>

እኔም ስለ ቅዳሜው ሰልፍ…(በፍቃዱ ዘ ሀይሉ)

እኔም ስለ ቅዳሜው ሰልፍ…

በፍቃዱ ዘ ሀይሉ
፩) ዋልታ ቲቪ፤ “መንግሥት እያደረገ ያለውን ለውጥ በመደገፍ ሰልፍ ይደረጋል። አስተባባሪዎቹ ‘ጥሩ ሲሠራ መንግሥትን የማመስገን ልማድ መበረታታት አለበት’ ብለዋል።”  ማን ነው ግን ይሔን ያለው? አዘጋጆቹ አንዳቸውም ‘መንግሥት’ ሲሉ አልሰማሁም።
፪) በነገራችን ላይ ሰልፉ ‘ዶ/ር ዐብይን ለማመስገን ነው’ የተባለውን ያክል፣ [ባይነገርም] ‘ትሕነግን ለማውገዝም’ ነው። መወገዝ ሲያንሳት ነው። ትሕነግ ከወደቀች በኋላ እንኳ ‘ለምን አላሰርንም፣ ለምን አላሳደድንም?’ እያሉ የሚቆጩ ሰዎች ስብስብ ነች።
፫) አስተያየት ሰጪዎች ‘ጠ/ሚ ዐብይን ብቻ ማመስገን ስህተት ነው። በአንደኛ ደረጃ ቄሮ እና ሌሎች ወጣቶች፣ ቀጥሎ ኦሕዴድ እና በኢሕአዴግ ውስጥ የተለወጡ ሰዎች ናቸው’ በሚሉት 100%  እስማማለሁ። አንድ ሰው ብቻ ማመስገን ወደ ተዐብዮ ያመራል።
፬) በሌላ በኩል ‘ከዐብይ ጎን እቆማለሁ በሚለው ፈንታ፣ «ከሪፎርሙ ጎን እቆማለሁ» ነው መባል ያለበት’ የሚሉትም በጣም ትክክል ነው። አደባባይ ወጥቶ ተጨማሪ ግፊት ማድረግ፣ የለውጥ ፈላጊዎቹን የሚገዳደሯቸውን ከማስደንገጥ ዕኩል አስፈላጊ ነው።
፭) ከአዘጋጆቹ እንደሰማሁት ‘ለዴሞክራሲ ሪፎርም ከጠ/ሚኒስትር ዐብይ ጎን እቆማለሁ’ (የሚል ወይም የሚመስል) መሪ ቃል እንደሚጠቀሙ ነግረውኝ ነበር። ግን ለምንድን ነው በደንብ የማያስተዋውቁት?
፮) እኔና ጓደኞቼ የሚከተለውን መፈክር ይዘን ነው የምንወጣው። ዓላማችን የሪፎርም ተስፋ መኖሩን እና የሚቃወሙትን የምንቃወም፣ የሚደግፉትን የምንደግፍ መሆኑን መግለጽ ብቻ ሳይሆን፣ ለሪፎርም አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱን ማስታወስ ነው። (እነዚህ ዐዋጆች ለምን መሻሻል እንዳለባቸው፣ ማብራሪያ ገና አቀርባለሁ።)
Filed in: Amharic