>

የአፍሪካ ጠኔ - የሰው ጠኔ ነው፤ የኢትዮጵያም እንደዚያው፤ ጠኔያችን የሌላ ሣይሆን - የሰው ነው!  (አሰፋ ሀይሉ)

— “ሀገር የሚለውጠው ሰው ነው፡፡ ሰው ነው መድሀኒታችን፡፡ ሰው ነው መጥፊያችን፡፡ መድሃኒታችንን ሰውን እንመልከት፡፡ እንደ ሰው እንብዛ፡፡ እናስብ፡፡ እንተሳሰብ፡፡”
አሜሪካኖች እንደ ሀገር ታሪካቸውን ‹‹ሀ›› ብለው ሊጀምሩ… ህገመንግሥታቸውን ያፀደቁት ልክ በትናንትናዋ ዕለት፣ እ.ኤ.አ. በጁን 21/1788 ዓ.ም. ነው፡፡ የዛሬ 230 ዓመት ማለት ነው፡፡ የሚገርመን ግን — በአራት ቅጾች ተዘጋጅቶ በአውሮፓ ምድር የተሠራጨውና — ስለ ታላቋ የኢትዮጵያ ኢምፓየር ታሪክ የሚናገረው ይህ መጽሐፍ — የታተመው መቼ ነው? ብለን ስንጠይቅ ነው፡፡ ይህ ስለታላቋ ኢትዮጵያ የሚዘረዝር መጽሐፍ በእንግሊዝ ታትሞ ለዓለም የተሠራጨው — አሜሪካኖች እንደ ሀገር ተቋቁመው ህገመንግሥታቸውን ከማፅደቃቸው ከ104 ዓመታት በፊት — ማለትም እ.ኤ.አ. በ1684 ዓ.ም. ነበር፡፡ የዛሬ 334 ዓመት እንደማለት፡፡ ይገርማል በእውነት!
ሉዓላዊት ሀገር ኢትዮጵያ እንዲህ… ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው… እነ አሜሪካ ሊመሠረቱ ቀርቶ ገና ሳይታሰቡ… ታላቅ ሉዓላዊት ሀገር የነበረች… የዘመናት ታሪክ ባለቤት… ገናና አፍሪካዊት ሀገር ነች፡፡ ወይም ነበረች፡፡ ይገርማል ይሄ! ግን መግረም ብቻ አይደለም!! በግርምቱ ውስጥ ቁጭትም አለበት፡፡ ከእኛ በኋላ ‹‹ሀ›› ብለው ተሰባስበው በባዶ እጃቸው ሀገርን ያህል ነገር የመመሥረቱን ከባድ ፈተና የተያያዙት የዓለም ሀገራት ከኢትዮጵያ ኋላ ተነስተው… በኢኮኖሚ ብልጽግና፣ በኑሮ ደረጃ፣ በቴክኖሎጂ ጥበብ፣ በዲሞክራሲ፣ በጉልበት፣ በስንቱ ነገር እንዲህ እኛን ሊያስከነዱን… እና ከዓለም አውራ ከሆንንበት ከሩጫችን በቀር … እንዲህ ስንቱ ነገራችን… እንዲህ  የዓለም ጭራ ሆኖ የቀረብን ግን.. ምን የሰው መቅሰፍት ቢወርድብን ይሆን??? የሚለው ቁጭት ያንገበግባል፡፡
ለነገሩ ኢትዮጵያ ብቻም አይደለች እኮ፡፡ አፍሪካችን ራሷስ… እንዲያ ከዓለም ቀድማ እስከዛሬ ምስጢራቸው ያልተፈታውን ታላላቅ ፒራሚዶች ያነፀች አህጉር፣ እስከዛሬም እንዴት እንደቆሙ የማይታወቁትን የአክሱም ሀውልቶች ያቆመች አህጉር፣ በድንቅ ጥበብ ከመሬት መስቀል ፈልፍላ ታላቅ ምድራዊ ኪነ-ህንጻን በላሊበላ ለዓለም ያሳየች አህጉር፣ እንዴ! ግን ምን ነክቷት ይሆን.. አፍሪካችን ራሷስ.. እንዲህ የግድየለሾች፣ የአምባገነኖችና የስደተኞች አህጉር ልትሆን የበቃችው???!! ስለምን ከእኛ አፍሪካውያን፣ ከእኛ ኢትዮጵያውያን.. በስንት ሺኅ ዓመታት ዘግይተው… ሀገር የመሠረቱ ህዝቦች እንዲህ የእድገትንና የብልጽግናን ጫፍ ሲነኩ… እኛ ጥላውን ራሱ መንካት የተሣነን በምን የተነሣ ነው ግን???!!! ታላቅ ሆነን ሣለ፣ ታናናሾች እንድንሆን የሆንነው በምን የተነሣ ነው??!
