>
5:13 pm - Thursday April 19, 0503

ይድረስ ለኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መሪዎች (አፈንዲ ሙተቂ)

ለዓመታት የኦሮሞ ህዝብ የነፃነት ጥያቄን አንግባችሁ ስትታገሉ እና ስታታግሉ መኖራችሁ ይታወቃል። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የኦሮሞ ወጣቶችም በድርጅታችሁ ስር ታቅፈው ውድ ህይወታቸውን ለኦሮሞ ህዝብ ነፃነት ሰውተዋል። በኦሮሞ ህዝብ ላይ ሲደርስ የነበረውን ጭቆና፣ በደል፣ ግፍ፣ ግድያ፣ አፈና፣ እስራት፣ ዘረፋ በማጋለጥ አኩሪ ስራ ሰርታችኋል።
ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ ነቅቶ በተደራጀ ሁኔታ ወደ ትግሉ ጎራ እንዲቀላቀል ቀን ከሌሊት በፈጸማቸው ስራዎች ሁሉ እንኮራባቸዋለን። ግንባሩ ከምስረታ ዘመኑ ጀምሮ የኦሮሞ ህዝብን የነፃነት ጉዳይ ለድርድር ሳያቀርብ ከጨቋኞች ጋር ያደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ዘወትር ሲዘከር የሚኖር ነው።
ዛሬ በኦሮሚያም ሆነ በመላው ኢትዮጵያ እየነጋገረ የሚገኘው “ቄሮ” የተባለው ትኩስ የነፃነት ተፋላሚ ኃይል በዋናነት በኦነግ ስር ተደራጅተው ሲታገሉ የነበሩ የኦሮሞ ሰማእታትና አርበኞች በዘሩት ደም የበቀለ መሆኑም አጠያያቂ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ የትግል ታሪክ በሚወሳበት ጊዜ ሁሉ የኦነግን አስተዋጽኦ ሳያወሱ ማለፍ ፈፅሞ አይቻልም። በአጠቃላይ ፕሮፌሰር ሙሐመድ ሐሰን እና ፕሮፌሰር አሰፋ ጃለታ የሚጠቀሙበትን ዐረፍተ ነገር በመዋስ “ኦነግ የኦሮሞ ህዝብ ብሄርተኝነት አባት ነው” ብል ከሐቅ መራቅ አይሆንብኝም።
——
የኦሮሞ ህዝብም ሆነ መላው የኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ህዝቦች ለዘመናት ሲታገሉ የኖሩት ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህ፣ ለዲሞክራሲ እና ለሁለንተናዊ ብልፅግና ነው። ኦነግም በፖለቲካ ፕሮግራሙ ላይ ይህንኑ በግልፅ አስቀምጧል። ህዝቦቻችን ሲያደርጉት የኖሩት ትግል በየዘመናቱ የተለያዩ ውጤቶችን ማስገኘቱ ይታወቃል። በዘንድሮው ዓመት ደግሞ የህዝቦቻችን ትግል ከመጨረሻው ድል ደጃፍ ላይ ሊደርስ በተቃረበበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በተለይም ባለፉት 27 ዓመታት ህዝቦቻችንን እያባላ ሀገራችንን ለመበታተን ሲውተረተር የነበረው አፋኝ ስርዓት ተመንግሎ ግብአተ መሬቱ ከሚፈፀምበት ምዕራፍ ላይ ደርሰናል። የዚህ ምክንያቱ የለውጥ ፈር ቀዳጅ የሆኑና ለህዝባችንና ለሀገራችን የሚቆረቆሩ ወጣት መሪዎች ከገዥዎቹ መንደር ተምዘግዝገው ወጥተው ከህዝቡ ጋር መተቃቀፋቸው ነው።
