>

ትህነግ እንደምን ኮሰመነች (ጌታነህ ልጅ አለም)

 
ትህነግ እንደምን ኮሰመነች
(What did really happened)
ጌታነህ ልጅ አለም 
መጀመሪያ ጠጠር ያለባትን የአማራ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውንና ሌሎች እምቢተኛ የአማራ ክልል አመራሮችን ኮርኩማ ልታባርር መኮረች። ከሸፈ!
~
የህዝብ ችግር ግልጥ ብሎ የታያቸው የግምባሩ አባል ድርጅቶች አመራሮች (በተለይ የብአዴንና ኦህዴድ) የህዝብ ጥያቄዎችን ማስተላለፍና ለፍትዊ የሀብት ክፍፍል መወትወት ቀጠሉ፣
~
እንደመፍትሔም ከትግራይ ክልል በሚተርፈው በጀት “የኢኮኖሚ አብዮት” በሚል እንቅስቃሴ ጥያቄዎች በሚበረቱባቸው ሁለቱ ክልሎች ሽሮ ፈሰስ አስፋልት፣ ኮብል ስቶን፣ መንገድ ጥርጊያ፣ አቧራ ማብነን(ማለዘብ)፣ የግንባታ መሰረት ድንጋይ ማስቀመጥ እና ወዘተ የይስሙላ የልማት ተግባራትን በየአካባቢው ለታይታ ለማስኬድ ተውተረተሩ፣ ህዝቡ ግን ነቄ በሎ ስለነበር ከቁብ አልቆጥረው አለ፣
~
የተይያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥያቄቸውን አበርትተው ቀጠሉ፣ መፍትሔ መስጠት ግዴታ መሆኑን የተረዱ የግምባሩ ውስን አመራሮች ውግንናቸውን ሙሉ ለሙሉ ከህዝቡ ጋር አደረጉ፣ ህዝቡ ይሄን ተረድቶ እኒህ ሰዎች የበለጠ ህዝባዊ እንዲሆኑ የሚያስችል የትግል ስልት ቀየሰ፣ ህዝባዊ የመሆን ዕድል ያላቸውን አመራሮች በማለፍ ዋናውን የጥፋት አስኳል ለይቶ ለማፍረስ የሚያስችል የቆረጣ ስልት!
~
ከዛም ወቅታዊና ትክክለኛ የህዝብ ጥያቄዎችን የሚያራምዱ አመራሮች በህዝብ ደጀንነት መተማማን ቀጠሉ፣ የውስጥ ትግል ተጠናከረ፣ የህዝብ ጥያቄዎች የዲሞክራሲ ማዕከላዊነትን የሽፋን ወሬ ከንቱ በማድረግ በቀጥታ በድርጅቱ ውስጥ መንሸራሸር ቀጠሉ፣ ህውሃት በዚህ ሁሉ ሂደት ጥያቄ በሚያራምዱት ሁሉ ጥርሷን እንደነከሰች ቀጠለች።
~
ሂደቱን በሚገባ እያጤነ የመጣው ህዝብ የሆነ የይቻላል መንፈስ በይበልጥ አዳባረ፣ ለውጥን ብቸኛ መፍትሔ እንደሆነ የተረዱ አመራሮችም ጥያቄዎችን መፍታት አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ተረዱ፣ በቁርጠኝነትም የለውጥ ፍላጎቶቹን ማራመድ ቀጠሉ፣
~
በስተመጨረሻ በህዝብ፣ በኢህአዴግ ውስጥ ባሉ የለውጥ ኃይሎች እና በተቃውሚዎች መካከል እየተፈጠረ የመጣው የኃይል አሰላልፍ ያብከነከናት ህውሃት ዕድሉን ለማጨናገፍና የዝርፊያ ሰንሰለቷን ለመታደግ ሞከረች፣ አልተሳካም!
~
የኦህዴድና የብአዴን የአመራር አደጃጅቶች እና የግምባሩ ዋነኛው የአመራር አወቃቅር ከህውሃት ፍላጎት በተቃራኒ ተደራጀ፣ እንደለመደችው ተፅዕኖ ማሳደር ሳትችል ቀረች፣
~
ይህ ሁሉ ያላማራት ትህነግ በደህንነቱ ያላትን ሰንኮፍ የጥቅም ተጋሪ የአባል ድርጅት አመርሮችን በመጠቀም ስርዓት አልበኝትነን በማስፈን ወደ ፊት የመጣውን ህዝባዊ አመራር ‘አልቻልህም’ በሚል ሰበብ ቀስ አድርጎ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግና ብሎም ወደ ወህኒ ለመወርወር ሙከራ አደረገች፣ ይሄም ከንቱ ሆነ!
~
ከዛም ህዝባዊ ግን ደግሞ ፀረ-ህውሃት የሆኑ ሃሳቦች፣ ቃሎችና ተግባራት በህዝብ ተወካዮች ምክር-ቤት ስምተን ተደመመን፣ ላለፉት 27 ዓመታት የነበረው የህውሃት መራሹ መንግስት ሰይጣናዊ ባህይሪ በግልፅ ተወገዘ፣ አሸባሪ እንደነበርም ታመነ!
~
በዚህ ሰዓት ህዝብ ለውጥ ቀልባሽ የቀድሞ አመራር አባላትን(የትህነግን በዋናነት) እና የጥቅም ተጋሪ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተፅዕኖ በመግታት መሰረተ ሰፊ ለውጥ እንዲቀጥል ለህዝብ የለውጥ ፍላጎት አወንታዊ ምላሽ ለሰጡ አመራሮች አስተማማኝ ድጋፍ እንለዳው ለማሳየት የድጋፍ ሰልፍ በመላ ሀገሪቱ ለማካሄድ እያሟሟቀ ይገኛል።
Filed in: Amharic