>
5:13 pm - Wednesday April 18, 3500

አብይን በዚህ መንገድ (ደረጀ ደስታ)

አብይን በዚህ መንገድ

1. የድጋፋችን ምንጭ ለአብይ ሀሳብ ካለን አክብሮት እንጂ ለሌሎች ካለን ጥላቻ እሚመነጭ ባይሆን
2.ለአብይ ያለን ክብር በአብይነታቸው እንጂ ለሌሎች ካለን ንቀት እሚቀዳ ባይሆን
3. ከወደድናቸው- እንኳን ያላሉትን- ያሉትንም ስህተት አርመን እምናወራ እንጂ አጣመን እምንናነገር ባንሆን
4. ለአብይ ወዳጅ እምናበዛ እንጂ ጠላት እምንገዛ ባንሆን
5. አብይን በአብይነታቸው እንጂ ሌላውን መደብደቢያ በትር ባናደርጋቸው
6. ሀሳቡን አብይ እንጂ ሰውየውን አብይ ብዙ ባናተኩርበት
7. አብይን እንቆጥብ በየቦታው“አብይ ድረስ!’ አንበል። እንዳልተደከመበት ገንዘብ የትም ከበተናቸው ቶሎ ያልቃሉ።
8. አብይ ተአምር እንድንሰራ ምክንያት ይሆኑናል እንጂ ራሳቸው ተአምር ሰሪ ወይም ተአምር አይደሉም።
9. እኛ ለሳቸው ህዝብ ከሆንላቸው አብይ መሪ ይሆናሉ። ህዝብ መሆን ካቃተን ግን ማንን ይመራሉ?
10. አብይ የሚደግፏቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን የሚቃወሟቸውም ሰዎች መሪ መሆናቸውን እንወቅ
11. ጸረ አብይ እና የአብይ ደጋፊዎች ስንደመር ኢትዮጵያውያን እንሆናለን
12. እማንወደውን ነገር ለማድረግ ነጻነት የሌለው መሪ – እምንወደውን ነገር ሊያደርግልን አይችልም
13. አብይ እማንስማማባቸው ሰው ሊሆኑ ይችላሉ እምንጣላባቸው ሰው ግን መሆን አይገባቸውም
14. አብይን አገኘናቸው እንጂ አልሠራናቸውም- ተስማሙን እንጂ አልመረጥናቸውም – ልዩነቱ ይግባን
15. ከአብይ ጋር መንገድ ለመጀመር ተነሳን እንጂ ገና አልደረስንም። ልንታረቅ አንጂ ገና አልታረቅንም። እርቅ ይሁን!
16. ባድመንና አሰብን ስናወራ ሰዎቹንና ኤርትራውያንን እናስብ። ከሆነልን የነገዎቹን – ካልሆነልንም የትናንቶቹን ኢትዮጵያውያንን አንርሳ – አብይ እሱን እያሉ ይሆን? ባይሉም እንዲሉ መግፋቱ ምን ይሆን ክፋቱ?
17. “መደገፍ” ሁለት ነው ቃሉ። እሳቸውን ደግፎ እና ተደግፎ ። ተደግፎ ሲሆን የዓላማው ቅንነት ጥሩ አይመጣም። ለሆድማ ከሆነ – የበላ ሊቀርበት ያልበላም ሊሞላበት እየሆነ ይሄድና – ሆድ ከአገር አይሰፋም!
18. “እንቁላሎችህን ሁሉ አንድ ቅርጫት ውስጥ አትክተት” እሚለው ተረት ላይ የተለያዩ ቅርጫቶችም ውስጥ የተለያዩ ዓይነት እንቁላሎችን ክተት እሚል ተረት ጨምርበት። አብይም ተሰባሪ ናቸው!
19. አብይ ደስ ካሉህ ዝምብለህ ተደሰትባቸው እንጂ ደስታህን አትመርምረው። ህይወት ወረት ናት። የጠላም ይጥላቸው ምን ቸገረህ ህይወት ምርጫ ናት። “አብይን የጠላ ሁሉ ይጠላ!” አትበል። ደስታህን ትተህ መጥላት ትጀምራለህ። ፖለቲካ ደግሞ ከምትወደውም ሰው ያጣላሃል። ጥላቻ ሀዘን ነው።
20 .ሰው ወይም ዜጋ ሁን እንጂ ከቡድን አትግባ። ቡድኖች አብይን ወይ የራሳቸው ብቻ ወይም የራሳቸው ያልሆነ ባዕድ አድርገው ይመለከታሉ። በቡድን እሚያስቡ ሰዎች ብዙ ጊዜ የትራጄዲ ምንጭ ናቸው። ከቡድን ሰንሰለት አምልጠው ለመሮጥ እሚሞክሩ ጥቂቶች ናቸው- አብይ ከእነኚህ አንዱ ከሆኑ አንተ አብረኻቸው እየሮጥክ ወይስ እያሳደድካቸው ይሆን? ራስህን ጠይቅ!

Filed in: Amharic