 እነዚህ ህዝቡ ተስፋ የጣለባቸው ወጣት መሪዎቻችን ከገዥዎች መንደር መውጣታቸው ግርታን ሊፈጥር ይችላል። በተለይም አዳዲሶቹ መሪዎች በሸረኛነቱና በአስመሳይነቱ ከሚታወቀው ኢህአዴግ የተባለ ፓርቲ ውስጥ መውጣታቸው ብዙዎችን ከጥርጣሬ ላይ መጣሉ አልቀረም። የኦነግ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ዳውድ ኢብሳም በቅርቡ ከአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “አዲሶቹ መሪዎች ሆን ተብሎ በተሰራ የወያኔ ሴራ ወደ መሪነት የመጡና በወያኔ ተደርሶ የተዘጋጀን ቴአትር  የሚጫወቱ ገፀ ባሕሪዎች ናቸው” ሲሉ በግልጽ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አዳዲሶቹ መሪዎች ዓመታት በግንባሩ ውስጥ ሲካሄድ በነበረ የውስጠ ፓርቲ ትግል የተገኙ እንጂ በአንድ ጀንበር የተፈለፈሉ አለመሆናቸው ሊጤን ይገባል። በግንባሩ ውስጥ ለዓመታት ሲጋጋም የነበረ ትግል ነው አዲሶቹን መሪዎች የፈጠረው። ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል አዲሶቹን መሪዎች የሚያካትተው ቡድን በኢህአዴግ ውስጥ ሆኖ የአቶ ዐባይ ጸሐዬን የ”ልክ እናስገባቸዋለን” ድንፋታ እንዴት ሲገዳደረው እንደነበረ በቂ መረጃዎች አሉ።
 በሌላ በኩል ወያኔ ህወሓት ድራማ እጫወታለሁ ብሎ የደህንነቱንና ሌሎች ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን ለኦህዴድና ለብአዴን ያስረክባል ተብሎ አይታሰብም። እነዚህን ቁልፍ ተቋማት ሲያስረክብ ሞቱ እንደሚፋጠን ለማወቅ ነቢይ መሆንን አይጠይቅም።
በሶስተኛ ደረጃ በአንዲት ደሃ የአፍሪቃ ሀገር ላይ ጉብ ብሎ የሚጨፍረው ህወሓት ይቅርና ሞሳድ እና ሲአይኤ እንኳ ህዝቡን እናታልላለን በሚል ዘንድሮ ያየናቸውን ዓይነት የለውጥ እርምጃዎች ይወስዳሉ ተብሎ አይታሰብም።
ሲአይኤ እና ሞሳድ የሚጫወቷቸው ድራማዎች እንደ ጠላት ለሚያበጠለጥሉት ሀገር በድብቅ መሳሪያ መሸጥ፣ አንድ ያስቸገራቸውን ቡድን ለማጥፋት ሲፈልጉ ከርሱ ጋር የሚመሳሰል ርእዮተ ዓለም የሚሰብክ ሌላ ቡድን እየፈበረኩ በእጅ አዙር ውጊያ መግጠም፣ የማይወዱት ሰው የሀገር መሪ ሆኖ ሲመረጥ በመፈንቅለ መንግስት ማስወገድ የመሳሰሉት ናቸው።
 ወያኔ ደግሞ በጣም የተካነባቸው ድራማዎች ቦምብ እያጠመዱ “የኦነግ ስራ ነው፣ ግንቦት ሰባት ነው፣ የኤርትራ ሴራ ነው” እያሉ መለፈፍ፣ የማይፈልጉትን ሰው የሽብር ወሬ እየለቀቁበት ከሀገር ማባረር፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን በሁለት ጎራ እየከፈሉ ማባላት የመሳሰሉት ናቸው። ከዚህ ባሻገር ህልውናውን ሊያጠፋው ከጫፍ ላይ የደረሰውን የዘንድሮውን አስገራሚ የተሐድሶ ለውጥ እንደ ድራማ ጽፎት አዳዲሶቹን መሪዎች በገፀ ባሕሪነት የሚያሰማራበት አቅምና ብቃት የለውም።
