>

በአንድ ቤተሰብ ላይ የተፈፀመ "መንግስታዊ" ሽብር (ጌታቸው ሺፈራው)

ዘር ጭፍጨፋ ተመሳሳይ ቋንቋ ወይ ማንነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው።  ሽብር በአንድና ከዛ በላይ ባሉ ግለሰቦች ላይ የሚፈፀም ወንጀል ነው። በኢህአዴግ ዘመን በ20 የአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ  ሽብር ተፈፅሟል። በማንነት በሚመሳሰሉት ብቻ ሳይሆን በአንድ ቤተሰብ አባላት ላይ ይህ ጭካኔ ተፈፅሟል።
ነጋ ደለለኝ ከ1998 ዓም ጀምሮ ከ”መንግስት” ጦር ጋር ተዋግቷል። ብዙ የሰራዊት አባላትን መግደሉ ይነገራል። የመንግስት ሰዎችን ላይ ቅጣትና ግድያ መፈፀሙም ይነገራል። ይህን ወጣት የ”የመንግስት” ጦር ሲፈልገው ትርፉ ኪሳራ ሆነ።  ነጋና ጓደኞቹ ጋር በሚደረግ ጦርነት ሙትና ቁስል የሚሆነው የ”መንግስት” ጦር ትኩረቱን ወደ ቤተሰብ አደረገ።  ቤተሰቡን በሙሉ በመፍጀት፣ ሽብር በመፈፀም ነጋ ደለለኝን ለመበቀል እቅድ አወጣ። በጀት አስመደበ።
 ህዳር 6/2006 ዓም  “በመንግስት” በጀት የሚተዳደር ጦር ቋራ ወረዳ ፋርሻ ቀበሌ  አይማ ማዶ ጎጥ  ከጠዋቱ አስራ ሁለት ሰዓት አካባቢ የነጋ ቤተሰቦችን ቤት ከበበ።  ነጋ ደሌን የሚፈራው ልዩ ሀይልና መከላከያ ቤተሰቦቹ  ላይ በመትረየስ ሩምታ ተኩስ ከፈተ። በዚህ ጭካኔም:_
1) ደለለኝ መስፍን (እድሜ 56፣ የነጋ አባት)
2) ሙሉ አበበ ( እድሜ 40፣ የነጋ እናት)
3)  ጋሻው ደለለኝ(እድሜ 25 ፣ ወንድም)
4) ደሳለኝ ደለለኝ (እድሜ 22፣ ወንድም)
5) መሰንበት ደለለኝ(እድሜ 19፣ ወንድም)
6) እባበይ ደለለኝ(እድሜ 15፣ ወንድም)
7) ይስማው ደለለኝ( እድሜ 8፣ ወንድም)
8/ ምንይሉ ደለለኝ  (እድሜ 12፣ ወንድም)
የ”መንግስት ጦር” የተቀመጡት ቤት ላይ በከፈተው ተኩስ ተጨፈጨፉ። የነጋ አባት አቶ ደለለኝ መስፍን ቆስለው የነበር ቢሆንም በመንግስት ጦር “አንተ የክፉ አባት” እየተባሉ ተወቅሰው በጥይት ተደብድበው ተገደሉ። እንደደመኛ ወቅሰው ጨረሷቸው። አንድ መንደር ውስጥ ይኖር የነበረ የቤተሰብ አባልን ጨርሰ፣ ሀብት ንብረቱን ተወርሶ ተመልሰዋል።
ቋራ ላይ በነጋ ቤተሰቦች የተደረገው መንግስታዊ ሽብር የመጀመርያ አልነበረም። ጥቅምት 12/2006 ዓም አብደረግ የሚባል ቦታ ሰሊጥ ሰብላቸውን እየሰበሰቡ የእርሻ ካምፓቸው ውስጥ የነበሩ የነጋ አጎቶች በተመሳሳይ የ”መንግስት” ጦር በመትረየስ ፈጅቷቸዋል። ” ነጋን ታስገባላችሁ፣ ታበሉታላችሁ፣ ስንቅ ትቋጥሩለታላችሁ” ተብለው የሽብር እርምጃ የተወሰደባቸው የነጋ አጎቶች:_
1) ማሩ መስፍን
2) ንጉሴ መስፍን
4) አስማረ መስፍን
5) ጋሻው መስፍን
6) ውበት መስፍን
7) ሀብታሙ መስፍን ናቸው።
የነጋ ደለለኝ አባት አቶ ደለለኝ መስፍን የ7 ወንድሞቻቸውን ሀዘን ሳይጨርሱ ነበር ከባለቤታቸውና ከልጃቸው ጋር ተመሳሳይ ኢህአዴጋዊ  ሽብር የተፈፀመባቸው።
