይታዘዟቸው እየበዙ በመምጣታቸው ክፉኛ የተበሳጩት አቡነ ማቲያስ በመጪው ሰኞ በሚጀምረው የሲኖዶሱ ጉባዔ ላይ መልቀቂያ ማቅረብ እፈልጋለሁ ብለዋል።
የፓትርያርኩ እርምጃ ያሳሰበው መንግሥት ፓትርያርኩ ሀገሪቱ ያለችበትን አስቸጋሪ ሁኔታ አጢነው ስልጣን ከመልቀቅ ይልቅ በውይይት ችግሮችን እንዲፈቱ ከማክሰኞ ምሽት ጀምሮ አንድ ቡድን በመላክ እያግባባቸው ነው።
አቡነ ማትያስ የቤተክርስቲያኒቱ የወንጌል ማስፋፋትና ትምህርት አንድ አሀድ ከሆነው ማኀበረ ቅዱሳን ጋር የተካረረ ውዝግብ ውስጥ የቆዩ ሲሆን መንግሥት ማኅበሩን እንዲዘጋው እስከመጠየቅ ደርሰዋል። ማኀበሩ በቅርቡ የጀመረውን የቴሌቭዥን ስርጭትም ህገወጥ በመሆኑ ሊታገድ ይገባል ባይ ናቸው አቡነ ማትያስ።
ፓትርያርኩ ለአራት ቀናት በተካሄደው የመንፈሳዊ ሰበካ ጉባዔ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ተወካዮች እንዳይካፈሉ ትዕዛዝ ስጥተው ማኅበሩን እንዳይሳተፍ ማድረግ ቢችሉም የቤተክህነት አስተዳደርና ሌሎች ገዳማት የማኅበረ ቅዱሳንን ሚና የሚያጎላና የሚያወድስ ሪፖርት ማቅረባቸው አቡነ ማትያስን አስከፍቷቸዋል።
ጉባዔው ማኅበረ ቅዱሳንን ከማውገዝ ይልቅ ለቤተክርስቲያኒቷ አለኝታ የሆነና ድጋፍ ሊደረግለት የሚገባ መሆኑንም የተናገሩ አባቶች ነበሩ።
በአራቱ ቀን ጉባዔ ከአቡነ ፋኑኤል ጋር የከፋ የቃላት ልውውጥ ያደረጉት ፓትርያርኩ ብዙውን ጊዜ በዝምታና በማኩረፍ እንዳሳለፉ ከጉባዔው ተሳታፊዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የውዝግቡን መካረር ተከትሎ መንግሥት የጉባዔውን ሂደት በቅርብ ሲከታተል የቆየ ሲሆን በማጠቃለያ የአቋም መግለጫ ላይ የማኅበረ ቅዱሳን የቴሌቭዥን ስርጭት “ህገ-ወጥ” መሆኑን የሚገልፅ አንቀፅ ከጉባዔተኛው ስምምነት ውጪ እንዲጨመር መደረጉ ብዙዎችን አሳዝኗል። አንቀፁ የተጨመረው አቡነ ማትያስን “ተሰሚ” አድርጎ ለመሳል “በትዕዛዝ” የተካተተ እንደሆነ ከቃለጉባዔ መዝጋቢዎች ተሰምቷል።
አቡነ ማትያስ መንግስት በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እርምጃ አለመውሰዱ እንዳስኮረፋቸው ለመንግሥት ተወካዮች ከዚህ በፊት ተናግረዋል። በመንግሥት በኩል ግን ማኅበሩ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ፍላጎት አለመኖሩን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ያሰረዳሉ።
የአቡነ ማትያስ ዛቻ መንግሥትንም ሆነ ሲኖዶሱን ለመገፋፋት የተዘየደ መላ ሊሆን እንደሚችል ግምት ያስቀምጣሉ።
ሌሎች አስተያየት ስጪዎች ደግሞ ፓትርያርኩ ስሜታዊና “ለክብራቸው ሟች” ስለሆኑ ሊሰናበቱ ይችላሉ ሲሉ ያስረዳሉ። ሲል ዋዜማ ራዲዮ ዘገባውን አጠናቋል ።
እኔ ግን እላለሁ ። እሳቸው በአንድም በሌላም ምክንያት ሥልጣናቸውን ባይለቁ እንኳን ቅዱስ ሲኖዶሱ የሚለቃቸው አይመስለኝም ። ይኼ የእኔ ግምት ነው ። አከተመ ።
Filed in: Amharic