ዕድል ነው? ወይስ ትንቢት? ስንፍና ነው? ወይስ መድከም? የአኗኗር ዘይቤ? የፍላጎት ማጣት? ማቃት? ወይስ… ወይስ ሰው ነው ችግሩ?? እንዲያውም ሰው ነው መሠለኝ ያጣነው እኛ?? ሰው ነው መሠለኝ ያጣችው አፍሪካ??! ይሆን ይሆን ወይ??? ቆይ ደቡብ አፍሪካን እንውሰድ፡፡ አፍሪካዊው ቀደምት ነዋሪ.. ከተፈጥሯዊው አኗኗሩ አልፎ… አሁን እንግሊዞቹና ደቾቹ ወራሪዎች ፈጥረውት የምናየውን ዓይነት የማቴሪያል ብልጽግና ለመፍጠር ወይ ፍላጎቱ ያልነበረው ህዝብ ነበር፣ ወይ አቅሙ ያልነበረው፣ ወይ ዕውቀቱ ያልነበረው፣ ወይ እየፈለገ እንዲሣነው የሆነ ያልታደለ አፍሪካዊ ማህበረሰብ ነበር ማለት እኮ ነው፡፡ ልዩነቱ እኮ የሰው ልዩነት ነው፡፡ እነዚያ ካውሮፓ መጥተው የረገጧትን ሥፍራ አውሮፓ አስመሰሏት… ዙሉዎቹ ደግሞ ከጥንት ጀምረው ተፈጥሯዊውን አኗኗራቸውን ተቀብለው በፀጥታና በዝንጋታ ከድሮ እስከ ዘንድሮ ይኖራሉ፡፡ ታዲያ ልዩነቱ ሰው ይሆን – ላንዱ ማደግ ለሌላው ባለበት መቅረት ለሌላው እያደር ወደኋላ መሆን??!! ቢሆን ነው እንጂ!!
አንዱን ሀገር ገናና፣ አንዱን ሀገር ኢምንት፣ አንዱን ሀገር ሀብታም፣ አንዱን ሀገር መናጢ ያረጉት ሰዎች ናቸው፡፡ ሰው ነው ልዩነት ፈጣሪው፡፡ ሰው ነው የውድቀትም የመነሳትም ምንጩም፣ ፍጻሜውም፡፡ ታላቋ አፍሪካ ሰው በማጣት ነው ዘወትር ልጆቿን ባህር የምታስበላ፣ እርስበርሷ የምትበላላ የጎስቋሎች መንደር፣ የቅን አሳቢዎች ማፈሪያ ሥፍራ ሆና በዓለም ፊት መሣለቂያ ሆነን፣ ተገፍተን እንድንቀር የሆንነው፡፡ አፍሪካ ተፈጥሮ አልጎደላትም፡፡ አፍሪካ ታሪክ አልጎደላትም፡፡ አፍሪካ ትልም አልጎደላትም፡፡ አፍሪካ ፋና አልጎደላትም፡፡ አፍሪካ የራሷን የታላቅነት ናሙናም አላጣችም፡፡ የአፍሪካ ጠኔ – የሰው ጠኔ ነው፡፡ የኢትዮጵያም እንደዚያው፡፡ ጠኔያችን የሰው ነው፡፡ ሀገር የሚለውጠው ሰው ነው፡፡ ሰው ነው መድሀኒታችን፡፡ ሰው ነው መጥፊያችን፡፡ መድሃኒታችንን ሰውን እንመልከት፡፡ እንደ ሰው እንብዛ፡፡ እናስብ፡፡ እንተሳሰብ፡፡ እና … በጋራ እንበልጽግ፡፡ ወደ ቀድሞ ከፍታችን ላይ፡፡ ሌሎቹ ወደነኩት የብልጽግና ጫፍ ላይ — በራዕይ እንማትር፣ በአዕምሯችን እንንጠራራ፣ በልቀት እንድረስ — ሰው እስከያዝን ድረስ — ወደማይቀረው — ወደ ታላቁ ኢትዮጵያዊ ከፍታችን፡፡
አምላክ ማህደረ ታሪክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ ቻው፡፡
በፎቶግራፍ የሚታየው የኢትዮጵያ ታሪክ መጽሐፍ (እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
“A new history of ethiopia being a full and accurate description of the kingdom of Abyssinia. 1684
Filed in: Amharic