>

የለውጥ ናፋቂና ሀገር ወዳድ የሆኑ በሙሉ ቅዳሜ ዕለት ወደ መስቀል አደባባይ ይተማሉ! (ስዩም ተሾመ)

አንዳንድ ወዳጆቼ በውስጥ መስመር “ህወሓቶች የጠሩትን ሰልፍ ሰርዘዋል! ዶ/ር አብይም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው በተግባር አረጋግጠዋል! ስለዚህ ቅዳሜ ዕለት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ምን ያስፈልጋል? ለምን አይሰረዝም?” የሚል መልዕክት ይልኩልኛል። በእርግጥ ጥያቄው መጠየቁ አግባብ ነው። ይሁን እንጂ ጥያቄው ስለ ሰላማዊ ሰልፉ ካለን የተሳሳተ ግንዛቤ የመነጨ ነው። በቀጣዩ ቅዳሜ ሰኔ 16/2010 ዓ.ም በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ የሚካሄደው ዶ/ር አብይን በተናጠል ለማድነቅ ወይም ለመደገፍ አይደለም። ከዚያ ይልቅ የሰላማዊ ሰልፉ መሰረታዊ ምክንያት በተለይ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ከሞላ ጎደል ሁላችንም በወታደራዊ ጉልበትና አስገዳጅነት የተነፈግነው ዴሞክራሲያዊ መብትን በተግባር ለማረጋገጥ ነው።

ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጋ የመሰብሰብ፥ የመደራጀትና ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ቅሬታና አቤቱታውን፣ እንዲሁም ድጋፍና ተቃውሞውን በነፃነት የመግለፅ መብት አለው። በመሆኑም ቅዳሜ ዕለት በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ የምናደርገው፤ አንደኛ፡- የመሰብሰብና ሰለማዊ ሰልፍ የማድረግ መብታችንን በተግባር ለማረጋገጥ ነው፣ ሁለተኛ፡- በዚህ አጋጣሚ የራሳችንን ሃሳብና አመለካከት በነፃነት ለመግለፅ ነው። በዚህ መሰረት በሰላማዊ ሰልፉ አማካኝነት በሕገ-መንግስቱ የተደነገጉ ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን በተግባር እናረጋግጣለን።

ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችንን በማረጋገጡ ሂደት ደግሞ በሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሃሳብና አስተያየት እንሰጣለን። እንደ ማንኛውም ዜጋ ለውጥና መሻሻልን በግልፅ እናበረታታለን፣ በአንፃሩ ፀረ-ለውጥ የሆነ አቋምና እንቅስቃሴን በይፋ እናወግዛለን። ስለዚህ በቅዳሜው ሰልፍ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ከማረጋገጥ በተጨማሪ፣ አንደኛ፡- ለለውጥና መሻሻል ጥሩ ጅምሮችን በማበረታታት ድጋፋችንን እንገልፃለን፣ ሁለተኛ፡- ጥሩ ጅምሮችን የሚያደናቅፉ እኩይ ተግባራትን በማውገዝ የዜግነት ግዴታችንን እንወጣለን።

ቀጣይ ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ፣ ሌላው ቢቀር ዛሬ ጠ/ሚ አብይ አህመድ በፓርላማ ያደረጉት ንግግር ብቻ በቂ ነው። አብዛኞቻች እንደ ተከታተላችሁት ዕለት ዶ/ር አብይ የተናገሩት ነገር እንደ ሀገር፥ ሕዝብ፥ ቡድንና ግለሰብ በእያንዳንዳችን ሕይወት ውስጥ ተጨባጭ የሆነ ለውጥና መሻሻል ሊያመጣ የሚችል ነው። ጠ/ሚኒስትሩ በንግግራቸው ከፖለቲካ ፍላጎትና ጥቅም ይልቅ የሕዝብን ጥያቄና የሀገርን ጥቅም አስቀድመዋል።

ለግማሽ ክፍለ ዘመን በግነትና ውሸት የተሞላ ሪፖርትና ንግግር በተደረገበት ፓርላማ ቀርበው በእውነትና ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ገለፃና ንግግር አድርገዋል። በዚህም የፖለቲካ ትርጉምና ፋይዳ የመንግስትን ስልጣን ማስከበር ሳይሆን የዜጎችን መብትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሆነ በግልፅ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ይህን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ወገኖች መኖራቸውን በግልፅ ተናግረዋል። ስለዚህ በቀጣዩ ቅዳሜ መስቀል አደባባይ በመውጣት የዜጎችን መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንደግፋለን።

ጠ/ሚ አብይን ጨምሮ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ በአመራርነት ሆነ በድጋፍ ሰጪነት ረገድ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ያሉ ሰዎችን በይፋ እናመሰግናለን። በተቃራኒው ይህን የለውጥ እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን በጥብቅ እንቃወማለን። ሀገርና ሕዝብን የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን በጥብቅ እንኮንናለን። እንዲህ ያሉ ወገኖች በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት ሆነ ተፈላጊነት እንደሌላቸው በተግባር እናረጋግጣለን። በዚህ መሰረት ቅዳሜ ዕለት የሚካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ መሰረዝ ወይም ማቋረጥ የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ሕዝባዊ መሰረት እንደሌለው ለማሳየት ጥረት ለሚያደርጉ ወገኖች ድጋፍ እንደ መስጠት ይቆጠራል። በመሆኑም ፀረ-ለውጥ አቋም ያላቸው ወገኖች የለውጡን እንቅስቃሴ እንዲያደናቅፉ ምቹ ሁኔታ ይፈጥርላቸዋል።

በአጠቃላይ ቅዳሜ ዕለት በመስቀል አደባባይ በሚካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የሚገኙት የኢህአዴግ መንግስት ደጋፊዎች ወይም የጠ/ሚ አብይ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆኑ ለውጥ ናፋቂ እና ሀገር ወዳድ የሆኑ ዜጎች ናቸው። በመስቀል አደባባይ የምንገናኘው ድጋፍና ተቃውሞ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለማስከበርና የዜግነት ግዴታችንን ለመወጣት ነው። ስለዚህ የለውጥ ናፋቂና ሀገር ወዳድ የሆኑ ዜጎች በሙሉ ቅዳሜ ዕለት በመስቀል አደባባይ ይገኛሉ!

Seyoum Teshome | June 18, 2018
Filed in: Amharic