በነጋ አባት፣ እናት፣ ወንድሞችና አጎቶች ይህን የመሰለ ጭካኔ ከመፈፀሙ በፊት “ነጋን አምጡ” እየተባሉ በርካቶች የሽብር ሰለባዎች ሆነዋል። ለምሳሌ በ2004 ዓም
1) ንጉሴ ሀጎስ ፈረደ
2) ሰጠኝ ሀጎስ ፈረደ
3) አወቀ ሀጎስ ፈረደን የ”መንግስት”ጦር ከእያሉበት አፍኖ “ነጋ ያለበትን አሳዩን፣ ምሩ”  እያለ በአርማጭሆን ጫካ ሲያዞራቸው ከሰነበተ በኋላ ነጋ ያለበትን ማወቅ ባለመቻላቸው አባዬ እየሱስ ልዩ መጠርያው ማላ የተባለ ቦታ ላይ ተረሽነዋል።  ሽብር ተገፅሞባቸዋል።
በተጨማሪም  አርማጭሆ ላስታ ወረዳ 1) እንየው ተረፈ 2) ደረጀ ተፈራ ምሽት ላይ ራት እየበሉ በነበሩበት ወቅት በ”መንግስት”ጦር ሩምታ ተመሳሳይ መንግስታዊ ሽብር ተፈፅሞባቸዋል። የእንየው ተረፈ ባለቤት በዚሁ ወቅት ቆስላለች።
ከ20 በላይ  የነጋ ደለለኝ ቤተሰቦች ነጋን ጋር ገጥሞ ሞትና ቁስል በሚሆን የ”መንግስት” ጦር በቀል ተፈፅሞባቸዋል። መንግስታዊ ሽብር!  ነጋ ደለለኝ በአሁኑ ወቅት አንድም የቅርብ ቤተሰብ የለውም።  ደርግ ይህን ያህል ቤተሰብ ላይ “ቀይ ሽብር” ብሎ ጭፍጨፋ ስለመፈፀሙ አልሰማሁም።
ትህነግ/ኢህአዴግ ግን ለአንድ ነጋ የሚባል አርበኛ የ8 አመት ህፃን ልጅ፣ የ56 አመት አባት፣ የ40 አመት እናቱን ጨምሮ 20 ቤተሰቡን ጨፍጭፏል። ሽብር ፈፅሟል። ማሳ እየሰበሰቡ የነበሩ አጎቶቹን  እንዲሁም እጃቸውን የኋሊት አስሮ “ነጋ ያለበትን አሳዩኝ” እያለ ተራራ ለተራራ ሲያዞራቸው የከረመውን የአጎቱን ልጆች ረሽኖ አስከሬናቸውን ለአውሬና አሞራ ሰጥቶ ተመልሷል።
በአንድ ማህበሰብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ዘር ማጥፋት ይባላል። ትህነግ/ኢህአዴግ ደግሞ ለማህበረሰብ መሰረት የሆነውን አንድ ቤተሰብ ፈጅቷል። ነጋ ደሌ ቤተሰቦቹን የጨረሰው የመንግስት ጦር እጅ ወድቆ በእስር ላይ ቆይቷል። ሙሉ ቤተሰቡ ላይ ምን አልባትም በየትኛውም አለም ያልተፈፀመ መንግስታዊ የሽብር ወንጀል የፈፀመ “መንግስት”   አሸባሪ ነህ ብሎ ከስሶ ፈርዶበታል። ሰኔ 8/2010 ዓም ደግሞ በ”ሽብር” ተከሰው የተፈረደባቸው እስረኞች ሲፈቱ  መንግስት ነኝ የሚል አካል ቤተሰብ አልባ ያደረገው ነጋም  ከዝዋይ ተፈትቷል። ነጋ ከእስር ቤት ይውጣ እንጅ ህይወቱ አደጋ ውስጥ ነው።
ትናንት ሰኔ 10/2010 ዓም ነጋን ጨምሮ ሌሎች እስረኞች ባረፉበት ሆቴል ፀጉረ ልውጥ ሰዎች አብረው እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ከአርማጭሆ የመጣና  መሳርያ (ሽጉጥ) የታጠቀ እንደነበር መረጃዎች አሉ። ይህ ሰው ነጋን ፈልጎ እንደመጣም ተገምቷል። በገንዘብ እነ ጎቤን ያስገደለው መንግስት ነጋ ደለለኝንም ለማስገደል ጥረት እያደረገ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ከደለለኝ መስፍን ዘር አንድም ሰው መትረፍ የለበትም ተብሎ ይሆናል!
(ፎቶው በደለለኝ መስፍን ቤተሰብ ላይ በተፈፀመ ሽብር ብቻውን የቀረው ነጋ ደለለኝ ነው)
Filed in: Amharic