በሌላ በኩል በጨቋኝነታቸውና በአፋኝነታቸው ጎልተው ከሚታወቁ ስመ ገናና ፓርቲዎች አብራክ እየወጡ አዲስ የለውጥና የተሐድሶ ጎዳና የፈነጠቁ ታላላቅ መሪዎች በሌሎች የዓለም ሀገራትም መታየታቸው መረሳት የለበትም። በዚህ ረገድ የሲቪየቱ ሚኻየል ጎርባቾቭ እና የደቡብ አፍሪቃው ፍሬድሬክ ዴክለርክ ቀዳሚ ምሳሌዎች ሆነው ሊጠቀሱ ይችላሉ።
—–
ኦሮሞዎችም ሆኑ መላው ኢትዮጵያዊያን በአሁኑ ወቅት በከባድ የለውጥ ጎዳና ውስጥ ይገኛሉ። ይህ በብዙዎች አዕምሮ ውስጥ ታላቅ ተስፋን የፈነጠቀው ተሐድሶና ለውጥ እንዲደናቀፍብን ፈጽሞ መፍቀድ የለብንም። በመሆኑም ነው በሀገር ውስጥ ካለው ህዝባችን ከ85% በላይ የሚሆነው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን መንበረ ስልጣኑን በቅርቡ የተረከቡት ክቡር ዶ/ር አቢይ አሕመድ ለለኮሱት የለውጥ ፋና ድጋፉን በመስጠት ላይ የሚገኘው። በሀገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ለለውጡ ድጋፋቸውን ሰጥተዋል።
 ከመንግስት ጋር በጦር ተዋግተን ለውጥ እናመጣለን የሚል አቋም ያላቸው ድርጅቶችም የህዝቡን ድምፅ የሚያከብሩ ከሆነ ተመሳሳይ እርምጃ መውሰድ ይኖርባቸዋል። በዚህ ረገድ ከኦነግ ጋር በቅርበት ሲሰራ የኖረው የ”አርበኞች ግንቦት ሰባት” ንቅናቄ የወሰደው አቋም በእጅጉ የሚደነቅ ነው። በትጥቅ ትግል ላይ የሚገኘው ኦነግም ተመሳሳይ እርምጃ ወስዶ ከአዲሱ መንግስት ጋር በቀጥታ መነጋገር እንጂምር ህዝቡ እየጠየቀ ነው።
ኦነግ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የለውጥ እርምጃ መደገፍ አለበት የምንለው በብዙ ምክንያቶች ነው። ዋነኛው ምክንያታችን ግን ባለፉት 27 ዓመታት በህዝቡ ጫንቃ ላይ እንደ መዥገር ተጣብቀው ደሙን ሲመጡ ከቆዩ በኋላ በለውጡ ባቡር እየተገፈተሩ የተወረወሩት የወያኔ ዲታዎች የተለያዩ አሻጥሮችን እየሰሩ በኦነግ በማሳበብ የአዲሱን መንግስት እድሜ ለማሳጠር እየጣሩ መሆናቸው የሚታወቅ መሆኑ ነው። ስለዚህ ኦነግ ስሙንና ታሪኩን ለመጠበቅ የሚሻ ከሆነ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ላቀረቡለት የሰላምና የመግባባት ጥሪ አፋጣኝ ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል እንላለን።
 ኦነግ ይህንን ማድረጉ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የነበረውን ክብርና ዝና ለመጠበቅ ይረዳዋል። በሌላ ጎኑ ደግሞ በኦሮሞ ታጋዮችና በሌሎች ኢትዮጵያዊያን የነፃነት ተፋላሚዎች ዘንድ የበለጠ መግባባትንና አንድነትን በመፍጠር ድሉን በአጭር ጊዜ ለማጣጣም ያስችለናል ብለን እናምናለን። ስለሆነም የኦነግ መሪዎች በመሳሪያ ኃይል የሚያደርጉትን ትግል ለጊዜው አቁመው ከአዲሱ መንግስት ጋር መነጋገር እንዲጀምሩ አበክረን እንጠይቃለን።
ድል ለሰፊው ህዝብ!!
Filed in: Amharic