>

የኢትዮጵያ ችግር ከኢህአዲግ አቅም በላይ ነው!!! (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

የጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ የዛሬው የፓርላማ ውሎ በአብዛኛው በድርጅታቸው ውስጥ ያለውን ሽኩቻ በግልፅ ያሳየ ነው። በተለይም ህወሃት ሰሞኑን ለሰጠው መግለጫ መልስና ማብራሪያ ለመስጠት የተዘጋጀ መድረክ ይመስላል። ከጠቅላይ ሚንስትሩ ንግግር ውስጥ በመልካም የሚወሰደው በህዝብ መካከል የሚፈጠር ጥላቻ ፣ቂምና ቁርሾ ለሃገር ህልውና አደገኛ ስለሆኑ በፍቅርና በወንድማማችነት እንዲተኩ በጠንካራና በሃላፊነት ስሜት መምከራቸው ነው።
ይሁን እንጅ ተጨባጭ ለሆኑ ለኢትዮጵያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮች ለምሳሌ ሙስናን መንግስታቸው እንዴት እንደሚዋጋው፣ ስራ አጥነትን ፣የኑሮ ውድነትን ፣የወጭና የገቢ ንግድ መዛባትን፣ በክልሎችና በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶችን እንዴት እንደሚፈቱዋቸው የመንግስታቸውን የአጭር ጊዜ እቅድ አላሳዩም።
የአልጀርሱን ስምምነትና በመንግስት እጅ የነበሩ ድርጅቶችን ወደ ግል ማዛወርን በተመለከተ ድርጅታቸው በግማሽ ቀን ተቻኩሎ እንዴት እንደወሰነ ሲጠየቁ እሳቸው ዛሬ አፈፃፀሙን በተመለከተ እስከ ሁለት አመት ጊዜ እንደሚወስድ፣ ስለ ኤርትራ የተወሰነውም የሰላም ጥሪ እንጅ መንግስት ድሮ ከወሰናቸው ውሳኔዎች የተለየ እንዳልሆነ ገልፀዋል። የተወሰነው ውሳኔ ዛሬ እሳቸው በሰጡት ማብራሪያ መሰረተ ከሆነ በጥድፊያ እና በችኮላ ውስኖ ለምን በሚዲያ ማስተጋባት አስፈለገ የሚል ጥያቄ ያስነሳል።
የዛሬው የጠ/ሚሩ ንግግር ስለ ዝርዝርና ተጨባጭ ጉዳይ ሲጠየቁ አጠቃላይና የመርህ ትንተና በመስጠት እንዲሁም ስለ ወቅታዊና ፋታ የማይሰጡ የመንግስታቸው ችግሮች ሲጠየቁ በቲዮሪ የተደገፉ የረጅም ጊዜ ህልማቸውን (ስለ ምስራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ደጋግመው የተናገሩትን ልብ ይሉዋል።) በመግለፅ የተሞላ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። ኢትዮጵያ ለምትገኝበት ውስብስብ የፖለቲካ ችግሮች መንግስታቸው ያለውን ተጨባጭ መፍትሔ አላሳዩም። ይልቁንም ንግግራቸው የሚመሩት ግንባርና መንግስት በከባድ የውስጥ ሽኩቻ ውስጥ መውደቁን ያሳያል።
በአጠቃላይ የጠ/ሚሩ የዛሬው ውሎ የኢትዮጵያ ችግር ከኢህአዲግ አቅም በላይ ነው የሚለውን አቋሜን አጠናክሮልኛል።
Filed in: Amharic